ፈልግ

ከ10,000 የሚበልጡ የዳ ናንግ ሀገረ ስብከት ምዕመናን በቬትናም በሚገኘው የእመቤታችን ትራ ኪዩ ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ንግደት ያደርጋሉ ከ10,000 የሚበልጡ የዳ ናንግ ሀገረ ስብከት ምዕመናን በቬትናም በሚገኘው የእመቤታችን ትራ ኪዩ ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ንግደት ያደርጋሉ  

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቬትናም የእመቤታችን ድንግል ማሪያም መገለጥን በማስመልከት መንፈሳዊ ንግደት ያደርጋሉ

የግንቦት ወርን ለማገባደድ እና ለጴንጤቆስጤ ቀን ለመዘጋጀት በቬትናም፣ የዳ ናንግ ሀገረ ስብከት ካቶሊኮች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ወደተገለጠችበት ስፍራ መንፈሳዊ ንግደት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥አዲስ አበባ

በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የተሰየመውን የግንቦት ወር ማጠቃለያን ለማክበር በዳ ናንግ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከ10,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ ከሚሸፍነው የተለያዩ አድባራት እና ማኅበረሰቦች የተውጣጡ ከ10,000 በላይ ሰዎች ወደ ትራ ኪዩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ።

ሃይማኖታዊ ክስተት
የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ እንደዘገበው ‘ማሪያን’ ተብሎ የሚጠራው ቤተ መቅደስ እናታችን ድንግል ማርያምን ከ140 ዓመታት በፊት የተገለጠችበት ቤተ መቅደስ ሲሆን፥ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአከባቢው ከሚገኙ የተለያዩ አቢያተ ክርስቲያናት በርካታ ምዕመን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ።

በአካባቢው ትውፊት መሰረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆቿን በችግር ጊዜ ለማጽናናት፣ ለማበረታታት እና ለመርዳት እንደታየች ይታመናል።

በርካታ ምእመናን በዚህ የድንግል ማርያም ጉብኝትን አስመልክቶ በሚከበረው ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት መንፈሳዊ ንግደት የሚያደርጉ ሲሆን፥
የሀዩ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጆሴፍ ዳንግ ዱክ ይሄንን መፈሳዊ ንግደት “የፍቅር፣ የእምነት፣ የቁርጠኝነት እና የአገልግሎት፣ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በመጋፈጥ እምነታችንን የምንገልጽበት አጋጣሚ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ድርብ ትርጉም
መንፈሳዊ ጉዞው የግንቦት ወር መጨረሻን ከማመልከት በተጨማሪ ሰኔ 1 ለሚከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል የሚዘጋጁበት እድል ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፥ በዕለቱም እመቤታችን ድንግል ማርያም “የጴንጤቆስጤ ሴት” በመባል እንደምትዘከር ተገልጿል።

በቬትናም ካቶሊኮች ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ 7 በመቶ ያክል (ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጋ) ሲሆኑ፥ ለድንግል ማርያም ባላቸው ጽኑ ፍቅር እና ክብር ይታወቃሉ።

በግንቦት ወር ውስጥ በተለያዩ የማሪያን ቤተ መቅደሶች የተለያዩ ክብረ በዓላት፣ የጸሎት ዝግጅቶች፣ መስዋእተ ቅዳሴዎች እና የማህበረሰብ መቁጠሪያ ጸሎቶች ይካሄዳሉ። 

የማርያምን ወር ለማክበር ምዕመናን በሀገሪቷ ታሪክ ውስጥ በከባድ ስደት ወቅት ካቶሊኮችን ለማዳን እመቤታችን ድንግል ማሪያም የታየችባቸውን ቦታዎች ይጎበኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ ለአብነት በሁዌ ሀገረ ስብከት ወደምትገኘው ወደ ላ ቫንግ እመቤታችን፣ በሱዋን ሎክ ሀገረ ስብከት ወደምትገኘው ወደ ኑኢ ኩይ እመቤታችን፣ እንዲሁም በዳ ናንግ ሀገረ ስብከት ወደምትገኘው ትራ ኪዩ ቤተ መቅደስ የማርያምን አማላጅነት እና ጥበቃን ለመጠየቅ በርካታ ሰዎች መንፈሳዊ ንግደት ያደርጋሉ።

የካቶሊካዊነት መነሻ
ሊቀ ጳጳስ ዳንግ ዱክ ትራ ኪዩ ወደሚገኘው የማሪያን ቤተ መቅደስ የሚደረገውን መንፈሳዊ ንግደት “ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን በእምነት፣ በፍቅር፣ በወንጌል አገልግሎት አብረን እየተጓዝን ጥሪያችንን እና ተልእኳችንን የምናድስበት የግለሰብ ድርጊት ብቻ ሳይሆን የጋራ ተግባር ነው” ሲሉ ገልፀውታል።

በጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ 1615 ዓ.ም. ወንጌልን ለመስበክ ሦስት የኢየሱሳውያን ማህበር ሚስዮናውያን ሆይ አን በመግባት አገልግሎት በመጀመራቸው ምክንያት የዳ ናንግ ሀገረ ስብከት በደቡባዊ ቬትናም ክልል የካቶሊክ እምነት መነሻ ተደርጎ እንደሚወሰድ ይገለፃል።

በ 17 ኛው እና በ 18 ኛው ክፍለ ዘመን የዳ ናንግ ሀገረ ስብከት በደቡባዊ ቬትናም ውስጥ ከሚገኙት የኮቺቺና ሀገረ ስብከት ዋና ማዕከላት አንዱ ሲሆን የበርካታ ሚስዮናውያን መዳረሻም ነበር።

ቬትናም የመጀመሪያ ሰማዕታቸው የሆኑት እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፁዕ መሆናቸው የተረጋገጠላቸው የፑ የን ሃገረ ስብከት ካቴኪስት የነበሩት ብፁእ እንድርያስ ሃገር ናት።
 

05 Jun 2025, 15:33