59ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባዔ መደበኛ ጉባዔ ተካሄደ
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በታህሳስ እና በሃምሌ ወር ላይ የሚደረግ ሲሆን፥ በዘንድሮው 59ኛ የታህሳስ ወር መደበኛ ጉባዔ ላይ ከአዲግራት ሃገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ በስተቀር የአስራ ሁለቱ ሃገረ ስብከቶች ብጹዓን ጳጳሳት እና የቅድስት መንበር ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብሪያን ተገኝተዋል።
ጉባዔው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን መልዕክት በማዳመጥ የተጀመረ ሲሆን፥ ይህም ጉባዔው ከቅድስት መንበር ጋር ያለውን ህብረት የሚያመላክት እንደሆነ እና ብፁዓን ጳጳሳቱ በጉባዔው አጀንዳቸው የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ላይ በማተኮር ሐዋርያዊ እና ማህበራዊ ልማት አገልግሎቶች፣ ወቅታዊ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እና ሌሎችም የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ በመወያየት አቅጣጫ እና መመሪያዎችን ሰጥተዋል።
ጉባዔው መዋቅራዊ ለውጦችን ያደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል የጉባዔው ፕሬዝደንት ከሆኑት ከብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ጋር በጋራ በመሆን የጅማ-ቦንጋ ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም የእምድብር ሀገረስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የጉባዔው ቋሚ ጸኃፊ በመሆን እንዲያገለግሉ፥ በተጨማሪም የጉባዔው ቋሚ ኮሚሽን ተጠናክሮ እንዲመሰረት ጉባዔው ወስኗል።
ከዚህም በተጨማሪ ጉባዔው በብፁዓን ጳጳሳት የሚመሩትን ከ10 በላይ ኮሚሽኖች ሁኔታ ላይ በመወያየት መሪ ጳጳሳትን የመደበ ሲሆን፥ የሥያሜ እና ሌሎች ማሻሻያዎችን ማድረጉ እንዲሁም እ.አ.አ በ2014 የተዘጋጀው የጉባዔው መተዳደሪያ ደንብ ላይ አስፈላጊ ማሻሻያዎች በማድረግ ለቅድስት መንበር እንዲላክ መወሰኑ ተነግሯል።
ብፁዓን ጳጳሳቱ የሁሉም ሀገረ ስብከቶችን ነባራዊ ሁኔታዎች በጥልቀት እና በመደማመጥ መወያየታቸውን የገለጹት የጉባዔው ማህበራዊ ተግባቦት ኮሚሽን ተወካይ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ፥ በተለይም በአዲግራት ሀገረስብከት ጉዳይ ላይ በአብሮነት እና በመደጋገፍ መጓዝ የሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በእምድብር ሀገረ ስብከት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በተካሄደው 59ኛ መደበኛ ጉባዔ አጀንዳዎች ውስጥ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ አንደኛው ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ ለሀገር እድገት መሰረታዊ ነገር ሰላም መስፈን መሆኑን ገልጸው፥ “እንደ ሀገር ያለው እድገት የሚበረታታ ቢሆንም ለሀገርም ሆነ ለዜጎች ዘላቂ እድገት ሰላም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው” ብለዋል።
59ኛ መደበኛ ጉባዔ ከመካሄዱ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የሐዋርያዊ ሥራዎች ጽ/ቤት አስተባባሪነት እና በክቡር አባ ምስራቅ ጥዩ በአማሪኛ ትርጉም የተዘጋጀው የመጨረሻው የሲኖዶስ የመተግበሪያ ሰነድ በብፁዓን ጳጳሳት ተባርኮ የተመረቀ ሲሆን፥ ይህ የሲኖዶስ የመጨረሻው ሰነድ እንደየሰበካው ተጨባጭ ሁኔታ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ካታኪስቶች እና መላው ምዕመናን በህብረት አብረው እንዲጓዙ ጥሪ እንደቀረበ ተገልጿል።
ለአራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው 59ኛው መደበኛ ጉባዔ ላይ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በርካታ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ሲሆን፥ በተለይም ለ3 ዓመታት ያክል ውይይት ሲደረግበት ቆይቶ የወጣው እና በአማሪኛ ቋንቋ ተተርጉሞ የወጣውን የመጨረሻው የሲኖዶስ ሰነድ በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችሉ አቅጣጫዎች የተሰጡበት መሆኑን የጉባዔው የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ገልጸዋል።