የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን፥ በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ላይ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ያለውን ስጋት ገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን (COMECE) ማክሰኞ ኅዳር 30/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፥በአውሮፓ ኅብረት ሀገራት ውስጥ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እውቅናን በተመለከተ የአውሮፓ ኅብረት የፍትህ ፍርድ ቤት (CJEU) በቅርቡ ባወጣው ውሳኔ ላይ ስጋት እንዳለው ገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት የፍትህ ፍርድ ቤት (CJEU) ኅዳር 16/2018 ዓ. ም. እንዳስታወቀው፥ “የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ዜግጎቻቸው በሌላ የአባል ሀገር ውስጥ የመዘዋወር እና የመኖር ነፃነትን ተጠቅመው በሌላ የአባል ሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚፈጽሙትን የሁለት ተመሳሳይ ጾታዎች ጋብቻን የመቀበል ግዴታ አለበት” ሲል ወስኗል።
ጉዳዩ በጀርመን አገር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 ዓ. ም. የተጋቡ ሁለት ተመሳሳይ የፖላንድ ጥንዶችን የሚመለከት ሲሆን፥ እነዚህ ተጋቢዎች ወደ ፖላንድ ሲመለሱ ባለስልጣናት የምስክር ማስረጃቸውን በፖላንድ የሲቪል መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፥ ምክንያቱ የፖላንድ ብሔራዊ ሕግ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የማይፈቅድ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
“የአውሮፓ ኅብረት የዳኝነት ሚናን ሙሉ በሙሉ ብናከብርም በውሳኔው አንዳንድ ገጽታዎች ላይ አስተያየት ለመስጠት እንገደዳለን” ያለው ኮሚሽኑ፥ በብሔራዊ ብቃት ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በቁም ነገር መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
የአውሮፓ ኅብረት ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ከዚህ ጋር በተያያዘ በሚሰጡ ፍርዶች ላይ ዕድገት ማሳየቱን ኮሚሽኑ ጠቁሞ፥ ነገር ግን ይህ የቅርብ ጊዜ ውሳኔ የሕግ የበላይነትን ከአውሮፓ ኅብረት የብቃት ወሰን በላይ የሚጋፋ ይመስላል” ብሏል።
ጋብቻ የብሔራዊ ሕግ ጉዳይ ነው ብሎ መወሰን
“በዚህ ጉዳይ ላይ ጋብቻን የማወቅ ግዴታ በብሔራዊ ሕግ ውስጥ የተገለጸውን የአባል ሀገር የጋብቻ ተቋም የሚያዳክም አይደለም” ሲል የአውሮፓ ኅብረት ፍርድ ቤት ውሳኔ ገልጿል። ስለዚህ እያንዳንዱ ሀገር የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን መፍቀድ ወይም አለመፍቀድ የመወሰን ነፃነት ያለው በመሆኑ የአውሮፓ ኅብረት ሕግ በአሁኑ ጊዜ ይህን ነጻነት ሊሽር እንደማይችል አስረድቷል።
ሆኖም የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን (COMECE) በመግለጫው፥ የአውሮፓ ኅብረት ፍርድ ቤት ይህንን ነጻነት በሚጠቀምበት ጊዜ እያንዳንዱ አባል ሀገር ከአውሮፓ ኅብረት ሕግ ጋር መጣጣም እንዳለበት ገልጾ፥ “ፍርዱ የዚህ ዓይነት ማረጋገጫ አስፈላጊነትን እጅግ ያሳንሳል” ሲል አስታውቋል።
“አንዳንድ አነጋጋሪ የሕግ ሥርዓቶች ትርጉምን በሚያዳክም መንገድ የተጠቀሱ ሃሳቦችን ተግባራዊ የማድረግ አዝማሚያን በሐዘን እናስታውሳለን” ሲል የገለጸው ኮሚሽኑ፥ የአውሮፓ ኅብረት መሠረታዊ መብቶች ቻርተር አንቀጽ 9ን በመጥቀስ፥ የማግባት እና ቤተሰብ የመመሥረት መብት በብሔራዊ ሕጎች የተረጋገጠ መሆኑን ገልጿል።
“በአንዳንድ ሁኔታዎች እና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች አማካኝነት በተለያዩ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የሕግ ሥርዓቶች ውስጥ ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ አንድነት እንደሆነ መገለጹን የጠቀሰው የኅብረት አገራት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን፥ ለአንዳንድ የአውሮፓ ኅብረት አገራት የጋብቻ ትርጉም የብሔራዊ ማንነታቸው አካል መሆኑን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በተጨማሪም፥ ይህ ውሳኔ በሕግ እርግጠኛነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደርን የመሳሰሉ ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች እንዳሉት በማስረዳት፥ የአውሮፓ ኅብረት አገራት ወደፊት የትኞቹ የቤተሰብ ሕጎች በራሳቸው ነፃነት መቅረት እንደሚችሉ አስቀድሞ ማወቅ የሚያዳግት እንደሚሆን ገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን በተጨማሪም፥ ማህጸንን ለእርግዝና ማከራየትን ጨምሮ ይህ ፍርድ በሌሎች ስሜታዊ ዘርፎች አሉታዊ ዕድገቶች እና ወደፊት ተመሳሳይ የሕግ ዓይነቶችን ሊያመጣ እንደሚችል ያለበትን ስጋት ገልጿል።