ፈልግ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን 7.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት መጋለጣቸውን ገልጿል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን 7.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት መጋለጣቸውን ገልጿል  (AFP or licensors)

አንድ የደቡብ ሱዳን ጳጳስ ወጣቶች ሰላምን ለመገንባት ወሳኝ ናቸው ማለታቸው ተነገረ

ብፁዕ አቡነ ኤድዋርዶ ሂቦሮ ኩሳላ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ለራሳቸው እና ለመጪው ትውልድ ማህበረሰብ ሰላም እንዲያመጡ ለማበረታታት ታስቦ ለሁለት ቀናት ስለተካሄደው አውደ ጥናት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ህዳር 23 እና 24 ለሁለት ቀናት የተካሄደው የትውልዶች ቅብብል ዝግጅት በደቡብ ሱዳን ከምዕራብ ኢኳቶሪያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ አስር አውራጃዎች የተውጣጡ ወጣቶችን እና ከተለያዩ ማህበረሰቦች እና ጎሳዎች የተውጣጡ ተወካዮችን አንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ የአውደ ጥናቱ መሪ ሃሳብ “ሰላምን የሚገነቡ ወጣቶች የወደፊቱን ጊዜ የሚገነቡ ናቸው” የሚል እንደነበር ተገልጿል።

በደቡብ ሱዳን የቶምቡራ ያምቢዮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኤድዋርዶ ሂቦሮ ኩሳላ ዝግጅቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ለራሳቸው እና ለወደፊት ማህበረሰባቸው ሰላም ሊያመጣ በሚችል ነገር ላይ እራሳቸውን ሰጥተው እንዲሰሩ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በመጥቀስ የአውደ ጥናቱን አስፈላጊነት አብራርተዋል።

በወጣቶች፣ ለወጣቶች
ብፁዕ አቡነ ሂቦሮ የቫቲካን የዜና ወኪል ለሆነው ፊደስ ኒውስ እንደተናገሩት ውይይቱ እንዴት እንደተጀመረ ጠቁመው፥ ወጣቱ ዛሬን እና ነገን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድ ጭምር የሚከፋፍለውን መጥፎ ፖሊሲዎች ከመከተል ይልቅ አሁን ባላቸው ነገር ላይ እንዲያተኩሩ ይገባል ብለዋል።

አውደ ጥናቱ ስብሰባ ብቻ ሳይሆን ንቅናቄም ጭምር መሆኑን የጠቆሙት ጳጳሱ፥ ዝግጅቱ በወጣቶች የሚመራ፣ በወጣቶች የተደገፈ እና በአዛውንቶች ጥበብ የበለፀገ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸው፥ እራስን መውደድ፣ የጎሳ ማንነት፣ ሰላምን በልማት ማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ዕድል እና እኩልነትን ጨምሮ ሰላም ላይ ለመድረስ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ አስፈላጊ ነገሮችን ጠቁመዋል።

አንድ ሕዝብ በአሮጌ ቁስሎች ላይ አዲስ መንገድ መገንባት እንደማይችል የገለጹት ብፁዕ አቡነ ሂቦሮ በሀገሪቱ ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፥ አንድ ህዝብ ሊፈወስ የሚችለው ያለፈውን እና ስህተቱን ሲያስታውስ ብቻ ነው ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ሂቦሮ ወጣቶች ለመጪው ትውልድ የሰላም ድልድይ ለሆነው የአንድነት መልዕክተኞች እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበው፥ ይህም ጥሩ ጥሩ የሆኑ ነገሮችን መውሰድን እና በጊዜው ባህል ውስጥ ሊገኙ የሚችሉትን ጎጂ ነገሮችን አለመቀበልን እንደሚያካትት ጠቁመው፥ ወጣቶችን ከጥቃት ለመከላከል ማስተማር ዋናው ቁልፍ ነገር እንደሆነ አስረድተዋል።

በደቡብ ሱዳን ያለው ሁኔታ
ደቡብ ሱዳን በውስጣዊ ግጭት ውስጥ የቆየች ሃገር ስትሆን፥ ህዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም. የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዳሳወቁት ሀገሪቷ በፖለቲካዊ ጽንፈኝነት፣ እንደገና በተቀሰቀሰ የትጥቅ ግጭቶች እና በከባድ የሰብአዊ ጫናዎች ምክንያት ወደከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ እየገባች መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወሳል።

የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት እንዲሁም የአየር ላይ የቦምብ ጥቃቶችን ጨምሮ በመንግስት እና በተቃዋሚ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ እየተባባሱ መሆናቸው ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ 7.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት መጋለጣቸውን ጠቁሞ፥ ይህም በሀገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለውን የውስጥ ግጭት እያባባሰ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎረቤት ሱዳን ተጠልለው በመገኘታቸው ምክንያት በሃገሪቷ ላይ ተጠናክሮ የቀጠለው ግጭት በደቡብ ሱዳን ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩ የሚገለጽ ሲሆን፥ ይህ በእንዲህ እያለ በ 2019 ዓ.ም. የተለያዩ ሃገራዊ ምርጫዎችን ለማካሄድ እንደታቀደም ተነግሯል።

ብፁዕ አቡነ ሂቦሮ ከወጣቶች ጋር በመሆን የተሻለ የወደፊት ሁኔታን መገንባት እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ ወጣቶች በእምነት እና በሥነ ምግባር እሴቶች ላይ የተገነቡ የሰላም አርአያ መሆን እንዳለባቸው መክረው፥ “አብረን መጸለይ፣ ተባብረን መሥራት እና በአንድነት መነሳት አለብን” በማለት አጠቃለዋል።

08 Dec 2025, 10:55