ፈልግ

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ 

ፍቅር በቤተሰብ፥ “የተክሊል እና የቤተሰብ መንፈሳዊነት”

ልግስና ከተጠራንበት የሕይወት ሁኔታ ላይ የተመረኮዙ የተለያዩ ቀለሞች ይኖሩታል። ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ስለ ምእመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲናገር፣ ከቤተሰብ ሕይወት ስለሚፈልቅ መንፈሳዊነት ትኩረት ሰጥቶ ነበር። ጉባኤው እንዳመለከተው፣ የምእመናን መንፈሳዊነት “ልዩ ባህርዩን የሚቀዳጀው… ከባለትዳሮችና ከቤተሰብ የሕይወት ሁኔታዎች ነው” ስለሆነም “የቤተሰብ እንክብካቤ ለዚያ መንፈሳዊነት ባእድ መሆን የለበትም”። እዚህ ላይ ትንሽ ቆም ብሎ በቤተሰብ ሕይወትና በግንኙነቶቹ ውስጥ ስለሚከሰተው ልዩ መንፈሳዊነት አንዳንድ መሠረታዊ ባሕርያት ማብራራት ጠቃሚ ይሆናል።

የመለኮታዊ ልዕለ ሱታፌ መንፈሳዊነት

እግዚአብሔር በጸጋው ሥር በሚኖሩ ሰዎች ልብ ውስጥ እንዴት እንደሚኖር በተደጋጋሚ ተነጋግረናል። ዛሬ ቅድስት ሥላሴ መለኮት በጋብቻ ሱታፌ ቤተመቅደስ ውስጥ ይኖራል የሚለውን ሐሳብ እናክልበታለን። እግዚአብሔር የሕዝቡ ምሥጋና ሆኖ እንደሚኖር ሁሉ (መዝ. 22፡ 2) እንዲሁ ለእርሱ ክብር በሚሰጥ በጋብቻ ፍቅር ውስጥ ይኖራል።

የጌታ መኖር በእውነተኛና ተጨባጭ ቤተሰቦች፣ በዕለታዊ ችግሮቻቸውና ትግሎቻቸው፣ በደስታቸውና በተስፋቸው ሁሉ ውስጥ ይኖራል። በቤተሰብ ውስጥ መኖር እንዳናስመስልና እንዳንዋሽ ያደርገናል፤ ከጭምብል ኋላ መደበቅ አንችልም። ይህ እውነተኛነት በፍቅር የሚመራ ከሆነ፣ ጌታ ከደስታውና ከሰላሙ ጋር በዚያ ይኖራል። የቤተሰብ ፍቅር መንፈሳዊነት በሺህ በሚቆጠሩ ትናንሽ፣ ነገር ግን፣ እውነተኛ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነው። ሱታፌን በሚያጠናክረው በዚያ የስጦታዎችና የግንኙነቶች ብዛት ውስጥ እግዚአብሔር የሚኖርበት ስፍራ አለው። ይህ የጋራ ሐሳብ በእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ ስለ ሆነ “ሰብዓዊውንና መለኮታዊውን ሐሳብ አንድ ያደርጋል”። በመጨረሻም፣ የጋብቻ መንፈሳዊነት መለኮታዊ ፍቅር የሚኖርበት የአንድነትና የትስስር መንፈሳዊነት ነው፡፡

የቤተሰብ አንድነት አዎንታዊ ተሞክሮ ወደ ዕለታዊ ቅድስናና መንፈሳዊ እድገት የሚመራ እውነተኛ መንገድና ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅ ኅብረት ለመፍጠር የሚያስችል ዘዴ ነው። የቤተሰብ ሕይወት የሚጠይቃቸው ወንድማዊና ማኅበራዊ ግዴታዎች በልባዊ ግልጽነት ለማደግና ከጌታ ጋር የበለጠ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያነሣሡ ናቸው። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን፣ “ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል” (1 ዮሐ. 2፡ 11)። እንዲህ ዐይነቱ ሰው “በሞት ይኖራል” (1 ዮሐ. 3፡ 14) እንጂ “እግዚአብሔርን አያውቅም” (1 ዮሐ. 4፡8)። ከእኔ በፊት የነበሩት ቤነድክቶስ 16ኛ እንዳመለከቱት፥ “ለጎረቤታችን ዐይናችንን መጨፈን እግዚአብሔርንም እንዳናይ ያደርገናል”፣  ስለዚህ፣ ፍቅር “የደበዘዘውን ዓለም ያለማkረጥ የሚያበራ” ብቸኛ ብርሃን ነው። “እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል” (1 ዮሐ. 4፡12)። “የሰው ልጅ በባህርዩ ማኅበራዊ ገጽታ ስላለው” እና “የሰው ማኅበራዊ ገጽታ ቀዳሚና መሠረታዊ መገለጫ ደግሞ ባለ ትዳር ጥንዶችና ቤተሰብ ስለሆኑ” መንፈሳዊነት በቤተሰብ ሱታፌ ውስጥ እውን ይሆናል። ስለዚህ፣ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የቤተሰብ መኖር በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ከማደግ ያሰናክለናል ብለው ማሰብ የለባቸውም፤ ይልቁንም ጌታ ወደ መንፈሳዊ የአንድነት ከፍታ ሊመራቸው የሚጠቀምበት መንገድ ይህ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል።

በትንሣኤ ብርሃን ለጸሎት መሰብሰብ

 አንድ ቤተሰብ ክርስቶስን ማዕከሉ ያደረገ ከሆነ፣ እርሱ መላ ሕይወቱን አንድ ያደርገዋል፣ ያበራዋል። ከጌታ መስቀል ጋር ሆኖ የሥቃይና የችግር ወቅቶችን መጋፈጥ ይችላል፣ በእርሱም ቅርበት ድልን ይቀዳጃል። የቤተሰብ ሕይወት በሚጨልምባቸውና በብቸኝነት ሰዓታት፣ ከኢየሱስ ጋር አንድ መሆን ቤተሰብን እንዳይፈርስ ይረዳዋል። ቀስ በቀስ “በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በመታገዝና ችግርንና መከራን ወደ ፍቅር መሥዋዕት በሚለውጠው በክርስቶስ የመስቀል ምሥጢር በመካፈል፣ ባልና ሚስት በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ በቅድስና ያድጋሉ”። ከዚህ በተጨማሪ፥ የደስታ፣ የመዝናኛ፣ የፈንጠዝያና የወሲባዊነት ወቅቶች ጭምር በትንሣኤ ሙሉ ሕይወት በመካፈል ሊገለጹ ይችላሉ። ባለ ትዳሮች በተለያዩ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው አማካይነት “ከሙታን የተነሣውን የጌታን ስውር መኖር የሚያውቁበትን በእግዚአብሔር ብርሃን የደመቀ ስፍራ ያዘጋጃሉ”።

የቤተሰብ ጸሎት ይህን የፋሲካ እምነት ለመግለጽና ለማጠናከር ዓይነተኛ መንገድ ነው። በሕያው እግዚአብሔር ፊት በአንድነት ለመሰብሰብና ጭንቀታችንን ለእርሱ ለመንገር፣ የቤተሰባችንን ፍላጎት እንዲያሳካ ለመለመን፣ ችግር ለደረሰበት ሰው ለመማለድ፣ ፍቅር ለማሳየት እንዲረዳን ለመማጸን፣ ሕይወትንና በረከትን ስለ ሰጠን ለማመስገን፣ እንዲሁም ከእናታዊ ካባዋ ሥር እንድትጠብቀን እመቤታችንን ለመለመን በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎችን ማግኘት ይቻላል። በጥቂት ቀላል ቃላት፣ ይህ የጸሎት ወቅት በቤተሰቦቻችን ውስጥ ትልቅ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። የሕዝባዊ ጸሎት የተለያዩ መገለጫዎች ለብዙ ቤተ ሰቦች የመንፈሳዊነት ቅርስ ናቸው። የቤተሰብ የጋራ የጸሎት ጉዞ ማሳረጊያው በመሥዋዕተ ቅዳሴ፣ በተለይም በእሁድ የዕረፍት ቀን፣ በአንድነት በመካፈል ነው። ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ቁርባናዊ እራት ለመብላት የቤተ ሰቦችን በር ያንኴኴል (ራእይ 3፡20)። ባልና ሚስትም በአንድነት ያጣመራቸውንና እግዚአብሔር በመስቀል ላይ ከሰው ዘር ጋር ያቆመውን ቃል ኪዳን የሚያንጸባርቀውን የፋሲካ ቃል ኪዳን ሁልጊዜ እንደ ገና ያድሱታል። መሥዋዕተ ቅዳሴ የክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚከናወንበት የአዲስ ኪዳን ምሥጢር ነው (ሉቃ. 22፡ 20)። ያን ጊዜ፣ በትዳር ሕይወትና በመሥዋዕተ ቅዳሴ መካከል ያለው የቅርብ ትስስር ይበልጥ ግልጽ ይሆናል።  ምክንያቱም የቁርባን ምግብ ለባልና ሚስት በየዕለቱ በቃል ኪዳናቸው መሠረት “የቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን” ሆነው ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬና ብርታት ይሰጣቸዋል።

ብቸኛ እና ነጻ ፍቅር መንፈሳዊነት

ጋብቻ ሙሉ በሙሉ ለእርስ በርስ የመሰጣጣት ተሞክሮ ነው። ባልና ሚስት እርስ በርስ የመደጋገፍ፣ አብሮ በዕድሜ የመግፋትና በዚህም መንገድ የእግዚአብሔርን ታማኝነት የመግለጽ ተግዳሮትና ተስፋን ይቀበላሉ። የአኗኗር ዘይቤን የሚቀርጸው ይህ ቁርጥ ውሳኔ “የጋብቻ ፍቅር ቃል ኪዳን የሚጠይቀው ውስጣዊ ግዴታ ነው” ምክንያቱም “ለዘላለም መውደድ ምርጫው ያልሆነ ሰው ለአንድ ቀን እንኳ መውደድ አይችልም”። ከዚህ ሌላ፣ ይህን የመሰለ ታማኝነት በፈቃደኝነት ለሕግ የመገዛት ጉዳይ ብቻ ከሆነ መንፈሳዊ ትርጉሙን ያጣል። ስለዚህ ፍቅር እግዚአብሔር ብቻ የሚያየው የልብ ጉዳይ ነው (ማቴ. 5፡28)። በየቀኑ፣ ጠዋት ከእንቅልፍ ስንነሣ፣ በቀኑ ውስጥ ምንም ነገር ቢያጋጥመን፣ ታማኝ የመሆን ውሳኔያችንን በእግዚአብሔር ፊት እናረጋግጣለን። ሁላችንም፣ ወደ መኝታ ከመሄዳችን በፊት፣ በእግዚአብሔር ረድኤት በመተማመን ይህን ገድል ለመቀጠል እንደምንነቃ ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ መንገድ፣ እያንዳንዱ ባለ ትዳር ለሌላው ብቻችንን ምን ጊዜም የማይተወንና “እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡20) የሚለው የጌታ ቅርበት ምልክትና መሣሪያ ይሆናል።

የባልና ሚስት ፍቅር ወደ ነጻነት ከፍታ የሚደርስበትና ለጤናማ ራስን መቻል መሠረት የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። ይህም የሚሆነው፣ ጥንዶቹ እርስ በርሳቸው ሳይሆኑ፣ ከሁሉ የሚበልጠው የአንድያ ጌታ ወገን መሆናቸውን ሲያውቁ ነው። የምንወደውን ሰው ጥልቅና ግላዊ ጓዳ ማወቅ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ የሕይወታቸው ዋና እምብርትም እርሱ ብቻ ነው። ከዚህ ሌላ፣ የመንፈሳዊ እውነታ መርሆ አንዱ ባለትዳር የሌላውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ማርካት ይችላል ብሎ አያስብም።  ዲትሪሽ ቦንሆፌር በሚገባ እንዳስቀመጠው፣ የእያንዳንዳቸው መንፈሳዊ ጉዞ ሌላውን “በገራገርነት ማመንን” እና የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ማድረግ የሚችለውን ነገር ከሌላው መጠበቅን ማቆም እንዳለባቸው ሊያደርጋቸው ይገባል። ይህ ደግሞ ውስጣዊ ነጻነትን ይጠይቃል። ጥንዶች ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖራቸው ግላዊ ግንኙነት የሚሰጡት ልዩ ቦታ በጋራ ሕይወት የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን ለመካስ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ የራሳቸውን ሕይወት ጥልቅ ትርጉም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እኛም በየቀኑ ይህን ውስጣዊ ነጻነት እውን እንዲያደርግልን የመንፈስ ቅዱስን ረድኤት መለመን አለብን።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 316-320

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

19 Jul 2025, 16:13