ፈልግ

ብፁዕ ካርሎ አኩቲስ በወጣትነቱ ይለብሰው የነበረው ሰማያዊ ሹራብ ብራዚል፣ ካፖ ግራንዴ ከተማ ውስጥ  የሚገኘው ቤተክርስቲያን ሲደርስ  ብፁዕ ካርሎ አኩቲስ በወጣትነቱ ይለብሰው የነበረው ሰማያዊ ሹራብ ብራዚል፣ ካፖ ግራንዴ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቤተክርስቲያን ሲደርስ  

በብራዚል ምዕመናን በካምፖ ግራንዴ ውስጥ የካርሎ አኩቲስ ሢመተ ቅድስናን አስመልክተው ሳምንታዊ መርሃ ግብር አካሄዱ

ብፁዕ ካርሎ አኩቲስ በህይወት እያለ በወቅቱ ወጣት ጣሊያናዊያን ይለብሱት ከነበረው ታዋቂ አለባበስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እና በበርካታ ፎቶግራፎች ላይ ለብሶ የሚታየው ጥቁር ሰማያዊ ሹራብ ሲሆን፥ ይህ ቅርስ ጳጉሜ 2 በቫቲካን ለሚካሄደው የብፁዕ ካርሎ አኩቲስ ሢመተ ቅድስናን አስመልክቶ ነሃሴ 26 ሳኦ ሴባስቲኦ (ቅዱስ ሴባስቲያን) ቁምስና እንደደረሰ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብጽዕናው በአሲሲ ከተማ ቅዳሜ መስከረም 30/2013 ዓ. ም. የታወጀለት ካርሎ አኩቲስ፥ በዓሉ በፋሲካ ሁለተኛ እሁድ ማለትም ሚያዝያ 19/2017 ዓ. ም. እንዲሆን ቀጠሮ የተያዘለት ቢሆንም ዕለቱ የታዳጊ ወጣቶች ኢዮቤልዩ የሚከበርበት በመሆኑ ወደ ሌላ ጊዜ መዛወሩ ይታወሳል።

ነፍስኄር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ዕለት፥ የወጣት ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና የወጣት ካርሎ አኩቲስ ቅድስናን ለታዳሚዎቻቸው ማሳወቃቸው ይታወሳል።

በደቡባዊ ምዕራብ ብራዚል የምትገኘው ካምፖ ግራንዴ ከተማ ጣሊያናዊው ካርሎ አኩቲስ በወጣትነቱ ይለብሰው የነበረው ሰማያዊ ሹራብ መምጣት ጋር ተደምሮ በጠንካራ እምነት እና ስሜት የተሞሉ ቀናትን እያሳለፈች እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ የዚህ ወጣት ሢመተ ቅድስና እሁድ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚመራ መስዋዕተ ቅዳሴ በቫቲካን እንደሚፈጸም ተነግሯል።

የሢመተ ቅድስና ሳምንት በይፋ መጀመሩን በማስመልከት ቅርሱ ወይም የብፁዕ ካርሎ አኩቲስ ልብስ ሰኞ ነሃሴ 26 ምሽት በእሳት አደጋ መምሪያ ታጅቦ ወደ ሳኦ ሴባስቲኦ ቁምስና መድረሱ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች እንደተሳተፉ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ እንዲገቡ የወሰኗቸው ወጣት ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና ወጣት ካርሎ አኩቲ ከተለያዩ ዘመናት የተውጣጡ፣ ፍጹም የተለያየ ሕይወት ይመሩ የነበሩ፥ ነገር ግን ለኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው ፍቅር እና ሕይወታቸውን ለተነኩ ሰዎች ያንን ፍቅር ለማካፈል ባላቸው ችሎታ አንድ እንደሆኑ ተነግሯል።

ሳኦ ሴባስቲኦ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ሴባስቲያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ከመሠዊያው ፊት ለፊት በመስታወት ሳጥን ውስጥ የሚታየው ይህ የብፁዕ ካርሎ አኩቲስ ሹራብ (ቅርስ) ከሢመተ ቅድስና ሥነ ስርዓቱ በኋላም በቁምስናው ውስጥ እንደሚቆይ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከቀናት በኋላ ቪላ ማርጋሪዳ ወደሚገኘው ተአምራዊው ጸሎት ቤት ከተወሰደ በኋላ እሁድ ዕለት ለምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ወደ ደብሩ እንደሚመለስ አባ ማርሴሎ ቴኖሪዮ ገልጸዋል።

የወጣት ካርሎ እናት አንቶኒያ ሳልዛኖ ልጃቸው ካርሎ በሰባት ዓመት ዕድሜው የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር እንደተቀበለና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ሳያቋርጥ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚሳተፍና ከመስዋዕተ ቅዳሴ በፊት ወይም በኋላ ለቅዱስ ቁርባን ክብር አጭር ጸሎት ያደርግ እንደነበር ተናግረዋል። ልጃቸው ካርሎ ከሌሎች ጓደኞቹ የተለየ ባሕርይ የማይታይበት ነገር ግን ለቅዱስ ቁርባን ያለውን ልዩ አክብሮትና ፍቅር ይናገር እንደነበር፣ በቅዱስ ቁርባን የሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘወትር ታማኝ ጓደኛው እንደሆነ ይናገር እንደነበር ተናግረዋል። ወይዘሮ አንቶኒያ በማከልም ልጃቸው ካርሎ ቤተክርስቲያን በአቅራቢያቸው በመገኘቱ ዕድለኞች መሆናቸውን ይናገር እንደነበር፣ በዚህም ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ኢየሱስ በሚኖርበት ኢየሩሳሌም አካባቢ ከኖሩት ሰዎች ይልቅ የበለጠ ዕድለኞች መሆናቸውና ሕያው ኢየሱስ ክርስቶስን በቅዱስ ቁርባን ውስጥ እናገኘዋለን ማለቱን አስታውሰዋል። በማከልም ካርሎ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገር እንደነበር፣ በቅዱስ ቁርባን በኩል ስለምንቀበለው ደስታ ሌሎችን ማስተማርና ለሌሎች መመስከር ያስፈልጋል ይል እንደነበር አስታውሰዋል።

ወጣት ካርሎ በ15 ዓመት ዕድሜው፣ በ1998 ዓ. ም. ከመሞቱ በፊት በቤተክርቲያን እውቅናን ያገኙ 136 የቅዱስ ቁርባን ተዓምራትን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ ምስሎችን በሰሜን አሜርካ ውስጥ በሚገኙት 10,000 ቁምስናዎች ለእይታ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን፥ ወጣት ካርሎ አኩቲስ ለጓደኞቹ ‘በቤተክርስቲያን ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮች ለመሆን ከፈለጋችሁ የቅዱስ ቁርባን ፍቅር ሊኖራችሁ ይገባል’ ይል እንደነበር እና በተጨማሪም ወጣቱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፊት ለፊት የምንገናኝበትን አጋጣሚ ነው በማለት ይናገር ነበር።

የማቶ ግሮሶ ዶ ሱል ከተማ ገዥ ባለቤት የሆኑት ቀዳማዊት እመቤት ሞኒካ ሪዴል በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የክስተቱን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት ‘በእውነቱ ልዩ እና በጣም አስደሳች ጊዜ’ እንደነበር ገልጸው፥ የካርሎ አኩቲስን ቅርስ ከእኛ ጋር በማግኘታችን በጣም ደስ ብሎናል፣ ገና በርካታ ተአምራትን እንደሚሰራ እናምናለን፥ ይህንን እውነታ ከ 15 ዓመት ወጣት በማየታችን በማይታመን ሁኔታ የካቶሊክ እምነታችንን ያጠናክራል” ብለዋል።

የቅድስና መንገድ
ወጣቱ የቅድስና ማዕረግ የተሰጡት በሁለት ተአምራት እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የመጀመሪያው እ.አ.አ. በ2010 ዓ.ም. በካምፖ ግራንዴ ከተማ ውስጥ ማቲየስ ሊንስ ቪያና የተባለች የ6 ዓመት ልጅ በሳኦ ሴባስቲኦ ቤተ ጸሎት ውስጥ በሚገኘው የካርሎ አኩቲስ ምስል ፊት ከፀለየች በኋላ ከከባድ የጣፊያ እክል እንደተፈወሰች፥ እንዲሁም ሁለተኛው እና ባለፈው ዓመት የተረጋገጠው ቫለሪያ ቫልቬርዴ የተባለች የ 21 ዓመት ተማሪ በደረሰባት ክፉኛ የብስክሌት አደጋ ጭንቅላቷ ውስጥ ደም ፈሶ በማንኛውም ጊዜ ልትሞት እንደምትችል ዶክተሮች ቢነግሯትም፥ አደጋው ከደረሰ ከስድስት ቀናት በኋላ የቫለሪያ እናት በብፁዕ ካርሎ አኩቲስ መቃብር ላይ ለልጇ ፈውስ ለመጸለይ ወደ አሲሲ ሄዳ በዚያው ቀን ቫለሪያ እንደገና በራሷ መተንፈስ እንደጀመረች እና እንደዳነች ቤተክርስቲያን ይፋ አድርጋለች።

የቅድስና ሳምንት መርሃ ግብር
የቅድስና ሳምንት አከባበር በተአምረኛው ቤተ ጸሎት ከሚደረጉ መርሃ ግብሮች ጋር እስከ ቅዳሜ ጳጉሜ 1 ድረስ የሚከበር ሲሆን፥ እሑድ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ብራዚል ውስጥ በሚገኘው ሳኦ ሴባስቲኦ ቁምስና የሚካሄደው የሢመተ ቅድስና ሥነ ሥርዓት በቫቲካን ከሚካሄደው እና በቀጥታ ስርጭት ከሚተላለፈው የሢመተ ቅድስና መርሃ ግብር ጋር በመቀናጀት የሚተላለፍ እንደሆነ ተገልጿል።

መርሃ ግብሮቹ እስከ 5፡30 ቀጥለው፣ በብራዚሏ ካፖ ግራንዴ ውስጥ በሚገኘው ‘ክለብ ኢስቶሪል’ በሚከናወን የምሳ ግብዣ ሥነ ስርዓት ይጠቃለላል ተብሏል።

ሚያዝያ 25 ቀን 1983 ዓ.ም. ለንደን ከተማ ተወልዶ ሚላን ውስጥ ያደገው ጣሊያናዊ ተማሪ ካርሎ አኩቲስ ለቅዱስ ቁርባን ባለው ልዩ ፍቅር እና ዲጂታል ሚዲያን በመጠቀም የካቶሊክ እምነትን ለማስተዋወቅ በሚያደርገው ትጋት የሚታወቅ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የቅዱስ ቁርባን ተአምራትን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም መገለጥን የሚዘግብ ድረ-ገጽ በመፍጠር በርካታ ሥራ እንደሰራ እና በደረሰበት የጤና እክል በአሥራ አምስት ዓመቱ ከዚህ ዓለም ድካም እንዳረፈ ይታወቃል።

05 Sep 2025, 15:50