በዓለማችን ወደ አምስት ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከባድ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት እንደሚደርስበት ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የፋውንዴሽኑ የ2025 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ ሪፖርት በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን የመድልዎ እና የስደት ሁኔታ ግልጽ ያደረገ ሲሆን፥ በ196 አገራት ላይ የተካሄደው የ2024 ዓ. ም. ሪፖርት፥ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 18 ላይ የተገለጸውን፥ “ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት አለው” የሚለውን መሠረት አድርጓል።
በዚህ መሠረት በቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ኢንስቲትዩት በተካሄደው ኮንፈረንስ የፋውንዲሽኑ አባላት ስደት እና አድልዎ እየደረሰባቸው ያሉ አገራትን በተመለከተ ከሁለት ዓመት በፊት በተሰበሰበው አሃዝ እና መረጃ ላይ ተወያይተዋል።
የስደት መበራከት
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት የዘንድሮው ሪፖርት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1999 መታተም ከጀመረ ወዲህ ትልቁ እንደ ሆነ ገልጸው፥ ይህም ቤተ ክርስቲያንን የሚያጋጥማት ስደት እያደገ መሄዱን ገልጸዋል። ሪፖርቱ 64.7% የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ወይም 5.4 ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከባድ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት ባለባቸው አገሮች ውስጥ እንደሚኖር ገልጿል።
የ2025 (እ.አ.አ) ዓ. ም. ሪፖርት ዋና አዘጋጅ ማርታ ፔትሮሲሎ፥ 24 አገራትን ስደት እንደሚደርስባቸው እና 38ቱ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ መድልዎ እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል። በበርካታ ሀገራት ውስጥ የእምነት ነፃነት በሕግ እንደማይረጋገጥ እና ሌሎችም “ሁሉም ሰው እኩል ነው” የሚል ነገር ግን በተግባር የማይገለጽ ሕግ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
የጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ዘገባን ልዩ የሚያደርገው የክርስቲያን ሃይማኖቶች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በመመልከት ሆን ተብሎ ዓለም አቀፋዊ አካሄድ መያዙ እንደሆነ ታውቋል። ፔትሮሲሎ ይህ ዘገባ በዓለም ላይ ከመንግሥት ጋር ያልተገናኘ ብቸኛው እንደሆነ አስረድተዋል። ሪፖርቱ በእውነቱ ዓለም አቀፋዊ እይታ እንዲኖረው በሚያስችለው ጥቂት አገሮች ብቻ የተገደበ አለመሆኑ ታውቋል።
የሃይማኖት ነፃነት አስፈላጊ ነው
ችግሮች ባሉባቸው አገራት ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ኢንተርናሽናል ፕሬዚደንት ሬጂና ሊንች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መስከረም 30/2018 ዓ. ም. ለድርጅቱ አባላት ባሰሙት ንግግር፥ “የሃይማኖት ነፃነት በመንግሥታት የተሰጠን ልዩ ሕጋዊ መብት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ እርቅ እንዲኖር የሚያደርግ መሠረታዊ ሁኔታ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ፕሬዝደንት ሬጂና ሊንች በመቀጠልም፥ እንደ ሕሊና የመኖር መብት የሰብዓዊ ክብር ትልቁ አካል እንደሆነ ገልጸው፥ ሰብዓዊ ክብር በተከበረበት ቦታ ሰላም እና ፍትህ እንደሚያብብ ነገር ግን ይህ በተከለከለበት ቦታ የሰው መንፈስ እና ኅብረተሰብ መሠረታቸውን እንደሚያጡ አስረድተዋል።
የተለያዩ ቅርጾችን መያዝ
በጉባኤው ወቅት ፔትሮሲሎ እንደተናገሩት፥ እንደ የሀገሩ የሚለያዩ የሃይማኖት ስደት መንስኤዎች አምባገነን መንግሥታትን፣ አክራሪነትን፣ ብሔርተኝነትን፣ የተደራጁ ወንጀሎችን እና አለመቻቻልን ሕጋዊ እንደሚያደርጉቸው ገልጸዋል። ከዚህም በላይ ጦርነቱ ሃይማኖታዊ ነው ባይባልም ሃይማኖታዊ ስደት በጦርነት ምክንያት ሊታይ እንደሚችል ገልጸው፥ ለዚህም ዩክሬንን፣ ጋዛን እና ሶርያን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።
በዲጂታል ዘመን ስደት እና መድልዎ በአውታረ መረብ ላይም ሊደርስ እንደሚችል የገለጹት ፔትሮሲሎ፥ አማኞች በአውታረ መረብ በኩል በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ክትትል እንደሚደረግባቸው እና አልፎ ተርፎም እንደሚታሰሩ ተናግረዋል። ፔትሮሲሎ በማከልም “ባለስልጣናት እና ጽንፈኛ ቡድኖች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተቃዋሚዎቻቸውን ዝም ለማሰኘት እና አናሳዎችን ዒላማ እንደሚያደርግጓቸው አስረድተዋል።
ለውጥን ለማምጣት አቤቱታ ማቅረብ
ፕሬዚደንት ሬጂና ሊንች በሪፖርቱ መጨረሻ ላይ ሁሉም ሰው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽንን በመቀላቀል ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበውን ዓለም አቀፍ አቤቱታ እንዲፈርሙ በመጋበዝ የሰዎችን የእምነት ነፃነት መብት ለማስጠበቅ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። አቤቱታው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እስከ ህዳር 2026 ድረስ እንዲፈረም ተዘጋጅቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የዲሞክራሲያዊ መንግሥታት ተወካዮች እና የዲፕሎማሲው ማኅበረሰቡ ንቅናቄውን እንዲቀላቀሉ ለማበረታታት በይፋ የሚቀርብ ይሆናል።