ፈልግ

በሱዳን ኑባ ተራሮች ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙት የከበረ ደም ሚስዮናውያን እህቶች በሱዳን ኑባ ተራሮች ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙት የከበረ ደም ሚስዮናውያን እህቶች 

በሱዳን ኑባ ተራሮች ላይ ለሚገኙ ህዝቦች ተስፋን የሚያድሱ ሚስዮናውያን እህቶች አገልግሎት በርካታ መሆኑ ተነገረ

በሱዳን ኑባ ተራሮች አከባቢ በሃገሪቱ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኝ አከባቢ ቢሆንም፥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የከበረ ደም ሚስዮናውያን እህቶች ማህበር ለአገልግሎታቸው ታማኝ በመሆን፥ በትምህርት እና በጤና አጠባበቅ ዘርፎች ላይ ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶችን እየሰጡ የሚገኝ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ችግር ውስጥ በሚገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ በመስራት እና አልፎ ተርፎም ለክልላዊ የሴቶች ማዕከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኑባ ተራሮች እንዲሁም ‘የኑባ ኮረብታዎች’ ተብሎ የሚጠራው ይህ የሱዳን ግዛት በደቡባዊ የኮርዶፋን አውራጃ ውስጥ የሚገኝ አካባቢ ሲሆን፥ በዚህ ስፍራ የኑባ ብሄረሰቦች በመባል የሚታወቁት ነባር ተወላጆች የሚገኙበት ሥፍራ እንደሆነ እና እነዚህ ጎሳዎች በሰሜን ሱዳን ከሚገኙት ነባር ተወላጆች ከሆኑት ኑቢያውያን ጋር እንደሚለያዩ ይነገራል።

የከበረ ደም ሚስዮናውያን እህቶች አባል የሆኑት እህት ሜሪ ካሮላይን በአከባቢው ከሰባት ዓመታት በላይ የሱዳንን ሕዝብ ለማገልገል ሕይወታቸውን የሰጡ ሲሆን፥ በሃገሪቷ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት እና የደህንነት እጦት ምክንያት በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም፥ በዚህ ሃይማኖታዊ የህይወት ጉዞ ውስጥ ይህ ተልዕኮ ጥልቅ እርካታ እንደሚሰጣቸው እና አበረታች እንደሆነ ገልጸዋል።

“በሁሉም የሕይወት ደረጃዎች ውስጥ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ” ያሉት እህት ሜሪ ካሮላይን፥ ነገር ግን ከምንም በላይ ይህ አገልግሎት ብዙ እርካታ እንዳለው ገልጸው፥ የእነሱ አገልግሎት ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋር በመገኘታቸው እና እነሱን ማገልገል በመቻላቸው በጣም ደስተኞች እንደሆኑ አብራርተዋል።

የማህበሩ መስራች ህልም
እንደ ሲስተር ሜሪ ገለጻ ከሆነ፣ የጉባኤው በሱዳን መገኘት በአጋጣሚ ሳይሆን፥ የማህበራቸው መስራች የሆኑት አቦት ፍራንሲስ ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረው ህልም እውን መሆን እንደሆነ ጠቁመው፥ አቦት ፍራንሲስ ወንጌል እስከ ሱዳን ድረስ እንዲደርስ ህልም የነበራቸው እንደሆነ እና ይህ ተልዕኮ ዛሬም ድረስ የአገልግሎታቸው ማዕከል እንደሆነ አስረድተዋል።

የከበረ ደም ሚስዮናውያን እህቶች ማህበር ስማቸው እንደሚያመለክተው በዋናነት ክርስቶስን እና ወንጌሉን በማያውቁ ህዝቦች እና ሃገራት መካከል በመገኘት የወንጌል አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ገልጸው፥ የአከባቢው ቤተ ክርስቲያናት በማይደርሱበት አካባቢዎች ላይ በመንቀሳቀስ አገልግሎት እንደሚሰጡ እና አሁን በሱዳን እየሠሩ ያሉት ይህንኑ እንደሆነ ጠቁመው፥ ገዳማዊያቱ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ለዘመኑ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሚሞክሩ ብሎም በሁሉም ተግባራቶቻቸው እና ተልዕኮአቸው የእርቅ፣ የተስፋ እና የአዲስ ህይወት መሳሪያዎች መሆን እንደሚሹ አስረድተዋል።

ሃዋሪያዊ ሥራ የአገልግሎታቸው ማዕከል መሆኑ
ሲስተር ሜሪ ካሮላይን አገልግሎትታቸው በዋናነት ሃዋሪያዊ ሥራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ የእርሳቸው ሀላፊነቶች በርካታ እና የተለያዩ መሆናቸውን አስታውሰው፥ አከባቢው ላይ በሚገኙ ፍላጎቶች በመመስረት ህፃናትን፣ ጥንዶችን እና መላውን ማህበረሰብ ህይወት የሚነካ አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በአከባቢው በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የወጣት ካቶሊክ ተማሪዎች ህብረትን (YCS) እንቅስቃሴ እንደሚመሩ የገለጹት እህት ሜሪ፥ ለጋብቻ የሚዘጋጁ ጥንዶችን ማስተማርን ጨምሮ ህፃናትን እና ጎልማሶችን ለሚስጥረ ጥምቀት እና ለቅዱስ ቁርባን ለማብቃት ትምህርተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ከካቴኪስቶች ጋር በቅርበት በመስራት፣ ወርሃዊ የሥራ እቅዶችን በማዘጋጀት፣ የተለያዩ የአገልግሎት ማህበራትን በመደገፍ፣ እንዲሁም በወር አንድ ጊዜ ከሁሉም አውራጃዎች ለሚመጡ የማርያም ጠባቂዎች ማህበር አባላት የጸሎት ቀን በማዘጋጀት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

ዕለተ ሰንበትን ብዙ ጊዜ ራቅ ባሉ አከባቢዎች ከሚገኙ ክርስቲያኖች ጋር በመጸለይ እንዲሁም ድሆችን እና አረጋውያንን በመጠየቅ እንደሚያሳልፉ በማስታወስ፥ ከዚህም ባሻገር በሳምንት አራት ጊዜ በአቅራቢያው ባሉ መንደሮች ውስጥ ትናንሽ ክርስቲያን ማህበረሰቦችን (SCCs) እንደሚጎበኙ ጠቁመዋል።

“በገዳማችን ውስጥ ለልመና የሚመጡ በርካታ ድሆች አሉ” ያሉት ሲስተር ሜሪ፥ እነዚህን ድሆች የማገልገል ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ በየሶስት ወሩ በአከባቢው የሚገኙ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመሄድ የመመሪያ እና የምክር አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

ከዚህም በተረፈ የመዋዕለ ሕፃናት መምህር በመሆን የሚያገለግሉት ሲስተር ሜሪ፥ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ አሥራ ስድስት ዓመት የሚሆናቸው ትምህርት ቤት ገብተው የማያውቁ ህፃናት ልጆች ወደ ገዳሙ እንደሚመጡ እና እዚያ ውስጥም ማንበብና መጻፍ እንደሚያስተምሯቸው ገልጸዋል።

ተግዳሮቶች
ሚስዮናውያን እህቶች በኑባ ተራሮች ውስጥ የሚያሳልፉት ሕይወት በጣም ከባድ እንደሆነ እና ዕለታዊ መርሃ ግብሮቹም ጥብቅ እንደሆኑ የገለጹት ሲስተር ሜሪ ካሮላይን፥ መጀመሪያ ላይ በጠዋቱ ለማሰላሰል እና ለጸሎት ከእንቅልፋቸው እንደሚነቁ፣ የጋራ ጸሎት ካደረጉ በኋላ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እንደሚሳተፉ፣ ከቅዳሴ በኋላ ወደ ቁርስ እንደሚሄዱ፣ ከዚያም ሥራ የሚበዛበት ቀናቸውን እንደሚጀምሩ ገልጸው፥ ጠዋት ላይ አረጋውያንን ምግብ እና የተለያዩ አልባሳትን ይዘው እንደሚጎበኙ፣ በመቀጠልም የታመሙትን እንደሚጠይቁ አስታውሰው፥ ከሰዓት በኋላ በጣም ሞቃታማ ስለሚሆን ጠዋት ከሁሉም የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።

ሲስተር ሜሪ ከጉብኝት ከተመለሱ በኋላ ለቅዱስ ቁርባን የሚዘጋጁ ህፃናት ልጆችን በማስተማር የተወሰኑ ጊዜያት የሚያሳልፉ ሲሆን፥ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ ገዳማዊያቱ ከአነስተኛ ክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር ለመጸለይ ወደ መንደሮች ከመሄዳቸው በፊት ለጋራ ጸሎት እንደሚሰበሰቡ ገልጸዋል።

እምነት በችግር ውስጥ
ድህነት እና መገለል እንዲሁም በጣም አስቸጋሪው የአየር ንብረትን ጨምሮ በሱዳን ያሉ ፈተናዎች እጅግ በጣም ብዙ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፥ ሲስተር ሜሪ በአገልግሎታቸው ተስፋ የሚያደርጉ እና ቀናተኛ እንደሆኑ የገለጹ ሲሆን፥ ከህዝቡ ዘንድ መገኘት፣ በደስታቸው እና በተጋድሎአቸው ወቅት ከእነሱ ጋር መመላለስ የእውነተኛ የወንጌል ፍቅር መገለጫ መሆኑን በመጥቀስ፥ የእነሱን መስዋዕትነት መኖር በሚያገለግሉት እና በጸሎታቸው የፋሲካን ምስጢር ፍሬያማ ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

“እዚህ ያለን ሥራ ቀላል አይደለም” ያሉት ሲስተር ሜሪ፥ ነገር ግን ህይወታቸው ትርጉም ያለው መሆኑን እና ወደ ስፍራው የመጡት የመስራቻቸውን ህልም የነበረውን ወንጌልን እስከ ሱዳን ድረስ ለማዳረስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሲስተር ሜሪ ካሮላይን በመጨረሻም በኑባ ተራሮች ላይ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጦርነቶች እና ግጭቶች ባሉበት ጊዜም ቢሆን የገዳማዊያቱ እዛ መኖር ለህዝቡ ተስፋቸው ስለሆነ ከእነሱ ጋር መቆየት እንደነበረባቸው ገልጸው፥ “እኛ ወደ አገሮቻችን ለመመለስ ከወሰንን ከእነሱ ጋር ማን ይኖራል?” የሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ አጠቃለዋል።
 

15 Sep 2025, 13:59