ፈልግ

የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ጉባኤ የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ጉባኤ 

የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን አዲስ መንገድ ማዘርጋታቸው ተገለጸ

በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከ “ዋታዋ ዋ ታ” ወይም “የብርሃን ልጆች ገዳማውያት” ማኅበር ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ምሁራን ጉባኤ አዘጋጅቷል። ይህ ትልቅ ጉባኤ ሴቶች በሥነ-መለኮት ዕውቀት እና በቤተ ክርስቲያን አመራር ውስጥ ያላቸውን ድምፅ ለማጉላት ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሲኖዶሳዊነት በተግባር” በሚል ዋና ርዕሥ እያበቡ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች፣ የሴቶች አስፈላጊነት እና አስተዋይ የአመራር ብቃት” በሚል ንዑስ ርዕሥ ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜ /2017 ዓ. ም. ድረስ በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የተውጣጡ እውቅ የሃይማኖት ምሁራን፣ ካኅናት እና ሐዋርያዊ መሪዎች ተሳትፈዋል። ጉባኤው በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ የቤተ ክርስቲያንን የወደፊት ሁኔታ በመቅረጽ ሂደት ሴቶች በሚጫወቱት ሚና ላይ የሚደረገውን ውይይትን ለማበረታታት እንደ ሆነ ታውቋል።

በሥነ-መለኮት ውስጥ ያለውን የሥርዓተ-ፆታ ክፍተት ማሳወቅ

ምንም እንኳን የአስርተ ዓመታት እድገት ቢኖርም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የሥነ-መለኮት ትምህርት በአብዛኛው ለወንዶች የሚሰጥ በተለይም ለክኅነት በሚዘጋጁባቸው የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጥ እንደሆነ ይታወቃል። የጉባኤው ሰብሳቢ፣ በሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ርዕሠ መምህር እና የቅድስት ሐና ፍራንችስካዊ ማኅበር አባል እህት ጃሲንታ አውማ ኦፖዶ በቃለ ምልልሳቸው ይህ አለመመጣጠን የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ይጎዳል ሲሉ ተናግረዋል።

እህት ጃሲንታ በቃለ ምልልሳቸው እንደገለጹት፥ ጉባኤው የአፍሪካ ሴቶችን ሥነ-መለኮታዊ ድምጽ ለማጉላት በሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተጀመረ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸው፥ “የሥነ-መለኮት ስልጠና ያለ ሴቶች አስተዋፅዖ የተሟላ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።  የሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሩን ለሴቶች ከከፈተ ከአርባ ዓመታት በኋላም ድምፃቸው ያልተወከለ መሆኑን ገልጸው፥ ጉባኤው የአፍሪካ ሴት የሥነ-መለኮት ምሁራን ድምጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰማ መድረክ ለመፍጠር እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ሴቶች የሥነ-መለኮት ሊቃውንት ጉባኤ፥ የሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሴቶችን የሥነ-መለኮት ሊቃውንት ቁጥር ለማሳደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሷል። የዘንድሮው ዓመት ቀጣይ ጉባኤ በሲኖዶሳዊነት፣ በኅብረት እና በጋራ ተልዕኮ አብሮ ለመራመድ በቤተ ክርስቲያን ጥሪ ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ታውቋል። ዓላማው ተሞክሮዎችን፣ ተግዳሮቶችን እና ዕድሎችን ማካፈል ብቻ ሳይሆን በሥነ-መለኮታዊ ንግግር እና በሐዋርያዊ አገልግሎት ልምምድ የሴቶችን አመራር ለማጠናከር ጭምር እንደ ነበር ተመልክቷል።

ሲኖዶሳዊነት እና የሴቶች ሚና

ሲኖዶሳዊነት እንደ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አገላለጽ፥ የአካታች ቤተ ክርስቲያን ራዕይ ማዕከል መሆኑን ጉባኤው አመልክቷል። እህት ጃሲንታ አውማ ኦፖዶ በቃለ ምልልሳቸው፥ እውነተኛ ተሳትፎ ለሴት የነገረ-መለኮት ምሁራን ትምህርትን፣ ትስስርን እና የአመራር ዕድሎችን የሚጠይቅ መሆኑን አሳስበው፥ የዘንድሮው ጉባኤ በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያሰላሰሉ የተለያዩ ድምፆችን ማሰባሰቡን ገልጸዋል። ዋና ዓላማው የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ምሁራን ከወጣት ምሁራን ጋር ለመምከር፣ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተባብሮ ለመሥራት፣ በጥናት እና በምርምር፣ በጽሁፍ እና በሐዋርያዊ አገልግሎት ተነሳሽነት፥ የነገረ መለኮት ትምህርት እና የሰበካ ሕይወት ላይ ተጽእኖ ለማድረግ የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ምሁራን መረብን ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች
የጉባኤው ተሳታፊዎች

ከጉባኤው ተሳታፊዎች የቀረበ የፈውስ እና የተስፋ ድምጽ

“የተቀደሰ አንድነት እህቶች ማኅበር” አባል፣ የሥነ-ልቦና መንፈሳዊ ቴራፒስት እና አማካሪ የጉባኤው ተሳታፊ እህት ጂሴላ ራፋንዩ፥ ምክርን ማሳደግ በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማዳመጥን እንደሚያጎለብት አስረድተዋል።

ምክርን ማዳመጥ ያበረታታል ያሉት እህት ጂሴላ፥ ሥነ-መለኮት ረቂቅ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት በሕይወት እውነታዎች ውስጥ እምነትን ማስተዋል እንደሆነ ተናግረዋል። የሐዋርያዊ እረኝነት እንክብካቤን እና መንፈሳዊ ሕክምናን ከቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ጋር ማዋሃድ ለቆሰለው ዓለም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት እና በትውፊት ሥር ሆኖ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ሕይወት ጥልቅ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ሂደትን የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ሴት የሥነ-መለኮት ሊቃውንት ልዩ የሆነ የእንክብካቤ፣ የምክንያታዊነት፣ የፈውስ እና የመደመር አመለካከቶችን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያመጡ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ የአፍሪካ ሴት የሥነ-መለኮት ሊቃውንት የወንዶችን መዋቅር በመቃወም በቤተ ክርስቲያን እና በኅብረተሰብ ውስጥ ለፍትህ እና ለእኩልነት የሚሟገቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከንግግር አልፎ ወደ ተግባራዊነት መሸጋገር 

የጉባኤው ተሳታፊዎች የሴቶችን ግንዛቤ ከሥነ-መለኮት ትምህርት እና ከቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ጋር ለማዋሃድ በርካታ ስልቶችን ለይተዋል። እነዚህም በወንዶች እና በሴቶች መካከል የተባበረ የስልጠና ስልቶችን መጠቀም፣ በጋራ ሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ ሕገ-ቀኖናን መተግበር፣ መደማመጥን መፍጠር እና ለአፍሪካ እውነታዎች ምላሽ የሚሰጡ አካባቢያዊ የሥነ-መለኮት ማስተዋወቅን እንደሚያካትቱ ተነግሯል። ለውጥን መቋቋም እና የሃብት ውስንነ ከተግዳሮቶቹ መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ ያሚናገሩት የጉባኤው አዘጋጆች፥ ውይይት እና አጋርነት እነዚህን መሰናክሎች እንደሚያሸንፉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

“የብርሃን ልጆች ገዳማውያት” ማኅበር ሚና

በጉባኤው ላይ ተደጋጋሚ ጭብጥ ሲያቀርብ የነበረው እና በኦሃዮ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ደም የገዳማውያት ማኅበር አባል በሆኑት በእህት ሙምቢ ኪጉታ የተመሠረተው የ “ዋታዋ ዋ ታ” ወይም “የብርሃን ልጆች ገዳማውያት” ማኅበር አስተዋፅዖ፥ የአፍሪካ ገዳማውያት የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ለማጉላት እንደሆነ ተገልጿል። ለሃሳቦች እንደ አቃፊ ሆኖ የሚሠራው በ “ዋታዋ ዋ ታ” ሠንድ ውስጥ የተጠቀሱት የችግር እና የመገለል ታሪኮች ገዳማውያቱ በፍትህ፣ በሰላም፣ በትምህርት እና በሐዋርያዊ የእንክብካቤ አገልግሎቶች የተሰማሩ መሆናቸውን ይዘግባል።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወን አብዛኛው የሴቶች ሥራ የተሰወረ እና በሠነድ ውስጥ ያልተጠቀሰ መሆኑ የተናገሩት የሰብሰባው አስተባባሪ፥ የ “ዋታዋ ዋ ታ” ማኅበር ታሪኮችን ለሌሎች መናገር የሚያበረታታ እና የሲኖዶሳዊነት ጉዞን የሚያበለጽግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ውጥኑ ሕይወትን የሚለውጥ ነው” ያሉት እህት ጂሴላ፥ “ሴት ልጅን ስታስተምር አገርን ታስተምራለህ” ብለው፥ የ “ዋታዋ ዋ ታ” ማኅበር የነገረ መለኮት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ ማድረጉን እና ሴቶች ቤተ ክርስቲያንን ትርጉም ባለው መንገድ የማገልገል አቅም እንዳላቸው እንድመለከት አግዞኛል” ብለዋል። በጉባኤው ላይ ከፍተኛ የሥነ-መለኮት ሊቃውንትን ማዳመጥ ጉዞውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ማጠናከሩን ግልጸው፥ በጦርነት የተበጣጠች አገራቸውን ለመፈወስ፥ በፍትህ እና በሰላም ዙሪያ የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም ለመከታተል ሕልም እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጉባኤ
የሄኪማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጉባኤ

በኅብረት የምትጓዝ ቤተ ክርስቲያን

በጉባኤው ማጠቃለያ፥ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነትን እንደ አኗኗር ዘይቤ በመቀበል፣ በኅብረት መጓዝን፣ ቁስሎችን በመስማት የፈውስ እና የተልዕኮ ማኅበረሰብ መሆን እንዳለባት መልዕክት ቀርቧል። ሴት የነገረ-መለኮት ምሁራን የቤተ ክርስቲያን የወደፊት ሁኔታን በመቅረጽ እውነተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልጉ ተገልጿል።

የጉባኤው መሪ እህት ጃሲንታ በንግግራቸው፥ “ጉባኤው ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት መዋቅር እንዲደርሱ እና በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ ያላቸውን ትብብር እንደሚያበረታታ ተስፋ አለኝ” ብለዋል። የስልጣን ባለቤት የሆኑ ሴት የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ማለት ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ማለት እንደ ሆነ፥ ሁሉንም የምታካትት፣ ፍትሃዊ እና ለአህጉራችን እውነታዎች ምላሽ የሚሰጡ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። ጉባኤው በተስፋ እንደሞላቸው የተናገሩት እህት ጃሲንታ፥ ይህም ቤተ ክርስቲያን በትህትና እና በኅብረት ለማደግ ፈቃደኛ መሆኗን እንደሚያሳይ ተናግረው፥ በኅብረት የሚጓዙ ከሆነ መጪው ጊዜ ብሩህ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 2025 ዓ. ም. የተካሄደው የአፍሪካ ሴት የነገረ መለኮት ምሁራን ጉባኤ ሲኖዶሳዊነት በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በውይይት፣ በጋራ ትምህርት፣ በሥነ-መለኮታዊ ማስተዋል እና በትብብር ሕይወት እንዲዘራ በማድረግ የለውጥ ጉዞን ማጎናጸፉ ተነግሯል። እህት ኦፖንዶም በበኩላቸው፥ በ “ዋታዋ ዋ ታ” ወይም በ “ብርሃን ልጆች ገዳማውያት” ማኅበር ተነሳሽነት የአፍሪካ ሴት የነገረ-መለኮት ተመራማሪዎች በአህጉሪቱ እና ከዚያም በላይ ላሉት የወንጌል ተልዕኮዎች የበለጠ አሳታፊ፣ ርህሩህ እና እውነት ለምትሆን ቤተ ክርስቲያን ረዳት ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

 

09 Sep 2025, 17:14