ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ለሰላም አዲስ ቋንቋ እና አዲስ ምስክርነቶች ያስፈልጋሉ” ሲሉ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“በቅድስት ሀገር ዘላቂ ሰላምን የማምጣት ተስፋ፣ በጋዛ እና በዌስት ባንክ ያሉ ችግሮች ሕዝቦችን በሰብዓዊ ክብር ስም እንዲሰባሰቡ ያደረጉ ሕዝባዊ ሰልፎች ስሜት የሚሉት፥ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ረቡዕ ጥቅምት 5/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ሬዲዮ ጣቢያ በእንግድነት ተገኝተው ካነሷቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ብፁዕነታቸው ተግባራዊነቱ አስተማማኝ ስላልሆነው የተኩስ አቁም ስምምነት ይናገሩ እንጂ በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መካከል ያለውን የጋራ ተስፋ በመጥቀስ፥ “ስምምነቱ የመሣሪያ ተኩስን ለአፍታ የሚስያቆም ብቻ ሳይሆን ጦርነት እና ሁከት ቆሞ ሕይወት በአዲስ መልክ እንዲቀጥል ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል።
በጋዛ ከሚገኝ የቅዱስት ቤተሰብ ቁምስና ምዕመናን ጋር በየጊዜው እንደሚገናኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ሌሊቱን በሙሉ የቦምብ ድምጽ ሳይሰሙ ማደራቸውን ማመን እንዳቃታቸው መጻፋቸውን ገልጸዋል። “የሰው አልባ አውሮፕላኖች እንቅስቃሴ ቢኖርም ለዓመታት ሲመለከቱት መቆየታቸውን እና በተለያዩ ወገኖች መካከል ግጭቶች መኖራቸው ቢስተዋልም ሁኔታው እጅግ የተረጋጋ ነው” በማለት አስረድተዋል። “ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ስለመጠናቀቁ እስካሁን እርግጠኞች አይደለንም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ከዚህ በኋላ ያሉት ነገሮች ያልተረጋገጡ እና አሻሚዎች እንደሆኑ፣ አሁንም ብዙ ውጣ ውረዶች መኖራቸውን፣ መኖሪያዎቻቸው ቢፈርሱም ቤተሰቦች ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን፣ ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን፣ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን እና ሁሉም ነገር እንደገና መገንባት እና መደራጀት እንዳለበት አስረድተዋል። የሟች እስራኤላውያን ታጋቾች አስከሬን የመመለስ ጉዳይን በተመለከተ በተፈጠረው ትርምስ እነዚህ አካላት የሚገኙበት ቦታ በመጥፋቱ አስከሬኖችን ማግኘት ቀላል አለመሆኑን ተናግረው፥ በተፋላሚዎች መካከል ያለው አለመተማመን አሁንም ከፍተኛ እንደሆነ እና የተኩስ አቁሙ ስምምነት አስተማማኝ ባይሆንም ነገር ግን ሁኔታው የተረጋጋ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በዚህ ታሪካዊ እና ስሜታዊ ሁኔታ ውስጥ ተስፋን እና ወንድማማችነትን መገንባት ጊዜ ሊወስድ የሚቻል መሆኑን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ተስፋን ከግጭቱ መፍትሄ ጋር ማደናገር እንደማይገባ እና በሽምግልና የሚገኝ አለመሆኑን ገልጸው፥ የጦርነቱ መቆም የሰላም መጀመሪያ እና የግጭቱ መጨረሻ አለመሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ገጽታዎች በሙሉ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው እና የተደረሰው ስምምነት የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ተስፋ የእምነት ፍሬ መሆኑን ልብ የሚያምን ከሆነ የሚያምነውን ነገር እውን እንደሚደርግ ገልጸው፥ በመሆኑም በቅድሚያ በዚህ ላይ መሥራት አለብን ብለዋል። ይህንን መረብ ለመፍጠር አሁንም በዚህ ሂደት መሳተፍ ከሚፈልጉት ጋር፥ በጋዛ ውስጥም ሆነ ከጋዛ ውጭ ከሚገኙት ጋር መተባበር እንደሚገባ እና ድንበር ያለያያቸውን ሁለት ወገኖች ሳይዘነጉ ወንድማማችነትን መገንባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። “አዲስ የፖለቲካ አመራር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ይህ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር መገናኘት መጀመራቸውን ተናግረው፥ “በእርስ በርስ መከባበር ላይ የተመሠረተ አዲስ ታሪክን እንደገና ለመገንባት የሚያግዙ አዳዲስ አመራሮች ያስፈልጉናል” ብለዋል። ጦርነቱ የፈጠራቸው ቁስሎች ጥልቅ በመሆናቸው ፈውሱ ብዙ ጊዜን ሊወስድ ቢችልም ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ አሳስበው፥ “በአሁኑ ጊዜ በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ ብንገኝም ዘላቂ ሰላምን የመገንባት ተስፋ አሁንም አለ” ሲሉ አስረድተዋል። በተዋዋይ ወገኖች መካከል መተማመን ባለመኖሩ ምክንያት ያልተደረሱ ስምምነቶችን ማስታወስ እንደሚገባ ተናግረው፥ መጪው ትውልድ የዛሬው ትውልድ ያላገኘውን ነፃነት እንደሚያገኝ በማሰብ የዛሬው ትውልድ ተግባርም ቀጣዩን ትውልድ ማዘጋጀት እንደሆነ አስረድተዋል። መሠረቱን እና ሁኔታዎችን ቀስ በቀስ በአዲስ መልክ እና በአዲስ አመራር በመገንባት ከምንም በላይ የመከባበር ባህልን የሚያጎለብቱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።
በየዕለቱ በኢየሩሳሌምም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚያገኟቸው ሰዎች የሚፈልጉት ተጨባጭ ተስፋን እንደሆነ የተጠየቁት የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳ ባላ ለሬዲዮ ጣቢያው ሲመልሱ፥ በአዲስ እና ደካማ ምዕራፍ ላይ ሁለት ዓመታትን ከስቆጠረው አስከፊ ጦርነት በመውጣት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ተስፋው እነዚያ ዓመታት ወደ መጨረሻ የደረሱበት ጊዜያዊ ዕረፍት ብቻ ሳይሆን እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን በቀኝም ሆነ በግራ የሚገኙ ሰዎች የሚጋሩት እንደሆነ አስረድተው፥ ሁሉም ሰው ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገርን እንደሚፈልግ፥ ፖለቲካዊ ሆነ ሃይማኖታዊ አስተያየቶች እና አመለካከቶች የተለያዩ ቢሆኑም በተራው ሕዝብ መካከል ጦርነት እና ብጥብጥ በሌለበት አዲስ አመለካከት ኑሮን እንደገና ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ብጹዕነታቸው አስረድተዋል።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በሃማስ ታግተው የነበሩ እና አሁን ነፃ የወጡ እስራኤላውያን የሚሰጡት አስገራሚ ምስክርነቶችን እና በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ በነበሩ ፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ ይደርስ የነበረውን ውርደት የሚገልጹ ዘገባዎችን በማስመልከት ሲናገሩ፥ ይህ በዚህ ወቅት ከተከሰቱት ታላላቅ አደጋዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጸው፥ እያንዳንዱ ወገን የራሱን ሕዝብ ስቃይ ብቻ እያየ በራሱ ህመም ውስጥ ተዘግቶ እንደሚገኝ አስረድተዋል። “አሁን ይህ ሁኔታ አብቅቷል” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ “ምናልባት ቀስ በቀስ የሌላውን ህመም ለመረዳት እራሳችንን መክፈት እንችል ይሆናል” ብለው፥ የሌላውን ሕመም መረዳት ማለት ማረጋገጥ ማለት እንዳልሆነ፣ ለማረጋገጥም ቢሆን ጊዜን እንደሚወስድ እና ሙሉ በሙሉ ይሳካ እንደሆነ አላውቅም ብለዋል። የተዘራው ጥላቻ በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከረጅም ጊዜ በፊት የጀምረ እንደሆነ ገልጸው፥ “በንቀት እና በማግለል የጀመረ በመሆኑ አዲስ ቋንቋን፣ አዲስ ቃላትን እና አዲስ ምስክርነቶችን የሚጠይቅ በመሆኑ ለየት ባለ መንገድ እንድናስብ የሚያግዙን አዳዲስ አመራሮች ያስፈልጉናል” ብለዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ በዌስት ባንክ ያሉ ቁምስናዎች እና ትናንሽ መንደሮች ሁኔታ እና ከእስራኤል ማኅበረሰብ ጋር ሙሉ በሙሉ የተዋሃዱ ዕብራይስጥኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች እና ካቶሊክ ምዕመናን ሚና ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ እነዚህ ሁለት በጣም የተለያዩ ሁኔታዎች እንደሆኑ ገልጸው፥ በዌስት ባንክ በሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ብቻ ሳይሆን ሁኔታው በአጠቃላይ እጅግ ደካማ እና በቀጣይነት እየተበላሸ የሚገኝ እንደሆነ ገልጸው፥ የመንደሮቹ ማኅበረሰቦች እርስ በርሳቸው የተገለሉ፣ የውስጥ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍተሻ ኬላዎች መኖራቸው ሁኔታውን የበለጠ አስቸጋሪ ማድረጉን አስረድተዋል። “ቦታው በሕገወጥ መንገድ የተያዘ አካባቢ በመሆኑ ሕግ የለሽ ግዛት ነው” ብለው፥ በአካባቢው ብዙ ጥቃቶች እና ውጥረቶች እንደሚታዩ ገልጸው፥ እነዚህን ሁኔታዎች ለማስቆም ይግባኝ የሚባልበት የባለ ስልጣን መሥሪያ ቤት አለመኖሩ በቁምስናዎቻችን እና በማኅበረሰቦች ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት እና ስጋት መፍጠሩን አስረድተዋል። በዌስት ባንክ ሁኔታው አሳሳቢ እነደሆነ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ በፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ረገድ ጭምር እንደሆነ ገልጸው፥ ሁለቱ ዋና ግብአቶች ማለትም ለሥራ እና ለመንፈሳዊ ንግደት ወደ እስራኤል መጓዝ አሁን መታገዱን አስረድተዋል። ይህ መቼ እና እንዴት ወደ መደበኛው ሁኔታ እንደሚመለስ የሚያቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ይህ ሁኔታ በሰዎች ሕይወት በተለይም በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸው፥ ዕብራይስጥኛ ተናጋሪው የካቶሊክ ማኅበረሰብ ጥቂት መቶ የሚሆኑ ሰዎችን ያቀፈ እንደሆነ እና እነዚህም ወደ እስራኤል የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወይም የውጭ አገር ሠራተኞችን ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ አስረድተዋል። ሚናቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ በተወሰነ መልኩ በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን ሀገረ ስብከታቸውን በሰፊው እንዲያስብ ማስገደዱን፥ በፍልስጤም ጥያቄ ላይ ብቻ ማትኮር ሳይሆን በእስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥም ሕመም መኖሩን በማስታወስ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው አመለካከቶች እና ራእዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጣሊያንን ጨምሮ ሚሊዮኖች ወደ ጎዳና የወጡበት ሕዝባዊ ንቅናቄ እና ሰልፎች፣ ከአክራሪ ቡድኖች እና ተቀባይነት ከሌላቸው ጥቂት መፈክሮች በተጨማሪ ከግዴለሽነት አመክንዮ መውጣት የሚፈልጉ ወጣቶች መኖራቸውን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ሰልፎቹ በርግጠጥ ከመጠን ያለፈ አመጽ የታዩባቸው እና በአይሁዶች ላይ ያለው ጥላቻ እና ፀረ ሴማዊነትን ሊያጸድቁ የሚችሉ መንገዶች የታዩባቸው በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል። “የሰልፉ ተሳታፊዎች በሙሉ ተመሳሳይ አቋም አላቸው” ብሎ መደምደም እንደማይቻል ተናግረው፥ ተሳታፊዎቹ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ የአመፅ ምስሎችን የተቃወሙት ከተለያዩ አስተዳደግ፣ ትውልዶች እና የፖለቲካ አመለካከቶች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ነበሩ አስረድተዋል። የተለያዩ የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች በማኅበረሰቡ ህሊና ውስጥ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ጥሩ ነገር እንዳለ እንዲገነዘቡ እና ምናልባትም ከዚህ ጦርነት አውድ ባሻገር ሌሎች አገላለጾችንም ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።
ወደ ቅድስት ሀገር የሚደረግ መንፈሳዊ ንግደት ይጀምር እንደሆነ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳ ባላ፥ ነጋዲያኑ ወደ ቅድስት አገር መምጣት እንደሚጀምሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህን አስመልክቶ በኅብረት ሆነው አንድ ነገር ለማድረግ ምናልባትም አንዳንድ መግለጫዎችን ለማውጣት ከቅድስት ሀገር መጋቢ ካኅን ጋር መነጋገራቸውን ተናግረዋል። ከሁለት ወይም ሦስት ሳምንታት በኋላ ነገሮች ምን እንደሚመስሉ ለማወቅ መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረው፥ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከቅድስት ሀገር ጋር ተባባሪ ከነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በጸሎት ብቻ ሳይሆን በዕርዳታም ሆነ በመንፈሳዊ ንግደት ጭምር አጋርነትን የምናሳይበት ጊዜ አሁን እንደሆነ አስረድተዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳ ባላ፥ የሰላም ሰው የነበሩት ይስሐቅ ራቢን የተገደሉበት 30ኛ ዓመት መታሰቢያ ጋር ራሳቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ አዲስ መሪዎች የመኖር አስፈላጊነትን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ይህ ከወሳኝ ገጽታዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጸው፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከምንሰማው በተለየ አዲስ ርዕሠ ጉዳይ የሚናገሩ አዳዲስ የፖለቲካ መሪዎች እንደሚያስፈልጉ፥ የፖለቲካ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት መሪዎችም እንደሚያስፈልጓቸው ተናግረዋል። ከሠላሳ ዓመት በፊት የሰላም ሰው የነበሩት ይስሐቅ ራቢን አንድ ነገር ሲናገሩ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ በተቃራኒ ሌላ ነገር ይናገሩ እንደ ነበር ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ በዚህ አውድ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ውይይቶችን ለማካሄድ አዳዲስ የሃይማኖት መሪዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፥ የተፈጠረው ችግር ሁሉንም ያቆሰለ በመሆኑ ችላ ሊባል እንደማይገባ አሳስበዋል። ችግሮቹ ብዙ ስለሆኑ ማኅበረሰቦች አዎንታዊ እና የተረጋጋ ስሜት እንዲኖራቸው ወደ ሌላ የወደፊት አቅጣጫ እንዲዞሩ የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ በፍልስጤም መንግሥት እውቅና ላይ የሚደረግ ዓለም አቀፍ ውይይትን በማስመልከት ሲናገሩ፥ በፍልስጤም ጦርነት እና ብጥብጥ እንዲያበቃ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ፖለቲካዊ ወደ ሆኑ ጥያቄዎች ውስጥ መግባት ባይፈልጉም ነገር ግን የፍልስጤም ሕዝብ እንደ ሕዝብ እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረው፥ “ሁለት ሕዝቦች እና ሁለት ግዛቶች” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሳካ እንደሚችል እርግጠኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን ፍልስጤማውያን በገዛ ምድራቸው እንደ ሕዝብ የመታወቅ መብታቸውን ማግኘት እንደሌለባቸው መናገር የሚችል ሰው የለም ብለዋል። በተዋዋይ ወገኖች መካከል በሚደረገው ውይይት ውስጥ ተጨባጭ ግንዛቤን ማግኘት የሚገባቸው ብዙውን ጊዜ በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ብቻ የሚወጡ መግለጫዎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታ እና ድጋፍ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሁለት ዓመታት ጦርነት ወቅት ለተጎጂዎች ያላቸውን ቅርበት በማስመልከት እንደተናገሩ፥ ቀደም ሲል የነፍስሔ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚያም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቅርበት በግልጽ ይታይ እንደ ነበር አስረድተዋል። ሁለቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተለያዩ ስብዕናዎች ያሏቸው ቢሆንም ከጋዛ የቅድስት ቤተሰብ ቁምስና መሪ ካኅን ጋር በተደጋጋሚ በስልክ በመገናኘት ቅርበታቸውን በተጨባጭ መንገድ መግለጻቸውን አስታውሰዋል። ይህ መቀራረብ ዕርዳታን ወደ አካባቢው በመላክ በተጨባጭ የተገለጸ መሆኑን አስታውሰው፥ በቅርብ ጊዜው ዕርዳታ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከጥቂት ቀናት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ አንቲባዮቲኮችን ወደ ጋዛ ሰርጥ ለመላክ መፈለጋቸውን ገልጸዋል።