የቤተክርስቲያን መሪዎች በስደት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ መሰብሰባቸው ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ባለፈው ሳምንት ከተከበረው የቫቲካን የስደተኞች ኢዮቤልዩ በኋላ ‘የካቶሊክ የነገረ መለኮት ሥነ ምግባር በዓለም ቤተክርስቲያን’ (CTEWC) አባላት እና ‘ዩኒቨርሲዳድ ኢቤሮአሜሪካና’ ወይም ‘ኢቤሮ’ ተብሎ ከሚታወቀው የሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “በሜክሲኮ እና በዩናይትድ ስቴትስ አዲስ የፖለቲካ አድማስ ውስጥ የሰው ልጅ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ ፈተናዎች ከክርስቲያናዊ እይታ አንጻር” በሚል ርዕስ በስደት እና ሥነ-መለኮት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረክ መካሄዱ ተነግሯል።
‘የካቶሊክ የነገረ መለኮት ሥነ ምግባር በዓለም ቤተክርስቲያን’ ማህበር አባል እና የቦስተን ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊው የሥነ መለኮት ምሁር ክሪስቲን ሄየር ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት ከውይይት መድረኩ ዋና ዓላማዎች አንዱ ለዓለም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በአጠቃላይ ለህብረተሰቡ ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት ሰብአዊ እርዳታን እና መስተንግዶን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፥ ጨካኝ ድርጊቶችን እና ኢሰብአዊ ፖሊሲዎችን ከሚያመለክቱ ኢፍትሃዊ ድርጊቶች ነፃ መውጣትን እንደሚጠይቅ ለማሳሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 1 ድረስ የተካሄደው ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ 40 ብፁዓን ጳጳሳትን፣ ምሁራንን፣ በጎ አድራጊዎችን እና የሃዋሪያዊ ሥራ አገልጋዮችን ከድንበር ከተሞች ውስጥ አንዷ በሆነችው፣ ብሎም የአሜሪካ እና የሜክሲኮ ማህበራዊ እውነታዎች እና ባህሎች ከሚገናኙባት፥ ነገር ግን በብረት አጥር ወይም ግድግዳ ሃገራቱ የተከፋፈሉባት የሜክሲኮ ከተማ ቲጁአና ውስጥ አንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ ይህቺ ከተማ በአሁኑ ወቅት በጠንካራ ፀረ-ስደተኛ እና ፖለቲካዊ ትርክቶች እንደተሞላች ይነገራል።
በቲጁአና የኢቤሮ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር የሆኑት ፍሎሬንቲኖ ባዲያል፣ ድንበር ገደብ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ የግንኙነት፣ የርህራሄ እና የተልዕኮ ቦታ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፥ የላቲን አሜሪካ የጳጳሳዊ ኮሚሽን ፀሐፊ የሆኑት ኤሚልስ ኩዳ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ አንድ ሦስተኛው ራሳቸውን እንደ ስደተኞች በሚያዩት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት ‘ስደተኛ ብፁዓን ጳጳሳት እና የነገረ መለኮት ሊቃውንት ከራሳቸው የግል ልምድ በመነሳት እንደ መነሻ ስነ-መለኮትን የሚተገብሩ እንደሆነ እና እውነታዎች ከሀሳቦች እንደሚበልጡ በድጋሚ አረጋግጠውልናል’ ብለዋል።
በ 19 ዓመታቸው ከትውልድ ሃገራቸው ሸሽተው ወደ አሜሪካ የገቡት እና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ረዳት ጳጳስ ኤቭሊዮ መንጂቫር በበኩላቸው “ይህ የድንበር አጥር ህልሜን አላቆመም” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሜክሲኮ፣ ጓዳላጃራ ከተማ በሚገኘው የኢቴሶ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ጥናት የዶክትሬት ተማሪ የሆነችው ሲልቪያ ኮሪያ “በ17 ዓመቴ ድንበር ስሻገር ሕልሜ መማርና በኅብረተሰቡ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችል ሰው መሆን ነበር” ያለች ሲሆን፥ ሲልቪያ በማከልም “ይህ የውይይት መድረክ የተስፋ ምልክት መሆኑን አመላክታ፥ ውይይቱ የስደተኞችን እና ከቦታ ወደ ቦታ ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች ጋር የሚራመዱትን ሰዎች ድምጽ እንደሚያዳምጥ፥ እንዲሁም ምሁራዊ አስተንትኖ የሚሰጡ እና በሃዋሪያዊ ሥራ አገልግሎት ውስጥ ውሳኔ የሚሰጡ ሰዎችን ድምጽ እንደሚያካትት ገልፃለች።
በዚህ መርሃ ግብር በሜክሲኮ የሞንቴሪ ሃገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ካርሎስ ኤ ሳንቶስ ጋርሺያ፣ ኤል ፓሶ ቴክሳስ የሚገኘው የተስፋ ድንበር ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲላን ኮርቤት እና በቲዬራ ብላንካ የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ሃላፊ የሆኑት ሲስተር ዶሎሬስ ፓሌንሺያ “ተመለከታቸው፣ ወደ እነርሱ ቀረበ እና ተንከባከባቸው” በሚል ርዕስ የድንበር አከባቢ ብፁዓን ጳጳሳት በ 2024 ዓ.ም. ባወጡት ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
“አንድ እና ልዩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስለሆንን እንደዚህ ያለ ደብዳቤ ያስፈልገናል” ያሉት ሳንቶስ ጋርሺያ፥ ይህም በመሆኑ ከማንኛውም ብሔርተኝነት ባሻገር ማለፍ አለብን ብለዋል።
“እነዚህን እውነታዎች አንድ ላይ ስናዋህድ፣ የስደትን ጉዳይ ከህዝባዊ ንግግሮች ወይም ከትምህርታዊ ጥናቶች ብቻ አድርገን ከማየት የበለጠ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረን ይችላል” ያሉት ደግሞ የሜክሲኮ የሥነ ምግባር ምሁር እና በቺካጎ የሎዮላ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዮሃንስ ጋርሺያ ናቸው።
በዚህ የሶስት ቀን ዝግጅት የሰውን ልብ ተጋላጭነት የሚያሳይ የልምድ ምክክር ለመቀስቀስ የሚረዳ አዲስ ትምህርታዊ የውይይት ሞዴል መቅረቡ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ሞዴል በመላው ዓለም በተለይም በሜክሲኮ እና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ይረዳል ተብሏል።
ከስምንት የተለያዩ ሃገራት ከመጡት ተሰብሳቢዎች መካከል በሜክሲኮ የሬይኖሳ ክልል ረዳት ጳጳስ እና የሜክሲኮ ብፁዓን ጳጳሳት የሰዎች ዝውውር አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኢጌኒዮ ሊራ፣ ሜክሲካዊ የሥነ መለኮት ምሁር ጁታ ባተንበርግ፣ የላስ ፓትሮናስ መስራች ወይዘሮ ኖርማ ሮሜሮ፣ አርጀንቲናዊ የሥነ መለኮት ምሁር ፓብሎ ብላንኮ፣ ሜክሲካዊው የኢየሱሳዊያን ማህበር አባል እና የቦስተን ኮሌጅ ፕሮፌሰር አሌሳንድሮ ኦላዮ-ሜንዴዝ እና ሜክሲኮ-አሜሪካዊ የሥነ መለኮት ምሁር እና የሳንዲያጎ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቪክቶር ካርሞና ይገኙበታል።