ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኬልቄዶኒያውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤልን በመምበራቸው ሲቀበሏቸው  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኬልቄዶኒያውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤልን በመምበራቸው ሲቀበሏቸው   (@Vatican Media)

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት በደስታ ተቀበሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በቱርክ እና በሊባኖስ ከኅዳር 18-23/2018 ዓ. ም. እንደሚያደርጉ ቅድስት መንበር በይፋ ማስታወቋ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በቱርኪ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወደ ኢዝኒክ (ኒቂያ) መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያን እንደሚያከብሩ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር ይህን ካስታወቀች በኋላ የኬልቄዶኒያው ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል ደስታቸውን ገልጸው፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና በቁስጥንጥንያ ፓትርያርኮች መካከል ላለው የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ቅድስት መንበር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝት መስከረም 27/2018 ዓ. ም. ካስታወቀች በኋላ ከቁስጥንጥንያ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርተሎሜዎስ ቀዳማዊ ተባባሪ የሆኑት የኬልቄዶኒያው ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳሳ አቡነ አማኑኤል፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን የቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

በየዓመቱ ሰኔ 22 በሮም በሚከበረው የቅዱሳን ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ እንዲገኙ ከቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የልዑካን ቡድን እንደሚልክ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም በበኩላቸው በየዓመቱ ህዳር 21 በሚከበረው የሐዋርያው ​​ቅዱስ እንድርያስ ክብረ በዓል እንዲገኙ የልዑካ ቡድንን ወደ ኢስታንቡል እንደሚልኩ ይታወቃል።

ዘንድሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ራሳቸው በኦርቶዶክስ እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት መካከል አንድነትን እና መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዝ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል ለዜና አገልግሎቱ እንደገለጹት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በፓትርያርካዊ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቤርተሎሜዎስ ቀዳማዊ ባደረጉላቸው ግብዣ መሠረት እንደ ሆነ ገልጸው፥ የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር በኅብረት የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ንግደት በታላቅ ደስታ የተቀበሉት መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ሲካሄድ የቆየው የልኡካን ልውውጥ እና በኢስታንቡል ወደምትገኝ የቁስጥንጥንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ መሆኑ ይታወሳል። እስካሁን ድረስ ጉብኝቱ በዋና ከተማዋ አንካራ እና ፓትርያርካዊ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ጽሕፈት ቤት እና በዚያው የሚገኙ ካቶሊካዊ ማኅበረሰቦችን በመጎብኘት ብቻ የተወሰነ እንደ ነበር ይታወቃል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ325 ዓ. ም. የተካሄደው የኒቂያ ጉባኤ እስከ አሁን አጀንዳ ሆኖ ያልቀረበ ቢሆንም ነገር ግን ዘንድሮ የሚከበረው የጉባኤው 1,700ኛ መታሰቢያ ለጋራ ጉብኝት ዕድል መፍጠሩ ታውቋል።

ዘንድሮ የሚከበረው የጉባኤው መታሰቢያ ሌሎች ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ወንድሞች በተገኙበት ሲሆን፥ ይህ ጉባኤ የመጀመሪያዎቹን ሰባት የሃይማኖት መግለጫ አንቀጾችን ያዘጋጀ እና ሌሎች አምስቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 381 ዓ. ም. በተካሄደው በሁለተኛው የአብያት ክርስቲያናት አንድነት ጉባኤ የተጠናቀቁ መሆናቸው ይታወሳል።

“የኒቂያው ጉባኤ በተለይም ሁሉም ክርስቲያኖች የሚጋሩትን የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት መግለጫን የያዘ በመሆኑ ለእምነታችን እና ለእምነተ አንቀጽ እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል ተናግረዋል።

“በሮም ቤተ ክርስቲያን እና በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ ጥሩ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል፥ በሁለቱ መካከል የሚደረግ ነገረ-መለኮታዊ የጋራ ውይይት ቀጥሎ ወደ ፊት እየገሰገሰ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ይህም ከፓትርያርካዊ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ራስ-ገዝ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር እንደሆነ አስረድተዋል።

ግልጽ ሊደረጉ የሚገቡ ነጥቦች ቢኖሩም ነገር ግን ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በተወሰዱ ተነሳሽነቶች፥ ከእነዚህ መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1054 ዓ. ም. የተወገደው የመለያየት ቅራኔ አንዱ እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህ ዓመት የቅራኔው መወገድ 60ኛ ዓመት በማክበር ላይ እንደሚገኙ እና ይህም ብዙ መሰናክሎች ማለፋቸውን የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

“ዛሬ እርስ በርስ በምንግባባበት ትክክለኛው መንገድ ላይ እንገኛለን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል፥ በቅርብ ጊዜያት በሁለቱ እህትማማች አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነት እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቤርተሎሜዎስ ቀዳማዊ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት  ፍራንችስኮስ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መፍጠራቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል ገልጸዋል።

ከእነዚህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ከተጀመሩት መልካም ግንኙነቶች በተጨማሪ አስቀድሞ የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቴናጎራስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1964 ዓ. ም. በኢየሩሳሌም ባካሄዱት ታሪካው ስብሰባ ግንኙነቶች መጀመራቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል አስታውሰዋል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጊዜ የተደረጉት ግንኙነቶች ወደ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች እና የልኡካን ልውውጥ ደረጃ ማደጋቸው በጋራ ዕውቀቶች በኩል ገንቢ ውይይቶችን ለማድረግ አስፈላጊ መሆናቸውን፣ የግንኙነቱ ማደግ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በሚደረግ ውይይት ብቻ ሳይሆን በተግባር ደረጃም ወደ ፊት እየገሰገሰ እንደሚገኝ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1964 ዓ. ም. በኢየሩሳሌም ከተካሄደው ስብሰባ እስከ 2025 ዓ. ም ድረስ የተደረጉ መልካም ግንኙነቶችን በማስታወስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ325 ዓ. ም. የተካሄደው የኒቂያ ጉባኤ ዋና መሠረት እንደ ሆነ እና “እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1054 ዓ. ም. የመለያየት ቅራኔ በመወገዱ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አዲስ ግንኙነት መፍጠሩን መመልከት በቂ ነው” ብለዋል።

በእርግጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አለማወቅ መኖሩን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል፥ ዛሬ ግን በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል የተሻለ እውቀት መኖሩን ገልጸው፥ ቢሆንም አሁንም መሠራት ያለባቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

“ሌላውን ወደምንቀበልበት እና በሚገባ ወደምናውቅበት ዘመን ውስጥ እየገባን ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ “በተለይ አሁን በተሻሻሉት ግንኙነቶች ‘ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ’ የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈቃድ ለመፈጸም የሚረዱን ብዙ ጥልቅ ትስስሮችን እየፈጠርን እንገኛለን” ሲሉ የኬልቄዶኒያው ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

 

09 Oct 2025, 14:52