ሞተው ለነበሩ ሕይወት ሊሰጥ “የማይሞተው ሞተ"
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በቀራኒዮ ኮረብታ ስለእኛ ሊሰዋ ፈቃዱ ሆነ፣ “ሞታችንን ለመሻር ሞተ" ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የወረደው እኛን ከመንፈሳዊ ሞት አስነስቶ መለኮታዊ ሕይወት ሊሰጠን ስለፈለገ ነው። እርሱ ከምጣቱ በፊት እኛ የሰው ልጆች በመንፈስ ሞተን የእግዚአብሔር ጸጋ ርቆብን በኃጢአት ጥላ ሥር ነበርን። በኃጢአት መቃብር ተዘግቶብን የሰይጣን ባርነት ቀንበር ተጭኖብን እንኖር ነበር።
በእውነት ሞት የሚባል የሥጋ ሞት አይደለም፤ የመንፈስ ሞተና ጥፋት ከሁሉም የከፋና የባሰ ሞተ ነው። በእውነት ሞት የሚለው ከአምላክ ጋር ተጣልቶና ተለይቶ በሰይጣን ስልጣን ሥር መሆን ነው፤ ዋና ሞት የሚባለውም የነፍስ ሞት ወይም ዘለዓለማዊ ኩነኔ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ከርስቶስ በፍቅራችን የተቃጠለ በመሆኑ በመንፈነሳዊ ሞታችን አዝኖ በኃጢአት መቃብር እንዳንበላሽ ብሎ በጊዜው ሊረዳን መጣ። እርሱ ሊሞት እኛ ግን ልንነሳ፣ እርሱ ወደ መቃብር ሊወርድ እኛ ግን ከመቃብር እንድንወጣ ፈለገ። ሕይወታችንና ነፍሳችንን ለማዳን ፍጹም መሥዋዕት ሆነ።
እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን በትንሣኤ ቀን “በሞቱ ሞታችንን ደመሰሰ፣ በትንሣኤው ሕይወትን መለሰልን ክርስቶስ ከሞት ተነሣ ሞትን ሻረው በመቃብር ለነበሩ ደግሞ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ሰጣቸው" እያለች ደስታዋን በመዝሙርና በዜማ ትገለጣለች። ለመንፈሳችን ትንሳኤ የሰጠንን ክርስቶስን ታመሰግናለች። እኛም ከእርሷ ጋር አብረን ስለተቀበልነው ደኀንነትና ዘለዓለማዊ ሕይወት እናመሰግነው። በኃጢአት ምክንያት አጥፍተነው የነበረውን ዘለዓለማዊ ይዋታችንን በሞቱ አማካይነት አገኘነው። በተቀደሰው ሞቱ ከዘለዓለማዊ ሞት፣ ኩነኔና ጥፋት ድነናል በእርሱ ታድሰን ተነሳን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያድነን ሞተ። እንዴት ቢወደን ነው! የእውነተኛ ፍቅርን ሥራ አሳይቶናል። ምክንያቱም “ሰው ሕይወቱን ስለ ወዳጆቹ አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር የለውም" እያለ ራሱ መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮአል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመሞቱ ሕይወት ሊሰጠን መሠዋቱ ደኀንነታችን ታላቅ መሆኑን ያረጋግጥልናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያድነን ብሎ ያደረገውን የፍቅር ሥራና መሥዋዕትነት በሚገባ በማስተዋል የተሰጡንን የደኀንነት ጸጋዎች እንወቅ፣ የደኀንነታችንም ጠላት ከሆነ ኃጢአትም በመራቅ ወደ ጽድቅም የሚያደርሰን መልካም ምግባር ለመፈጸም እንትጋ።