በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የአንድነት ተምሳሌት የሆኑት አባ ፔትሮ ፓኦሎ ኦሮስ ሥርዓተ ብፅእና ተካሄደ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የፖላንድ ሊቀ ጳጳስ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተወካይ የሆኑት ብፁእ ካርዲናል ግሪጎርዝ ራይስ እ.አ.አ. በ 1953 ዓ.ም. በሰማዕትነት የተሰውትን እና ቅዳሜ መስከረም 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በዩክሬን፣ ቢልኪ ከተማ ውስጥ ሥርዓተ ብፅእናቸው የተፈጸመላቸውን አባ ፔትሮ ሲገልጹ፥ በአስፈሪ ጦርነቶች በተሞላች፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተከፋፈለች እና ሰዎች በእውነት እርስ በርሳቸው የመገናኘት አቅማቸውን አጥተው በብቸኝነት በሚሰቃዩባት አሁን ባለንባት ዓለም ውስጥ እንደ አባ ፔትሮ ፓኦሎ ኦሮስ ያሉ እውነተኛ ሰዎች ያስፈልጉናል ያሉ ሲሆን፥ ይህ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ክስተት መሆኑን አስታውሰው፥ ሥነ ስርዓቱ በዩክሬን ጦርነት እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሞት ምክንያት በተደጋጋሚ መራዘሙን ገልጸው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቅዳሜ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባቀረቡት የኢዮቤልዩ ዓመት ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ይሄንኑ ማስታወሳቸው ተናግረዋል።
በበጎ አድራጎት የተገለጸ ሕይወት
ብፁእ ካርዲናል ራይስ በ 36 ዓመታቸው በኮሚኒስት አገዛዝ ስለተገደሉት ስለ አዲሱ ብፁእ ሲናገሩ፥ አባ ፔትሮ አጭር ግን ጥልቅ ትርጉም የነበረው ህይወታቸውን ለመልካምነት፣ ለምህረት እና ለበጎ አድራጎት ማዋላቸውን አስታውሰው፥ “ዛሬ መስቀሉ ሞቱ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ህይወቱ የሆነለትን ሰማዕት ብፅእና እናውጃለን” ያሉ ሲሆን፥ የአባ ፔትሮ ኦሮስን ‘ጥልቅ እምነት እና መንፈሳዊነት’ በማስታወስ፣ ጉልበታቸው ከጸሎት ብዛት የተነሳ እንደ ውስጥ እግር መደንደኑን እና ቅዱስ ቁርባንን ለታመመ ሰው ለመስጠት ተንበርክከው በእጃቸው እንደያዙ መሞታቸውን ገልጸዋል።
በምሳሌ ማስተማር
ካርዲናሉ አክለውም አባ ፔትሮ ህይወትን ያስተማሩት በተፃፉ ቃላት ሳይሆን ምሳሌ በመሆን እና በህይወት ኖረው እንደሆነ አስታውሰው፥ ከበርካታ ስብከቶቻቸው ወይም ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው መካከል አንዳቸውም በጽሑፍ መልክ እንዳልቀሩ ገልጸዋል።
ሆኖም ብዙዎች አሁንም ድረስ የእርሳቸውን “መልካም ሥራ” እንደሚያስታውሱ የገለጹት ብፁእ ካርዲናሉ፥ በአባ ፔትሮ ህይወት ውስጥ ድህነት እና በጎ አድራጎት የአንድ ፊት ሁለት ገፅታዎች በመሆን አንድ ባህሪ እንደነበራቸው ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት እሳቸው ይሰጡ ስለነበር ድሃ እንደነበሩ፥ እንዲሁም ድሃ መሆንን ስለሚያውቁ ይሰጡ እንደነበር አስረድተዋል።
ካህኑ ይኖሩበት በነበረው ቤት ውስጥ ከአንድ አነስተኛ ጠረጴዛ እና ከጥቂት ወንበሮች በስተቀር ምንም ነገር እንዳልነበረ ያስታወሱት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተወካይ፥ ከጥልቅ እና መንፈሳዊ እስከ መሰረታዊ እና ቁሳዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን ለሟሟላት ሲሉ የተቀበሉትን ሁሉ ይሰጡ እንደነበር፥ ከዚህም ባሻገር የተቸገሩ ሰዎች ሁልጊዜ ጥሩ የሆነውን እና አዲሱን ነገር መቀበል እንዳለባቸው ያምኑ እንደነበር አስረድተዋል።
በጦርነት ጊዜ ምሕረትን መለማመድ
ብፁእ ካርዲናል ራይስ ለዩክሬን ምዕመናን ባስተላለፉት ጠንካራ እና ወቅታዊ መልዕክት “እናንተ ለበርካታ ዓመታት ግጭትን እና ጦርነትን የታገሳችሁ፣ ቤቶቻችሁንና ንብረቶቻችሁን ብቻ ሳይሆን በዋጋ ሊተመን የማይችል የምትወዷቸው እና የራሳችሁን ህይወት እና ጤና ያጣችሁ፣ ከሁሉም ሰው እርዳታ እና ድጋፍ መጠበቃችሁ ተፈጥሯዊ ቢሆንም፥ ነገር ግን እንደዚህ ባሉ በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት ብፁእ አባ ፔትሮ ‘ፍጹም መሐሪ እንድትሆኑ’ ይነግሯችዋል በማለት መክረዋል።
የበለጸገ መንፈሳዊነት
ብፁዕ ካርዲናል ራይስ በመጨረሻም ሁለቱ የክርስትና ማዕከል በሆኑት በምስራቁ እና በምዕራቡ ዓለም ውስጥ የኖሩት አዲሱ ብፁእ የበለጸገ መንፈሳዊነትን ማዳበራቸውን በማጉላት፥ በእነዚህ ጊዜያት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን በሁለት ዓለማት መካከል “ድልድይ” ሆነው ማገልገላቸውን ያስታወሱ ሲሆን፥ ሁላችንም ድልድይ የምንፈልግ ቢሆንም ነገር ግን በጦርነት ጊዜ ድልድዮች ሁል ጊዜ ቀድመው በቦምብ እንደሚመቱ ማወቅ እንደሚገባ፥ ብሎም ‘ድልድይ’ መሆን ማለት የሚከፋፍል ሳይሆን አንድ የሚያደርግ ሰው እንደሆነ፣ ሰይፍን ወደ ማረሻ የሚቀይር እና የጦር መሣሪያን ወደ ጠቃሚ መሣሪያነት የሚቀይር ሰው መሆን እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ አባ ፔትሮ ከላቲን ወይም ከባዛንታይን ካቶሊኮች፣ ከኦርቶዶክስ እንዲሁም ምንም እምነት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ሳይቀር አንድ የጋራ ቋንቋ መናገር እንደሚችሉም ጭምር አስታውሰዋል።
ሥነ ስርዓቱ ላይ ለመገኘት ወጣቶች ያደረጉት መንፈሳዊ ንግደት
ብፁዕ ካርዲናል ራይስ እንደገለጹት የብፁእ ፔትሮ ህይወት ከታሰሩት፣ ከተሰደዱት፣ ከተሰቃዩት፣ ከተገደሉት ወይም በእስር ቤት ከሞቱት ካህናት ባልንጀሮቻቸው ህይወት ጋር የነበረው ቁርኝት በህይወትም ሆነ በሞት ውስጥ ጠንካራ እና መሰረታዊ ስለሆነው ፍቅር ያስተምረናል በማለት አጠቃለዋል።
ከብፅእናው ሥነ ስርዓት አንድ ቀን ቀደም ብሎ መስከረም 16 ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች የባዛንታይን ሥርዓተ አምልኮን ተከታይ ወደሆነው የሙካቼቮ ሃገረስብከት፣ ወደ ቢልኪ መንደር በእግራቸው መፈሳዊ ንግደት እንዳደረጉ ተነግሯል።