የሄይቲ ብፁዓን ጳጳሳት ባስተላለፉት የገና መልዕክት ተስፋ እና ለውጥ እንዲኖር ጥሪ ማቅረባቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሄይቲ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ (CEH) ከገና ሳምንታት ቀደም ብሎ “የክርስቶስ ብርሃን በጨለማዎቻችን ውስጥ ይበራል” በሚል መሪ ቃል “የተፈተነ፣ በጥርጣሬ እና በህመም በተሞላ ጨለማ ሌሊት ውስጥ እየተጓዘ” ለሚገኘው ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሄይቲ ህዝብ “ያልተጠበቁ ስኬቶች” ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።
የገና ተስፋ
ህዳር 29 በተለቀቀው በዚህ የብፁዓን ጳጳሳት መልዕክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በድህነት ጥላ ስር” መወለዱን ጎላ አድርጎ በመግለጽ፥ ይህ ነገር በሄይቲ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ሰዎች ተምሳሌታዊ ሊሆን የሚችል መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ በዚህ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ላይ የሚከበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለሁሉም ሰው የተስፋ ምንጭ እንደሚሆን ብፁዓን ጳጳሳቱ አስታውቀዋል።
የብፁዓን ጳጳሳቱ ጥሪ ከእውነታው ተግዳሮቶች ለማምለጥ ብቻ ለሚደረግ የክርስቲያን ተስፋ ወይም ለቀቢፀ ተስፋ የተደረገ ጥሪ ሳይሆን፥ ከዚህ ይልቅ ይህ የክርስቲያን ወይም የገና ተስፋ ወደ ኃላፊነት እና ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ የሚገፋፋ መሆኑን ገልጸውታል።
በሄይቲ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት እንደገለጸው ከጥር 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም. ባሉት ወራት ብቻ ቢያንስ 4,388 ሰዎች በሃገሪቷ በተከሰተው የቡድን ጥቃት መገደላቸውን፣ ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና 12 ሚሊዮን ከሚጠጋው አጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለአስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት መዳረጋቸውን ይፋ አድርጓል።
ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ውስጥ በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም፥ የሄይቲ ብፁዓን ጳጳሳት ጥሪው ወይም እድሜው ምንም ይሁን ምን ሁሉም ሰው ‘ሰላም ፈጣሪዎች’ የመሆን ተልዕኮውን እንዲቀጥል አበረታተዋል።
ብፁዓን ጳጳሳቱ ‘የተስፋ ምልክት’ ብለው ያመሰገኑት ሌላው አካል ለ 2026 የዓለም ዋንጫ ያለፈውን የብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ሲሆን፥ የሄይቲ ህዝብ መለያየትን ማሸነፍ የሚችልበት ልዩ ምልክት በማለት ጠርተውታል።
ሃገራዊ ምርጫዎች መጪው ጊዜ ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ
ብፁዓን ጳጳሳቱ በሀገሪቱ እየተቀጣጠለ ያለውን ሁከት አስመልክተው “የተቋማት ጉልህ ውስንነቶች” እና የድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ማነስ እንደሆነ በመግለጽ፥ ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች፣ ማህበራዊ ተዋናዮች፣ የህዝብ እና የግል ተቋማት “ከፓርቲያዊ ፍላጎቶች በላይ ከፍ ብለው እንዲሰሩ” ጥሪ አቅርበዋል።
የሄይቲ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባዔ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሚካሄደው ሃገራዊ ምርጫ በፊት የህጎች ሁሉ ህግ ብለው የጠሩትን የ1987ቱን ሕገ መንግሥት ማዕከላዊ ሚና ጠቅሰው፥ ይህ ቀን የፕሬዚዳንታዊ የሽግግር ምክር ቤት (C.P.T.) የስልጣን ማብቂያ ጊዜ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ ሕገ መንግስቱን እንደ ማዕቀፍ ተጠቅመው ሁከት እንዳይፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።
መጪው ምርጫ “ዲሞክራሲያዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ግልጽነት” ሊኖረው የሚችለው እውነተኛ የጸጥታ ሁኔታ ከተፈጠረ ብቻ እንደሆነ የገለጹት ብፁዓን ጳጳሳቱ፥ ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር ሁሉም የሃገሪቱ ባለስልጣናት ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መልዕክታቸው በታማኝነት፣ በአገልግሎት እና መብቶችን ለመጠበቅ ባለው ድፍረት ላይ የተገነባ አዲስ አመራርን ያበረታታ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ ሃገሪቱ ሙስናን የሚጸየፉ፣ ማጭበርበርን የሚቃወሙ እና ለጋራ ጥቅም የሚሰሩ መሪዎች ያስፈልጓታል ብለዋል።
የሄይቲ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ በመጨረሻም ሃገሪቱን “የሰላም ልዑል” ለሆነው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አደራ በመስጠት እና ሄይቲን በድንግል ማርያም ጥበቃ ሥር እንድትሆን በመማጸን፥ ብርሃነ ልደቱ መጪው ዓመት ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አዲስ ተስፋ እንደሚፈነጥቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የብፁዓን ጳጳሳቱ መልዕክት የተፈረመው በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-አው-ፕሪንስ ሲሆን፥ በወቅቱ ሁሉን የሄይቲ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባዔ አባላት መገኘታቸው ተገልጿል።