ፈልግ

የዳሬሰላም ሊቀ ጳጳስ በድህረ-ምርጫ ሁከት ለተጎዱ ሰዎች ለመጸለይ ታስቦ የተደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያሳርጉ የዳሬሰላም ሊቀ ጳጳስ በድህረ-ምርጫ ሁከት ለተጎዱ ሰዎች ለመጸለይ ታስቦ የተደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያሳርጉ   (AFP or licensors)

የታንዛኒያ ሊቀ ጳጳስ ከምርጫ በኋላ የሚከሰት ሁከት 'በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው' ማለታቸው ተነገረ

የዳሬሰላም ሊቀ ጳጳስ ጁድ ታዴየስ ራዋኢቺ የታንዛኒያ የምርጫ ውጤትን ተከትሎ በቅርቡ በተፈጠረው ሁከት ለተጎዱት እና ለቤተሰቦቻቸው ባደረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ደም መፋሰሱ “የታንዛኒያን እውነተኛ ገጽታ እንደማያንጸባርቅ” አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በታንዛኒያ የተካሄደው የአጠቃላይ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን፥ ቁጥሩ እስካሁን ይፋ ባይደረግም አንዳንዶች በግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

በሃገሪቷ ውስጥም ሆነ በውጪ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ጸሎት እያደረገች እንደምትገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በዳሬሰላም ሀገረ ስብከት የጸሎት ጥሪ ከተደረገ በኋላ ሊቀ ጳጳስ ጁድ ታዴዎስ ተጎጂዎችን ለማስታወስ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው ተገልጿል።

‘እውነተኛ የታንዛኒያ ነጸብራቅ አይደለም’
ሊቀ ጳጳሱ በመስዋዕተ ቅዳሴው መግቢያ ላይ እንደተናገሩት ከምርጫው በኋላ በተከሰቱት ግጭቶች “በርካታ ህዝብ መቁሰሉን እና ሰብዓዊ ክብሩን መነፈጉን” አሳስበው፥ ሃገሪቷ ክብሯን ከማጣቷም ባለፈ “በጅምላ” የተገደሉ ሰዎችን አጥታለች ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ጁድ ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ተቃውሞዋቸውን በመግለፃቸው በጥይት መመታት ቅጣት መሆን እንደሌለበት አሳስበው፥ አንዳንዶቹም በቤታቸው ውስጥ እያሉ መገደላቸውን ጠቁመዋል።

‘ይህ ድርጊት የታንዛኒያን እውነተኛ ገጽታ በጥቂቱም ቢሆን አያንጸባርቅም’ ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ምንም ማብራሪያ የሌለው፣ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ተግባር ነው ሲሉ አስምረውበታል።

በምርጫው ወቅት የሞቱትን ለማስታወስ የተዘጋጀ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት
በምርጫው ወቅት የሞቱትን ለማስታወስ የተዘጋጀ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት   (AFP or licensors)

ሊቀ ጳጳሱ በዕለቱ ንባብ ላይ በማሰላሰል “ፍትህ እና ጥበብ” የሚሉ ሁለት ነጥቦችን ያነሱ ሲሆን፥ “ታንዛኒያ የፍትህ እይታዋን አጥታለች” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ከሰላም ንግግሮች በተጨማሪ “የሰላም መሠረት ስለሆነው ስለፍትህ” የመናገር አስፈላጊነትን ጠቁመው፥ ከምንም በላይ ግን ጥበብ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ እና በዚያ የተገኙት ሰዎች ‘እኔ ጥበብ አለኝ ወይ?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

እንደ አዲስ መጀመር
በተመሳሳይ ሁኔታ በምዋንጄልዋ በሚገኘው የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳስ ገርቫስ ኒያሶንጋ የተመራ የሀገረ ስብከት መስዋዕተ ቅዳሴ መካሄዱ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም ሥነ ስርዓት ሊቀ ጳጳሱ በግጭቱ የተጎዱት እና ቤተሰቦቻቸው በዳዮቻቸውን ይቅር እንዲሉ እና ህይወታቸውን እንደገና እንዲጀምሩ ጠይቀው፥ “ይሄንንም የሚያደርጉት እንደ ፈሪ ሳይሆን፥ የፈረሰውን ነገር ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ በሚጠቅም ሁኔታ እንደገና ለመገንባት ዝግጁ የሆኑ ጀግኖች” በመሆን እንደሆነ ተናግረዋል።

ከቅዳሴው ጀርባ ስድስት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፥ እነዚህም ከምርጫ ጋር በተገናኘ በተፈጠረው ሁከት ለሞቱት ሰዎች መጸለይ፣ ለቆሰሉት መጸለይ፣ የጠፉትን (በሕይወት ያሉትንም ሆነ የሞቱትን) ለማግኘት አምላክ እንዲረዳቸው መጠየቅ፣ ንብረታቸው የወደመባቸውን ማጽናናት፣ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ቆም ብላ እንድታሰላስል እና ከእግዚአብሔር ዘንድ ፈውስና ዕርቅ እንዲወርድ ለመጸለይ እንደሆነ ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ ይህም ይሆን ዘንድ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ትሑት እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበው፥ “ትህትና ድክመት ሳይሆን፥ ነገር ግን ማንም ሰው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ብቻ የሚገባውን ቦታ ሊወስድ እንደማይችል የሚያውቅ ሰው ጥንካሬ ነው” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በመጨረሻም በመቤያ ሃገረ ስብከት ውስጥ ያሉ ካቶሊኮች በሙሉ በመስዋዕተ ቅዳሴው የጸሎት ዓላማ አንድ እንዲሆኑ በማበረታታት፥ አምላክ ሃዘን ለደረሰባቸው ሰዎች መፅናናቱን እንዲሰጣቸው፣ ምንም እንኳን ሀዘናቸው ቢበዛም የቆሰሉ ወገኖች እንዲፈወሱ፣ ሁኔታዎች ምንም ቢሆኑም የጠፉት ሰዎችም እንዲገኙ፣ ንብረታቸውን ያጡት ደግሞ እንዲበረታቱ በመጸለይ፥ “ህይወት እስካለ ድረስ አሁንም ተስፋ አለ” በማለት አጽናንተዋል።

11 Nov 2025, 13:40