ሰብዓዊ ጥበቃን ወደ ብርሃን ማምጣት የሁሉም ሰው ተልዕኮ ሊሆን ይገባል ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በፊሊፒንስ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን እና አቅመ ደካሞችን ለመጠበቅ የቤተክርስቲያኗን ተልዕኮ የሚያጎላ ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን፥ ይህም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ ጥበቃ ጥረት ለማጠናከር አስፈላጊ እርምጃ እንደሆነ ተመላክቷል።
ይህ ጉባኤ በክልሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ መገኛ በሆነችው በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኘዋ ፊሊፒንስ የተካሄደ በዓይነቱ የመጀመሪያው ብሔራዊ ጉባኤ ሲሆን፥ በጉባኤው ላይ የፊሊፒንስ እና አጎራባች ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ባለሙያዎች መሳተፋቸው ተነግሯል።
“የሰብዓዊ ጥበቃ ተልዕኳችን፡ የተስፋ እና የመተሳሰብ ጉዞ” በሚል መሪ ቃል በፓምፓንጋ ግዛት፣ አንጀለስ ከተማ ለአራት ቀናት ያህል በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ብፁዓን ጳጳሳትን፣ የገዳማዊያት የበላይ አለቆች፣ ካህናት አባቶችን እና በጉዳዩ ላይ ባለሙያ የሆኑ ምዕመናንን ጨምሮ ከ300 በላይ ልዑካን ተሳታፊ እንደነበሩ ተገልጿል።
ዝግጅቱ በፊሊፒንስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ (CBCP)፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን (PCPM)፣ የፊሊፒንስ ዋና የበላይ ተቆጣጣሪዎች ጉባኤ (CMSP) እና በማኒላ ላይ የተመሰረተ የካቶሊክ ጥበቃ ተቋም (CSI) በጋራ ማዘጋጀታቸው ተነግሯል።
ጥበቃን የጋራ ተልዕኮ ማድረግ
በፊሊፒንስ ውስጥ በሚገኘው የካቶሊክ ሰብዓዊ ጥበቃ ተቋም ውስጥ የሰብዓዊ ጥበቃ ምርምር እና ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ኮሊን ራኢ ራሚሬዝ ለቫቲካን ረዲዮ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ብሄራዊ የጥበቃ ጉባኤ ሰብዓዊ ጥበቃ ሁሉም የሚጋራው ተልዕኮ መሆኑን የሚያሳይ አዲስ እይታን መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ፊሊፒናዊው ኤክስፐርት ከዚህ በፊት ጉዳዩ በጨለማ ውስጥ የቆየ መሆኑን እና የጥቂቶች ብቻ ኃላፊነት ተደርጎ ሲወሰድ እንደነበረ አብራርተው፥ አሁን ሊወሰድ የሚገባው በጣም አፋጣኙ እርምጃ ከምንም በላይ የሰፊው ማህበረሰብ ለውጥ እና ቁርጠኝነት ለመጠበቅ ሲባል ከጉባኤው የተገኘውን ነገር ለሌሎች ማካፈል መሆኑን አስታውሰው፥ ፍርሃቶች እና ይሉኝታዎች እየደበዘዙ እንዲሄዱ ሁሉንም ሰው ወደ አጀንዳው ማምጣት እና ውይይቱን መጀመር እንደሚገባ አሳስበዋል።
“በመካከላችን ያሉትን ተጋላጭ ሰዎችን ለማወቅ ሰዎቹ ያሉበትን ሁኔታ፣ ችግሮቻቸውን እና ተስፋቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው” ያሉት ባለሙያው፥ ይህም ሲሆን የአቢያተ ክርስቲያናት መሪዎች በራሳቸው ቁምስና ውስጥ ሊወስዷቸው የሚገቡትን የመከላከያ እርምጃዎች መቅረጽ ይችላሉ ብለዋል።
ጉባኤው በተለያዩ የሰብዓዊ ጥበቃ ዘርፎች ላይ በርካታ የትምህርት እድሎችን ያቀረበ ሲሆን፥ ራሚሬዝ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ሁለቱንም ማለትም ተጎጂዎችን እና ወንጀለኞችን የሚያካትቱ ክፍለ ጊዜዎች፣ የቀኖና እና የፍትሐ ብሔር ሕግን የሚመለከቱ ትንተናዎች፣ ቅድመ መከላከል እና ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን፣ ከደብሮች እና ትምህርት ቤቶች እስከ ድህረ-ገጽ ያሉ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ የህፃናት ጥበቃ ሥርዓቶችን፣ እንዲሁም በህፃናት ጥበቃ መንፈሳዊነት ላይ የሚያንፀባርቁ ክፍለ-ጊዜዎችን እንዳካተተ አብራርተዋል።
በጉባኤ ላይ የተገኙት የተለያዩ የተሳታፊዎች ውህደት በተለየ ሁኔታ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት የገለጹት ባለሙያው፥ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያት እና ምዕመናን ጎን ለጎን ሆነው የመማማር እድል እንዳገኙ አስታውሰው፥ ከዚህም በተጨማሪ ተሰብሳቢዎቹ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ሁለተኛ ዓመታዊ ሪፖርት ቀርቦላቸው እንደተወያዩበት ተገልጿል።
ጉባኤው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት መጠናከሩ
ወይዘሮ ራሚሬዝ እንዳሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጉባኤው የላኩት መልዕክት በሁሉም ተሳታፊዎች ታላቅ አድናቆት እና ምስጋና እንዳገኘ፥ እንዲሁም ጥንካሬን እንዳገኙበት ገልጸው፥ “በግሌ የቅዱስ አባታችንን ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ጋር ያለኝ ጥልቅ የአብሮነት ስሜትም ተሰምቶኝ ነበር” ብለዋል።
የብፁዕነታቸው መልዕክት በፊሊፒንስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ይህንን የሰብዓዊ ጥበቃ ተልዕኮ ብቻዋን እንደማትሸከመው፥ ነገር ግን ከመላው ቤተክርስትያን ጋር ሆና እንደምትወጣው የሚያረጋግጥ እንደነበር ጠቁመው፥ በመጨረሻም “ሁሉም ሰው በአዲስ ጉልበትና ለዚህ የጋራ ተልዕኮ በአዲስ ቁርጠኝነት ወደ ክልላቸው እንዲመለሱ አነሳስቷል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት አጠቃለዋል።