ፈልግ

የታኅሳስ 05/2018 ዓ.ም የመጀመርያው የስብከተ ገና ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የታኅሳስ 05/2018 ዓ.ም የመጀመርያው የስብከተ ገና ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የታኅሳስ 05/2018 ዓ.ም የመጀመርያው የስብከተ ገና ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.    ኢሳያስ 2፡1-5

2.    መዝሙር 121

3.    ሮም 13፡11-14

4.    ማቴዎስ 24፡37-44

የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል

ጌታ የሚመጣበት ቀን አለመታወቁ

በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና። ከጥፋት ውሃ በፊት በነበሩት ከእነዚያ ቀናት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩና፥ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ እንዳላወቁት፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች አንዷ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ።

“ነገር ግን ይህን እወቁ፤ ባለቤት ሌባ ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

እንደ ቤተክርስቲያናችን ስርዓተ አምልኮ ደንብ አቆጣጠር ዛሬ አዲስ የአምልኮ ዓመት እንጀምራለን፣ ይህም ለእግዚአብሔር ሕዝብ አዲስ የእምነት ጉዞ ነው። እናም ሁልጊዜ በእየአመቱ እንደምናደርገው ዛሬ የመጀመርያውን የስብከተ ገና ሣምንት እንጀምራለን። በዚህ ዛሬ በሥርዓተ አምልኮ በምንጀምረው የስብከተ ገና ወቅት ለመጪዎች አራት የስብከተ ገና ሣምንታት አራት የተለያየ ቀላማት ያላቸውን ሻማዎች አንድ በአንድ በእለተ ሰንበት እንለኩሳቸዋለን። የእነዚህ አራት በእየዕለተ ሰንበቱ የምንለኩሳቸው አራት ሻማዎች የዓለም ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ የዓለም ጨለማ ሊመጣ እንደ ሆነ ያመለክታሉ፣ እያንዳንዱ ሻማ ከገና በፊት ባሉት አራት ሣምንታት ውስጥ የተለየ የመንፈሳዊ ዝግጅት ገጽታን ይወክላል። በባህላዊ መልኩ፣ አራት ሻማዎች (ሦስት ሐምራዊ ቀለም ያላቸው እና አንድ ሮዝ የጽጌሬዳ ቀልም ያለው ሻማ) ክብ ቅርጽ ባለው አረንጓዴ የአበባ ጉንጉን ውስጥ ይደረደራሉ፣ እሁድ እሁድ ደግሞ አዲስ ሻማ ያበራል። በየሳምንቱ የሚበሩ ሻማዎች ቁጥር አንድ በአንድ ይጨምራል፣ ይህም የገና ቀን እየቀረበ ሲመጣ እየጨመረ የመጣውን ተስፋ እና እየጨመረ የመጣውን ብርሃን በምስል ያሳያል።

የእያንዳንዱ ሻማ ትርጉም እና ወጎች በስያሜ ትንሽ ሊለያዩ ቢችሉም፣ ለአራቱ ሻማዎች በጣም የተለመዱት ትርጉሞች እና ስሞች ተስፋን፣ ሰላምን፣ ደስታን እና በመጨረሻም ፍቅር ይወክላሉ።

ተስፋ፡ የመጀመሪያው ሐምራዊ ቀለም ያለው ሻማ አማኞችን በተለይም የመሲሑን መምጣት የተነበየውን ኢሳይያስን ያስታውሳል፣ በመጀመርያው ምንባብ ላይ እንደ ተጠቀሰው (ኢሳያስ 2፡1-5)።

ሰላም፡ ሁለተኛው ሐምራዊ ቀለም ያለው ሻማ ማርያምንና ዮሴፍን ወደ ቤተልሔም ያደረጉትን ጉዞ እና የክርስቶስ ልደት ለዓለም የሚያመጣውን የሰላም መልእክት ያስታውሳል።

ደስታ፡- ሮዝ (ወይም የጽጌረዳ) ቀለም ያለው ሻማ በሦስተኛው እሑድ ይበራል፣ በላቲን ቋንቋ 'ጋውዴቴ' ሰንበት በመባል ይታወቃል ትርጓሜውም "ደስታ" ማለት ነው። ቀለሙና ጭብጡ የገና በዓል እየቀረበ ሲመጣ ከንስሐ ወደ ክብረ በዓል የሚደረገውን ሽግግር ያጎላል፣ ይህም የምሥራቹን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙትን እረኞች ደስታ ያንፀባርቃል።

ፍቅር፡- የመጨረሻው ሐምራዊ ቀለም ያለው ሻማ የሚወክል ሲሆን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለሰው ልጅ ያለውን ወሰን የሌለው ፍቅር ያመለክታል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ አሁን ደግሞ ሐሳባችንን ወደ የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንመልስ።

ዛሬ በመጀመርያው የስብከተ ገና ሳምንት ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል የእግዚአብሔር ሕዝብ አዲስ የእምነት ጉዞ ማድረግ እንደሚገባው የሚገልጽ ሲሆን በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል (ማቴ 24:37-44) በስብከተ ገና ወቅት በጣም ቀስቃሽ ከሆኑ ጭብጦች አንዱን ያስተዋውቀናል፤ ይህም ጌታ የሰው ልጅን ለመገናኘት እንድሚሄድ ያስታውሰናል። የመጀመሪያው ጉብኝት - ሁላችንም የምናውቀው - የተከሰተው ከምስጢረ ሥጋዌ (ቃል ሥጋ መልበሱ)፣ ኢየሱስ በቤተልሔም ዋሻ ውስጥ ከመወለዱ ጋር የተገናኘ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ይገኛል፣ ጌታ ዘወትር ይጎበኘናል፣ በየቀኑ ከእኛ ጋር ይመላለሳል፣ የሚያጽናና መገኘት ይሆናል፤ በመጨረሻም፣ “በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ በክብር ዳግመኛ ይመጣል” የሚለውን በጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ ስንደግም ወይም ስንዘክር የምናውጀው ሦስተኛው፣ የመጨረሻው ጉብኝት ይኖራል። ዛሬ፣ ጌታ ስለዚህ የመጨረሻ ጉብኝት ይነግረናል፣ ይህም በዘመን መጨረሻ ላይ ስለሚሆነው፣ በጉዟችንም የት እንደምንደርስ ይነግረናል፣ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል" (ማቴ. 25፡31-32) ላይ እንደ ተጠቀሰው።

የእግዚአብሔር ቃል በተለመደው የክስተቶች መገለጥ፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና በጌታ ያልተጠበቀ መምጣት መካከል ያለውን ልዩነት ያጎላል። ኢየሱስ እንዲህ ይላል፡- “ከጥፋት ውሃ በፊት በነበሩት ከእነዚያ ቀናት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩና፥ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ እንዳላወቁት፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል" (ማቴ 24፡ 38-39)" ኢየሱስም እንዲሁ ይለናል። ከታላቅ አደጋ በፊት ስለሚሆኑት ሰዓቶች ስናስብ ሁልጊዜ ገመድ በአንገታችን የገባ ይመስለናል። ሁሉም ሰው የተረጋጋ ነው፣ እናም ሕይወታቸው ሊገለባበጥ እንደሆነ ሳያውቁ የተለመደውን ተግባራቸውን ያከናውናሉ። እርግጥ ነው፣ ቅዱስ ወንጌል ሊያስፈራራን አይፈልግም፣ ነገር ግን አድማሳችንን ወደ ሌላ፣ ወደ ትልቅ ገጽታ ለመክፈት ይፈልጋል፣ ይህም በአንድ በኩል የዕለት ተዕለት ነገሮችን ወደ እይታ የሚያመጣ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውድ እና ወሳኝ ያደርጋቸዋል። ሊጎበኘን ከሚመጣው አምላክ ጋር ያለው ግንኙነት እያንዳንዱን ምልክት፣ እያንዳንዱን ነገር የተለየ ብርሃን፣ ንጥረ ነገር፣ ምሳሌያዊ እሴት ይሰጣል።

ከዚህ አንፃር፣ በዚህ ዓለም ነገሮች፣ በቁሳዊ እውነታ ቁጥጥር ሥር ከመዋላችን በፊት እነሱን ለመቆጣጠር ወደ ንጽህና መሥመር እንድንጓዝ ሊጋብዘን ይመጣል። በተቃራኒው፣ በእነዚህ ነገሮች ተጽዕኖ እንዲደርስብን እና እንድንሸነፍ ከፈቀድን፣ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እንዳለ ማስተዋል አንችልም፡ ይህም ከጌታ ጋር ያለን የመጨረሻ ግንኙነት ነው። ይህ አስፈላጊ ነው። ያ መገናኘት፣ የጌታ በሕይወታችን ውስጥ መገኘት አስፈላጊ ነው። እናም የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ይህ አድማስ ሊኖራቸው ይገባል፣ እናም ወደዚያ አድማስ መመራት አለባቸው። ይህ ለእኛ ሲል ከሚመጣው ጌታ ጋር የመገናኘት ዕድል ይከፍታል። በዚያ ቅጽበት፣ ወንጌል እንደሚለው፣ “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል" (ማቴ 24፡40) ይለናል። ንቁ እንድንሆን የቀረበ ግብዣ ነው፣ ምክንያቱም መቼ እንደሚመጣ ስለማናውቅ ለመሄድ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን አለብን።

በዚህ የስብከተ ገና ወቅት፣ የልባችንን አድማስ ለማስፋት፣ በየቀኑ በአዲስነት በሚቀርበው ሕይወት እንድንደነቅ ተጠርተናል። ይህንን ለማድረግ፣ በራሳችን እርግጠኛነት፣ በራሳችን በተቋቋሙ ስልቶች ላይ ላለመመካት መማር አለብን፣ ምክንያቱም ጌታ በማናስበው ጊዜ እና ሰዓት ይመጣል። ወደ ይበልጥ ውብ እና ታላቅ ገጽታ ሊወስደን ይመጣል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

በዛሬው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መካከል ከማቴ. 24: 37 – 44 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የሚገልጽ የደስታ ቃል ኪዳን ያለበት ነው። በማቴ. 24:42 ላይ ‘ጌታችሁ ይመጣል’ ይላል። የተስፋችን መሠረት የሆነው ይህ ቃል ኪዳን በችግር እና በስቃይ ሕመም ውስጥ ለሚገኝ ሕይወታችን ድጋፍ ይሆነናል። እግዚአብሔር የሚመጣበት ጊዜ መቃረቡን መዘንጋት የለብንም! እግዚአብሔር ወደ እኛ ዘወትር ይመጣል፣ ይጎበኘናል፣ ይቀርበናል። በጊዜው መጨረሻ በእቅፉ ሊቀበለን ተመልሶ ይመጣል። ነገር ግን ከሁሉ አስቀድመን ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን አንድ ጥያቄ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ በምን መልኩ እንደሚመጣ እና እርሱ መሆኑንም እንዴት ማወቅ እንችላለን? እንዴትስ እንቀበለዋለን? የሚሉ ጥያቄዎችን መመልከት ይኖርብናል።

‘ኢየሱስ ክርስቶስ በምን ሁኔታ ይመጣል?’ የሚለውን የመጀመሪያ ጥያቄ ስንመለከት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንገዳችን አብሮን እንደሚጓዝ ሲነገር ብዙውን ጊዜ እንሰማለን። ነገር ግን አዕምሮአችን በብዙ ነገሮች ስለሚያዝ ይህን እውነት እንደ ሐሳብ ብቻ እንመለከተዋለን። በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ ብናውቅም እንኳ እውነቱን በተግባር አንኖረውም። ወይም አንዳንድ ተዓምራትን እያሳየን በአስደናቂ መንገድ እንደሚመጣ እንገምታለን። ‘በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና’ (ማቴ. 24:37) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ተሰውሮ እንደሚገኝ እና ዘወትር ከእኛ ጋር መኖሩን ልብ ልንለው ይገባል። እርሱ በተለመደው ዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ይገኛል። እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ የሚገልጸው ልዩ ክስተቶች በማሳየት ሳይሆን በዕለት ተዕለት ክስተቶች አማካይነት ነው። በዕለታዊ ሥራዎቻችን መካከል እግዚአብሔር አለ። በተቸገሩት ሰዎች አምሳል እግዚአብሔር ራሱን ይገልጻል። ልንወጣ የማንችላቸው በሚመስሉ የመከራ ቀናት ውስጥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አለ። ዘወትር ይጎበኘናል፣ ይጠይቀናል፣ በሥራዎቻችንም ያግዘናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምን መልኩ እንደሚመጣ፣ እርሱ መሆኑንም እንዴት እናውቃለን? እንዴትስ እንቀበለዋለን? የሚለውን ሁለተኛውን ጥያቄ እንመለከታለን። መምጫውን በንቃት ልንጠብቅ ይገባል። የመምጫ ጊዜውን ካለማወቅ የተነሳ ሳንዘጋጅ እንዳንቆይ ኢየሱስ ክርስቶስ አስጠንቅቆናል። ቅዱስ አውግስጢኖስ ‘የእግዚአብሔርን የጉብኝት ቀን በፍርሃት እጠባባቃለሁ!’ ማለቱን በሌሎች አጋጣሚዎች መናገሬን አስታውሳለሁ። ቅዱስ አውጎስጢኖስ ይህን ያለበት ምክንያት እግዚአብሔር እንደጎበኘው ሳይረዳ እንዳይቀር በመፍራት ነው።በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንደነበር ተናግሯል። ‘የጥፋት ውሃም መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስኪወስድ ድረስ አላወቁትም ነበር፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል’ (ማቴ. 24:39) ይህን ልብ እንበል! በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች ምንም ነገር አላስተዋሉም ነበር! በግል ጉዳያቸው ተይዘው ነበርና የጎርፉን መምጣት አላስተዋሉም ነበር። “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 24:40 ላይ ተናግሯል። የጌታ መምጫ ቀን እንዴት ማወቅ ይችላል? ከሌሉች ቀናት የሚለየው በምንድን ነው? ይህን ማወቅ የሚቻለው ነቅቶ በመጠበቅ ነው። በዕለት ተዕለት ሕይወት መካከል እግዚአብሔር መኖሩን በመረዳት እና በማስተዋል ነው። ነገ ግን ሃሳባችን እና ትኩረታችን የሚከፋፈል ከሆነ ምንም ላናስተውል እንችላለን።

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት በምንጠብቅበት በዚህ የገና ሰሞን ከምንገኝበት የሕይወት ወጣ ውረዶች ተለይተን፣ ከአንቅልፋችንም በመንቃት ስለምገኝበት ሕይወት ራሳችንን ልንጠይቅ እንሞክር። በዕለት ተዕለት ሁኔታዎች መካከል እግዚአብሔር እንደሚገኝ ለማወቅ እሞክራለሁ? ወይስ በሃሳብ መከፋፈል የተነሳ በነገሮች ተጨናንቄያለሁ? በማለት ራሳችንን እንጠይቅ። ስለ እርሱ መምጣት ዛሬውኑ የማናውቅ ከሆነ በዘመኑ ፍጻሜ በሚመጣበት ጊዜም ዝግጁዎች ሆነን መጠበቅ አንችልም። ስለዚህ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የጌታን መምጫ ቀን ነቅተን እንጠብቅ። እርሱ ከእኛ ጋር፣ አጠገባችን ቢሆንም ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል። በናዝሬት ከተማ ከእግዚአብሔር ጋር በትህትና ያሳለፈችውን ሕይወት የተረዳች እና እግዚአብሔርን በማህፀኗ የተቀበለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኛም በመካከላችን የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣበትን ቀን በሕይወታችን ውስጥ ትኩረት ሰጥተን ነቅተን እንድንጠብቅ ትርዳን።”

የድነት ድንግል እመቤታችን፣ የሕይወታችን ባለቤቶች እንዳንሆን፣ ጌታ ሊለውጠው ሲመጣ እንዳንቃወም፣ ነገር ግን እቅዳችንን ቢያስተጓጉል እንኳን፣ በሚጠበቀው እና በሚቀበለው እንግዳ፣ እንዲጎበኘን እንድንፈቅድ ትርዳን።

ምንጭ፣ የቫቲካን ዜና የአማርኛው ክፍል

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)- ቫቲካን

 

 

13 Dec 2025, 20:47