ፈልግ

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ የሆነችው የቅዱስ ፍራንቺስኮ ታናናሽ እህቶች አባል እህት ኢማኩሌት ሙቶኒ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ የሆነችው የቅዱስ ፍራንቺስኮ ታናናሽ እህቶች አባል እህት ኢማኩሌት ሙቶኒ  

አንዲት ካቶሊካዊት ሲስተር ባልተለመደ ሁኔታ በኬንያ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ፍትህን እያስጠበቀች እንደምትገኝ ተነገረ

በርካታ ሰዎች ስለ አንዲት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወጣት እህት ሲያስቡ በአዕምሮአቸው ቀድሞ የሚመጣው በተለመደው መልኩ ምናልባትም ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ስታስተምር፣ በጸጥታ ጸሎት ቤት ውስጥ ስትጸልይ ወይም የታመሙትን ስትንከባከብ ሊሆን ይችላል፥ ነገር ግን በኬንያ አንዲት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እህት በፍርድ ቤት አዳራሽ ውስጥ የህግ ባለሙያ ልብስ ለብሳ፣ በዳኛ ፊት ቆማ እና እራሷን ስታስተዋውቅ በዋና ስሟ ብቻ “ጠበቃ ኢማኩሌት ማቶኒ” ብላ ሳይሆን፥ “ሲስተር ኢማኩሌት” ብላ ስታስተዋውቅ ማየት በሃገሪቷ ውስጥ የተለመደ አልነበረም።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅዱስ ፍራንቺስኮ ታናናሽ እህቶች አባል የሆነችው እህት ኢማኩሌት ሙቶኒ፣ መነኩሴ ብቻ ሳትሆን የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ፣ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የህግ ባለሙያ፣ በብሄራዊ ማሰልጠኛ ባለስልጣን እውቅና ያላት አሰልጣኝ እና በኬንያ የህግ ማህበር እውቅና ያገኘች የህግ ኦዲተር ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

ከማዕረግም ባሻገር በእርግጥም የሰብዓዊ ክብር ተሟጋች እና የተስፋ ምስክር የሆነችው ሲስተሯ፥ የፍትህ ወንጌል በመሠዊያው ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን በፍርድ ቤቶች ውስጥም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል በተግባር እያሳየች የምትገኝ እህት መሆኗ ተነግሯል።

በሥራዋ ወቅት የተረጋጋ፣ ጠንካራ እና ብሩህ የሆነ ምስል የምታቀርብ ሲሆን፥ ይህም ብዙዎቹ ሃይማኖታዊ ሕይወት እና የሕግ ልምምድን አብረው ሊሄዱ አይችሉም ብለው የሚያስቡትን ሁለት ዓለማት በማገናኘት አስመስክራለች።

በጥሪ ውስጥ የተደረገ ጥሪ
የሲስተሯ ታሪክ የሚጀምረው በህግ ሳይሆን ወጣት የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ለመሆን በማሰብ ቢሆንም፥ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ምስረታ እና ደንቦች የህይወት መንገዷን ቀይረዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ ከፓርቲያዊ ጦርነቶች ጋር በጣም የተሳሰረ እንደሆነ ሲነገራት ያደገችው ሲስተሯ፥ የሕግ ሙያ ግን ከልጅነቷ ጀምሮ ለመሆን የምትፈልገውን ሃይማኖታዊ ጥሪ ሳያበላሽ ፍትህን ማስከበር የሚቻልበትን መንገድ ማቅረቡን ተረድታለች።

እህት ኢማኩሌት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ “ሕግ ትንሹ መጥፎ ነገር ነው ብዬ አስብ ነበር፥ ሆኖም እስከ ዛሬ ድረስ ጠበቃ በመሆኔ አልቆጨኝም” በማለት አስታውሳለች።

ለእህት ኢማኩሌት ሕግ እና ሃይማኖታዊ ሕይወት የተለያዩ ጥሪዎች ሳይሆኑ የአንድ ተልዕኮ ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የገለጸች ሲሆን፥ ሃይማኖታዊ ሕይወት በጸሎት፣ በጽናት እና በርኅራኄ እንድትታነጽ የሚረዳት፥ ህጉ ደግሞ በእነዚያ እሴቶች ላይ እንድትሰራ መድረክ እንደሚያመቻችላት እና አንድ ላይ ሆነው እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት እርስ በርሳቸው እንደሚደጋገፉ እንደሆነ አስረድታለች።

ፍትህ በሰው ፊት
እሷ የምታስተናግደው እያንዳንዱ ጉዳይ ከህጋዊ ክብደት በላይ እንደሆነ እና የሰው ልጅን ነፍስ ጉዳይ የያዙ፣ አንዳንዴ በነገሮች ልባቸው የተሰበረ ሰዎች ጉዳይ፣ ብዙ ጊዜ ተሰሚነት ያጡ እና ከሁሉም በላይ ሰብዓዊ ክብርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንደሆነ አስረድታለች።

“ጉዳዩን ስለማሸነፍ ወይም ስለመሸነፍ አይደለም” ያለችው ሲስተሯ፥ ከሰዎች ጋር፣ ከተሸነፉትም ጭምር ስለመጓዝ እና ፍትህ ሁሌ የሚሳካም ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ መሸነፍም እንዳለ ለማረጋገጥ መሆኑን ገልፃለች።

ከዚህም ባለፈ እምነቷ ልምምዷን እንደሚቀርጽ ገልፃ፥ ሌሎች የአሰራር ሂደቱ ላይ በሚያተኩሩበት ቦታ እሷ ርህራሄን እንደምታስቀድም፣ ሌሎች ግጭትን የሚያዩበት ዓይን ውይይትን እንደምታስቀድም እና ሌሎች ሽንፈትን በሚያዩበት ዓይን እሷ ተስፋን እንደምታይ አብራርታለች።

በፍትሕ እጦት መከራ የደረሰባት እና የሕግ ሥርዓቱን በመፍራት ሸሽታ የነበረች አንዲት ሴት መነኩሴ በመሆኗ እንደቀረበቻት እና ፍትህ እና ፈውስ እስክታገኝ ድረስ በህጋዊ ሂደት በነፃ እስከመጨረሻ የተጓዘችበትን ወቅት በማስታወስ ገልፃለች።

የተለመዱ አመለካከቶችን መቀየር
ድርብ ሚናዋ በሰዎች ዘንድ ጥርጣሬ የተሞላበት እንደነበር የገለጸችው እህት ኢማኩሌት፥ በፍርድ ቤት ውስጥ ያሉ አንዳንድ የሥራ ባልደረቦች ለህጋዊ ክርክሮች "በጣም ለስለስ ያለ አቀራረብ" በማለት ውድቅ ሲያደርጉባት እንደነበር አስታውሳ፥ በሃይማኖት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም አንዲት መነኩሲት ለምን 'በዓለማዊ ሥራ ትዘፈቃለች' ብለው ቢያስቡም፥ ነገር ግን ውጤቷና አቋሟ እንዲናገር በማድረግ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ማድረጓን ገልፃለች።

ሰዎች በአንድ ጊዜ መነኩሴ እና ጠበቃ መሆን ጥልቅ እና ተአማኒነትን እንደሚያመጣ መገንዘብ መጀመራቸው “አንዲት የእምነት ሴት በሙያዊ ቦታዎች ውስጥ ልታበረክተው የምትችለውን በፊት የነበረ የተሳሳተ አመለካከት ይቀይራል” በማለት ገልፃለች።

“በፍርድ ቤት ውስጥ 'እህት ኢማኩሌት፣ ለደንበኞቿ የቆመች’ ብዬ ራሴን ሳስተዋውቅ፣ ከስሜ በፊት ያለው መጠሪያዬ ብዙ ጊዜ ተቃዋሚዎችን ያስደነግጣል፥ ውጥረቱንም ያቀልላል፣ ለውይይት እና ከፍርድ ቤት ውጪ በሽምግልና ጉዳዩን ለመፍታት ሁኔታዎችን ያመቻቻል” በማለት ተናግራለች።

ከሚያጋጥሟት ተግዳሮቶች ውስጥ ዋናው ወደ ፍርድ ቤት ሥርዓት በሄደች ቁጥር ዳኞች መነኮሳትን እንደ ጠበቃ የማየት ልምድ ስለሌላቸው፥ ጠበቃ መሆኗን እርግጠኛ እንደሆነች እና የተግባር ሰርተፍኬት ቁጥሯን እንደሚጠይቋት አስታውሳለች።

አዲስ ዓይነት የወንጌል ስርጭት
እህት ኢማኩሌት በአፍሪካ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጸጥ ያለው የለውጥ አብዮት አካል ስትሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና በርካታ የሃይማኖታዊ ተቋማት መስራቾች ለረጅም ጊዜ ያሳሰቡትን ማለትም "የዘመኑን ምልክቶች" ለመገንዘብ እንዲሁም እግዚአብሔርን እና የሰው ልጆችን የማገልገል አዳዲስ መንገዶችን መቀበልን እንደሚያካትት ገልፃለች።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ገዳማዊያት እና ገዳማዊያን በአንድ ወቅት መስራቾቻቸው እንዳደረጉት የዘመኑን ምልክቶች በትህትና እንዲከታተሉ ያበረታቱ ሲሆን፥ "መስራቾቻችሁ አስተዋይ፣ ገምጋሚ እና አፍቃሪ ነበሩ፥ በታላቅ ስቃይ እና ውድቀት ስጋት ውስጥ እንኳን ቢሆን በጎረቤቶቻቸው ድህነት ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምጽ በመገንዘብ የሌሎችን እውነተኛ ፍላጎት ለማገልገል ወጡ” ማለታቸው ይታወሳል።

“ወንጌልን መስበክ በስብከት ብቻ አይደለም” ያለችው ሲስተር ኢማኩሌት፥ “ከስብከትም በተጨማሪ የወንጌል እሴቶች በሆኑት በፍትሕ፣ በርኅራኄ እና በአቋም ጽናት በመኖር ወንጌልን ማስፋፋት ይቻላል” ብላለች።

ከዚህም ባሻገር በሕግም ይሁን በመገናኛ ብዙኃን ወይም በማንኛውም ዘርፍ ሃይማኖታዊ ሴቶች በሙያቸው እምነታቸውን እንዲያንጸባርቁ ማድረግ እንደሚችሉ እና ማድረግ እንዳለባቸውም ጭምር አሳስባለች።

ህልሟ ብዙ እህቶችን በአንድ ወቅት “ዓለማዊ” ተደርገው በተወሰዱት በሕግ፣ በአስተዳደር እና በሙያ ቦታዎች ሲያገለግሉ ማየት እንደሆነ እና በአፍሪካ ያለው የገዳማዊያን ሕይወት አሮጌውን ድንበር ጥሶ የፍትህ ሥርዓቶችን በወንጌል መንፈስ ሲቀርጽ ማየት እንደሆነ ያላትን ተስፋ ገልፃ፥ “በፖሊሲዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር እና ማህበረሰቦችን በሰፊው ለማጎልበት የህግ ትምህርቴን እንደማሻሽል ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች።

ለዘመናችን ምስክር
የሲስተር ኢማኩሌት ህይወት ገዳማዊያት ሴቶች በድፍረት ወደ ፍትህ ቦታዎች ሲገቡ ቤተክርስቲያን ሕያው፣ አዲስ ነገር ፈጣሪ እና ትንቢታዊ መሆኗን የሚያስታውስ ነው።

የመቁጠሪያ ዶቃዎቿን እና ህግ-ነክ መጽሃፎቿን ስትይዝ፣ በፍርድ ቤቱ እና በቤተ መቅደሱ መተላለፊያዎች ላይ በመነኮሳት ልብስ እና በጠበቃ ልብስ ስትመላለስ እምነት እና አመንክዮ መስማማት እንደሚችሉ ታሳያለች።
ተልዕኮዋ፥ እሷም ነቢዩ ሚክያስን ጠቅሳ እንደምትናገረው ሁሉ፥ “በጽድቅ መኖር፣ ምሕረትን መውደድ እና ከእግዚአብሔር ጋር በትሕትና መጓዝ” እንደሆነ አስረድታለች።

24 Oct 2025, 13:23