ፈልግ

በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከተዘጋ አራተኛ ሳምንት አስቆጥሯል በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከተዘጋ አራተኛ ሳምንት አስቆጥሯል 

የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት የመንግስት መዘጋት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ 'አደጋ' መሆኑን ገለጹ

የዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ ብሮሊዮ የአሜሪካ መንግስት መዘጋት “በሃገሪቷ ውስጥ በሚገኙ ድሆች እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ላይ” ጫና ስለሚያሳድር በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳሰቡ።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአሜሪካ መንግስት ከመስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም. (ኦክቶበር 1 ቀን 2025) ጀምሮ የተዘጋ ሲሆን፥ የመንግስት መዘጋት የሚከሰተው የአዲሱ የበጀት ዓመት ሳይገባ ሁለቱ የአሜሪካ ምክር ቤቶች በፕሬዝዳንቱ በቀረበላቸው የበጀት ረቂቅ ላይ ተስማምተው ማጽደቅ ሳይችሉ ሲቀሩ እንደሆነ ይታወቃል።

በፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀረበው የአዲሱ የበጀት ዓመት ረቂቅ ሪፐብሊካኖች በሚበዙበት በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ እንደራሴዎች ምክር ቤት (ሰኔት) ተመርቶ የነበረ ቢሆንም፥ ይሄንኑ ረቂቅ ለማጽደቅ የሚያስፈልገው ድምጽ ደግሞ 60 እና ከዛ በላይ እንደሆነ ይታወቃል። በምክር ቤቱ ውስጥ ሪፐብሊካን 53፣ ዲሞክራቶች ደግሞ 47 ሲሆኑ፥ ይሄንኑ በጀት ከደገፉ ሁለት ዲሞክራቶች በስተቀር 45 ዲሞክራቶች በጀቱ በተለምዶ የጤና መድህን ዋስትናን፣ የማህበራዊ ድጋፎችን እና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች የሚሰጡ ድጎማዎችን ይጎዳል በሚል ስለተቃወሙ የመንግስት መዘጋት እንዲከሰት ሆኗል።

ይሄንን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ አራተኛውን ሳምንት በያዘው የመንግሥት መዘጋት እየተጋፈጠች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕረዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ ብሮሊዮ ሕግ አውጪዎችና አስተዳደሩ ለሕይወት አድን ፕሮግራሞች የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች እንዲረጋገጥ እና የመንግሥት መዘጋት እንዲያበቃ ሁለቱ የሃገሪቱ ምክር ቤቶች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ የቀረበበት መግለጫ አውጥተዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በአሜሪካ መንግሥት መዘጋት ምክንያት ከ42 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አሜሪካውያን የሚሰጠው የምግብ እርዳታ (SNAP benefits) ሊቋረጥ እንደሚችል አስታውሰው፥ በዚህም በርካቶች አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ ያሳሰቡ ሲሆን፥ የዚህ የመንግስት መዘጋት ጫና የሚያርፈው ተጋላጭ የሆኑ ድሆች እና አቅመ ደካሞች ላይ እንደሆነ፥ ብሎም ይህ “ኢ-ፍትሃዊ እና ተቀባይነት የሌለው” ውጤት መሆኑን በአጽንዖት ገልጸው፥ ከዚህም በላይ የዩናይትድ ስቴትስ ብፁዓን ጳጳሳት ‘የተቸገሩትን የሚደግፉ ህዝባዊ ፖሊሲዎችን ይደግፋሉ’ በማለት ጠቁመዋል።

የአሜሪካ የግብርና ሚኒስቴር (USDA) ባወጣው ማስታወሻ መሰረት፣ አሁን ባለው የመንግሥት መዘጋት ወቅት ለምግብ እርዳታ የሚውለው የድንገተኛ ጊዜ ገንዘብ ጥቅም ላይ የማይውል ሲሆን፥ ይህ ደግሞ ከመስከረም 21 ጀምሮ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሚሰጠውን የምግብ አቅርቦት ድጋፍ አደጋ ላይ እንደሚጥል አሳስቧል።

መንግስት በመዘጋቱ 803 ሺ የፌደራል ሰራተኞች በጀት እስኪለቀቅ ድረስ ምንም ደሞዝ ሳይከፈላቸው ሥራ አቁመው እቤታቸው እንዲቆዩ (furloughed) የተደረጉ ሲሆን፥ ሌሎች 700 ሺ ሰራተኞች ደግሞ ሳይከፈላቸው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ታዘዋል።

የካቶሊክ ድርጅቶች በአንድነት
የመንግስት መዘጋት ከተነገረበት መስከረም 21 ማግስት ጀምሮ በርካታ የካቶሊክ ድርጅቶች በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ በሚደረግላቸው ፕሮግራሞች ላይ ማንኛውንም አሉታዊ ተጽእኖ ለማስወገድ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ለአብነት የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሬዚዳንት ኬሪ አሊስ ሮቢንሰን “በእነዚህ የማይግባቡ ምክር ቤቶች ውስጥ የሚያስተጋቡ ድምፆች ከዋሽንግተን አዳራሾች አልፎ ይሰማል” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

መንግስት በተዘጋ በ 27ኛው ቀን (ጥቅምት 17) የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጤና ማህበር ፕሬዝዳንት እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሲስተር ሜሪ ሃዳድ በበኩላቸው የአስፈላጊ ፕሮግራሞች መስተጓጎል በቤተሰብ እና በግለሰቦች ላይ ከባድ ጫና እንደሚያሳድሩ አስጠንቅቀው፥ ኮንግረሱ “ተጎጂዎችን የሚጠብቅ፣ የማህበራዊ ሴፍቲ ኔቶችን የሚያጠናክር እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው የጤና ጉዳዮች የሚያሻሽል የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ለመድረስ” እርምጃ መውሰድ አለበት ሲሉ አፅንዖት በመስጠት አሳስበዋል።

30 Oct 2025, 12:51