ፈልግ

ስደተኞች ሜክሲኮ በሚገኘው የአሜሪካ ድንበር አጥር አጠገብ ሲደረሱ ስደተኞች ሜክሲኮ በሚገኘው የአሜሪካ ድንበር አጥር አጠገብ ሲደረሱ  (ANSA)

የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት ሃገሪቱ ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች ባስተላለፉት መልዕክት ‘በመከራችሁ ጊዜ ከጎናችሁ ነን' ማለታቸው ተነገረ

የዩናይትድ ስቴትስ ብፁዓን ጳጳሳት ስደትን አስመልክቶ ባስተላለፉት “ልዩ መልዕክት” ሃገሪቱ ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች ‘በመከራችሁ ጊዜ ከጎናችሁ ነን’ በማለት አጋርነታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የሀገሪቱ የኢሚግሬሽን ህጎች “ትርጉም ያለው ማሻሻያ” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዩናይትድ ስቴትስ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባዔ እንደ አንድ የቤተክርስቲያን አካል ‘በተለይ አስቸኳይ የንግግር መንገድን’ በመሻት ባስተላለፉት “ልዩ መልእክት” በሃገሪቷ ውስጥ ባሉ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ነገር እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

በብፁዓን ጳጳሳቱ የተለቀቀው ይህ ልዩ መልዕክት እ.አ.አ. በ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት የወሊድ መከላከያ ህግን አስመልክቶ ላወጣው መመሪያ ምላሽ ለመስጠት ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ ይህ የመጀመሪያው ‘ልዩ መልዕክት’ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ እንደዚህ ያሉ መልዕክቶች ሊወጡ የሚችሉት በምልአተ ጉባዔ ብቻ እንደሆነ እና በጠቅላላ ጉባዔው ከተገኙት ብፁዓን ጳጳሳት መካከል ሁለት ሦስተኛው ሲያጸድቀው እንደሆነ ተገልጿል።

የአሁኑ መልዕክት 97 በመቶ የድምጽ ብልጫ በማግኘት የተላለፈ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ በልዩ መልዕክታቸው ለስደተኞች ባስተላለፉት መልዕክት “በመከራችሁ ጊዜ ከእናንተ ጋር እንቆማለን” በማለት ስደተኞቹ ብቻቸውን እንዳልሆኑ አረጋግጠውላቸዋል።

ደብዳቤው በመግቢያው ላይ “በፍርሀት እና በጭንቀት” ውስጥ ስለሚገኙት ስደተኞች በመጥቀስ የብፁዓን ጳጳሳቱን ስጋት የገለጸ ሲሆን፥ በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን “የሥም ማጥፋት” ዘመቻ፣ በማቆያ ማዕከላት ውስጥ ስላሉ ሁኔታዎች፣ ስለ ሃዋሪያዊ አገልግሎት እጦት እና ሌሎች በስደተኞች ክብር ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ጨምሮ የስደት ጉዳዮችን አስመልክቶ ስለሚነሳው ክርክር አንስቷል።

መልዕክቱ ብፁዓን ጳጳሳቱ ለሀገራቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ “ለሰላሟ እና ብልጽግናዋ” ያቀረቡትን ጸሎት በማስታወስ፥ “እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሰብዓዊ ክብር ለመጠበቅ” ድምፃቸውን ለማሰማት “እንደተገደዱ” ተናግረዋል።

“የካቶሊክ አስተምህሮ ሃገራት ስደተኞችን ጨምሮ የሁሉንም ሰዎች መሠረታዊ ክብር እንዲገነዘቡ ያሳስባል” የሚለው ልዩ መልዕክቱ፥ በተመሳሳይ ሁኔታ “የሰው ልጅ ክብር እና የአገር ደኅንነት እንደማይጋጭ” እና “ሁለቱም የሚቻሉት መልካም ፍቃድ ያላቸው ሰዎች አብረው መስራት ሲችሉ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ “ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሕጋዊ መንገድን” በማረጋገጥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ስደትን ብሎም ብዝበዛን ለመከላከል “መሳሪያ” ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ገልጸው፥ ሃገራት “ድንበሮቻቸውን እንዲቆጣጠሩ እና ለጋራ ጥቅም ሲባል ፍትሐዊ እና ህጋዊ የስደት ሥርዓት መመሥረት” እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ በልዩ መልዕክታቸው በጅምላ ማፈናቀል እና ሰብአዊነት የጎደለው ንግግር እንዲሁም ስደተኖችም ላይ ሆነ የሕግ አስከባሪ አካላት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን እንደሚቃወሙ በግልጽ ያመላከቱ ሲሆን፥ ለዩናይትድ ስቴትስ የስደተኞች ሕግ እና ሂደቶች ‘ትርጉም ያለው ማሻሻያ’ እንዲደረግም መክረዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም የቤተክርስቲያን አስተምህሮ የተመሰረተው “የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳያና ተምሳሌት በመፈጠሩ ለሱ በሚደረገው መሰረታዊ እንክብካቤ ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ መበለቲቱን፣ ወላጅ አልባውን፣ ድሆችን እና እንግዶችን ጨምሮ በጣም ተጋላጭ ለሆኑት “ጌታ ቅድሚያ” እንደሚሰጥ አመላክተዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ “ቤተክርስቲያን በስደተኛውም ሆነ በማንኛውም ሰው ላይ የሚደርስ በደል እንደሚያሳስባት” ገልጸው፥ “የስደተኞች ጉዳይ የሚያሳስበን ጌታ እንደወደደን እኛም እንደዛው መውደድ እንደሚገባን አምላክ ለሰጠን ትእዛዝ የተሰጠ ምላሽ ነው” በማለት አጠቃለዋል።

14 Nov 2025, 12:57