ፈልግ

የእስራኤል እና የኢራን ግጭት፤ የእስራኤል እና የኢራን ግጭት፤  

የአሜሪካ ካቶሊካዊ ጳጳሳት፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሰላም ጥረት እንዲያደርግ አሳሰቡ

በእስራኤል እና በኢራን መካከል እየተፈጸመ ያለው የእርስ በእርስ ጥቃት አምስተኛ ቀኑን በያዘበት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ካቶሊካዊ ጳጳሳት አገራቸው እና ሰፊው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት፥ መንግሥታቸው እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ፥ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለማደስ የሚቻላቸውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አሁን በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ግጭት ዓርብ ሰኔ 6/2017 ዓ. ም. እስራኤል በኢራን ላይ በጀመረችው የአየር ጥቃት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት እና በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ሲገደሉባት እንደ ነበር ታውቋል። ኢራን በእስራኤል ኢላማዎች ላይ የሚሳኤል እና የሮኬት ጥቃቶችን በማካሄድ ምላሽ መስጠቷ ታውቋል። አንዱ በሌላው ላይ በፈጸመው ጥቃት በኢራን ውስጥ ከ220 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በእስራኤል 21 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ይህ ጥቃት እስከ ማክሰኞ ድረስ መቀጠሉ ታውቋል።

በአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የዓለም አቀፍ ፍትህ እና ሰላም ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቡነ ኤሊያስ ዛይዳን በጉባኤ ስም በሰጡት መግለጫ፥ “በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ተጨማሪ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መስፋፋት እና የጥቃት መባባስ በአካባቢው ያለውን ደካማ መረጋጋት አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሰላምን የመደገፍ ግዴታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን በመጥቀስ የተናገሩት አቡነ ዛይዳን፥ “የሁሉም አገሮች ደኅንነት እና ክብርን የሚያረጋግጡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስጀመር የሰላም ጥረትን መደገፍ የሁሉም አገሮች ግዴታ ነው” ብለዋል።

የኢራን መዲና ቴህራን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ጆሴፍ ማቲዩን በጸሎት የተቀላቀሉት አቡነ ኤሊያስ ዛይዳን፥ “በመግባባት ላይ በተመሠረተ ውይይት የሚመጣ ሰላም እንዲሰፍን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

አቡነ ኤሊያስ ዘይዳን እንደዚሁም፥ ካቶሊካዊ ምእመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ “በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ በትጋት እንዲጸልዩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

እስራኤል ዕርዳታን የሚጠብቁ ፍልስጤማውያንን ገደለች

በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ብጥብጥ እየተባባሰ በሄደበት በዚህ ወቅት የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚፈጽመውን ጥቃት መቀጠሉ ታውቋል።

የጋዛ ባለስልጣናት ማክሰኞ ሰኔ 10/2017 ዓ. ም. ባወጡት ሪፖርት፥ በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ካን ዮኒስ ከተማ ውስጥ የዕርዳታ መኪኖችን ሲጠብቁ የነበሩ ቢያንስ 51 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር ለውንጀላው ወዲያውኑ የሰጠው ምላሽ የለም።

የዜና ወኪሎች የዓይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ባወጡት ዘገባ፥ የእስራኤል ታንኮች ሰብዓዊ እርዳታን በመጠባበቅ ላይ በነበሩት ሰዎች ላይ ተኩሱ መክፈታቸውን ያስታወቁ ሲሆን፥ ይህም በፍልስጤም ሲቪሎች ላይ የጅምላ ሞትን ያስከተለ የቅርብ ጊዜ ክስተት እንደሆነ ተነግሯል።

 

 

17 Jun 2025, 17:15