ክርስቲያኖች ሊባኖስን ለቀው እንዳይወጡ መደገፍ ይገባል ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ማሬሌ፣ ቻርሎቴ እና ፉአድ የተባሉ ሦስት ግለሰቦች በሊባኖስ የሚገኘውን የ ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢን ኒድ’ ቡድን የሚመሩ ሲሆን፥ እነዚህ ሰዎች በአከባቢው የሚገኙ ብፁዓን ጳጳሳትን ለማግኘት እና በየሀገረ ስብከቶች እየተካሄዱ ያሉትን ፕሮጀክቶች ለማጥናት በመላ አገሪቱ እንደሚጓዙ ተገልጿል።
እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. በሊባኖስ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ የቤተሰቦችን እና የቤተክርስቲያን ተቋማትን የገንዘብ አቅም በእጅጉ እንደጎዳ የተነገረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ትምህርት ቤቶች፣ ቁምስናዎች እና ሀገረ ስብከቶች በየወሩ ለሰራተኞቻቸው ክፍያ እንደሚከፍሉ ተገልጿል።
በሊባኖስ ሰሜናዊ ክፍል በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ቆባይት ከተማ ውስጥ ያሉ በርካታ ትምህርት ቤቶችን እና የማገገሚያ ማዕከልን የሚቆጣጠሩት አባ ሬይመንድ አብዶ የዚህ ተቋም ዓላማ ቤተሰቦችን መደገፍ እንደሆነ ገልጸው፥ ለምዕመናን ልግስና እንዲሁም ለጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ፖላንድ እና ለፈረንሳይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ ምስጋና ይሁንና ትምህርት ቤቶቹን ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል።
ለሊባኖስ ቅድሚያ
ዋና መሥሪያ ቤቱን በፍራንክፈርት ያደረገው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አቢያተ ክርስቲያናትን የሚያግዘው ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢን ኒድ’ (ACN) ከ140 ሃገራት ዕርዳታ በማሰባሰብ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ፕሮጀክቶቹ የሚመድብ ሲሆን፥ በሊባኖስ የሚገኙ ክርስቲያናዊ ትምህርት ቤቶች አሁን በሚገኙበት አስቸጋሪ ሁኔታ እና በርካታ ክርስቲያኖች ሃገሪቷን ለቀው እየወጡ በመሆኑ ምክንያት ለሊባኖስ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
በሃገሪቷ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች በኑሮ ውድነት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በእርስ በርስ ግጭት፣ እንዲሁም በደቡባዊ ሊባኖስ እና በቤካ ሸለቆዎች ውስጥ በእስራኤል እና በሂዝቦላህ መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለስደት መዳረጋቸው ይገለፃል።
በምስራቃዊ ሊባኖስ በሚገኘው ቤካ ሸለቆ ውስጥ በ 2017 ዓ.ም. ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት ወራት ብቻ ቢያንስ 186 የቦምብ ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ለሂዝቦላህ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ሆኖ በሚያገለግል ቦታ ላይ በመፈንዳቱ በዙሪያው ባሉ ቤቶች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት አብዶ የተባለ ጡረታ የወጣ ወታደር እና የሁለት ሴት ልጆች አባት በፍንዳታው ከቤቱ መፈናቀሉ ተነግሯል። ከፍንዳታው በኋላ ከፍርስራሽ ስር ክፉኛ ተጎድታ የተገኘችውን ሴት ልጁ ለአምስት ቀናት በፅኑ ህክምና እንዳሳለፈች እና የሆስፒታሉን ወጪ ኤ.ሲ.ኤን እንደሸፈነው የተነገረ ሲሆን፥ ህጻኗ በአካል ብትድንም ነገር ግን የስነ-ልቦና ቁስሉ ጥልቅ እንደሆነ እና መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ከተከናወኑት ክስተቶች ‘የማይረሱ መሆናቸውን’ የገለጸው አብዶ፥ ከአደጋው በፊት ታድሶ የነበረው ቤቱ አሁንም እንደገና መገንባት እንዳለበትና ይህ ደግሞ የበለጠ ዕዳ ውስጥ እንደሚከተው ተናግሯል።
በእንደዚህ አይነት ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ ኤ.ሲ.ኤን ልክ እንደሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሁሉ የአደጋ ጊዜ ዕርዳታን ለማቅረብ ተግቶ የሚሰራ ሲሆን፥ ሦስቱ የአከባቢው ሰራተኞች እያንዳንዱን ጉዳይ ፍራንክፈርት ለሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤት ከማቅረባቸው በፊት ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚመረምሩ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ በደቡባዊ ሊባኖስ በግጭቱ ለተጎዱ የክርስቲያን ቤተሰቦች የምግብ እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፥ እስራኤል በአከባቢው ላይ የምትፈጽመው ወታደራዊ ዘመቻ ሲያበቃ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ድርጅቱ ተስፋ ማድረጉ ተገልጿል።
ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም የወደሙ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እንዲቻል እርዳታ ለማድረግ ማቀዳቸውን የገለጹ ሲሆን፥ መኖሪያ ቤት እና ትምህርት ቤቶች ከሌሉ ክርስቲያኖች አከባቢውን ለቀው እንደሚሄዱ ስለሚታወቅ፥ ይሄንን ለማስቀረት ኤሲኤን የግል የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።
ብዙ ጊዜ ‘ላውቬር ዲ ኦሪየንት’ (L'Œuvre d'orient) ከመሳሰሉ ትልልቅ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር አብሮ የሚሰራው ኤሲኤን ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እንዲያስችላቸው ለመምህራን የገንዘብ ድጎማ እንደሚያደርግ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ቁጥራቸው ከቀውሱ በኋላ ቢጨምርም ለተጋላጭ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ክፍያ በከፊል እንደሚሸፍን ተገልጿል።
‘ላውቨር ዲ ኦሪየንት’ የተሰኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ተቋም በበኩሉ ለጥገና እና እድሳት ግንባታ የራሱን አስተዋፅዖ የሚያደርግ ሲሆን፥ እነዚህ ድርጅቶች አንድ ላይ በመተባበር በአከባቢው የሚገኘውን ተግዳሮት ለመፍታት ተግተው እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አባ ሬይመንድ አብዶ ይህ ትብብር መልካም ነገር እንደሆነ እና ትምህርት ቤቶቹን ለማደስ ከበርካታ በጎ አድራጊዎች እርዳታ ማግኘታቸውን ገልጸው፥ ልጆቹ ብዙውን ጊዜ ከሩቅ ቦታ እንደሚመጡ እና አንዳንዶች ወደዚህ ስፍራ ለመድረስ ሁለት የትምህርት ቤት አውቶቡሶችን እንደሚሳፈሩ አስረድተው፥ ይህ ሁሉ ችግር ቢኖርም ቤተሰቦቻቸው የካቶሊክ ትምህርት ቤት ጥራት ላለው ትምህርት ዋስትና እንደሚሰጥ ስለሚያውቁ ልጆቻቸውን ይልካሉ ብለዋል።
በእምነት ለማደግ ምክንያቶችን ማቅረብ
በሰሜናዊ ሊባኖስ ውስጥ በምትገኝ መንጄዝ መንደር የቅዱስ ልብ ፍራንቺስካውያን ማህበር ሚስዮናውያን በአከባቢው የሚገኘውን ትምህርት ቤት እና ክሊኒክ የሚያስተዳድሩ ሲሆን፥ በየወሩ መምህራንን እና የአስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ ለ 35 ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ከገዳማዊያቱ ውስጥ አንዷ የሆኑት እህት አውሮር ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ለራሳቸው ገንዘብ እንደማይፈልጉ ገልጸው፥ ከተለያዩ ተቋማት በሚያገኙት ልገሳ ለሰራተኞች ደሞዝ እና ለመድኃኒት ማከፋፈያ አገልግሎት እንደሚያውሉ ገልጸዋል።
በኤል ሁሳን ከተማ የሚገኙት የ82 ዓመቱ የሳሌዢያን ካህን አባ ማሪዮ የበጋ ካምፖች፣ ጨዋታዎች እና ትምህርተ ክርስቲያንን ጨምሮ ህፃናትን በተመለከተ ብዙ አይነት እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ሲሆን፥ በሳሌዥያኖች መሬት ላይ በተቋቋመው እና ክርስቲያኖችንም ሆነ ሙስሊሞችን ተቀብሎ በሚያስተናግደው የሕዝብ ትምህርት ቤት ዙሪያ ህብረተሰቡ የተለያዩ ዛፎችን በመትከል፣ ለድንግል ማርያም ክብር የተሰጠ አደባባይ በመገንባት እና የስፖርት ሜዳ በማዘጋጀት ሁሉም ሰው በእንቅስቃሴው ውስጥ እንዲሳተፍ ጥረት እንደሚያደርግ እና በዚህም “የመገናኘት ባህልን” እንደሚያዳብሩ፣ ብሎም ሰላማዊ አብሮ የመኖር ባህል በትምህርት ቤት እና በቤተሰብ እንደሚጀምር አባ ማሪዮ በአጽንዖት ገልጸዋል።
የመታደስ ምልክቶች
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አዳዲስ እህቶች ትምህርት ቤቱን የሚመሩትን የቅዱስ ቤተሰብ ማሮናይት እህቶች የተቀላቀሉ ሲሆን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን የቤሩትን ጉብኝት በቅርበት የተከታተሉት እህት ሜሪ አንቶይኔት ሳዴ ለአስር ዓመታት ያክል የእህቶች ማሰልጠኛ ተቋም ተዘግቶ እንደነበር በመግለጽ፥ አሁን ግን ከኤሲኤን በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት ተቋሙ በመከፈቱ ምክንያት ሁለት እህቶች ስለተላኩላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
“አረጋውያን እህቶቻችን ትተውን እየሄዱ ነው” ያሉት እህት ሜሪ፥ ነገር ግን በእነዚህ አዳዲስ ጥሪዎች በኩል የመታደስ ምልክት እንደሚታያቸው ገልጸዋል።
ይህ ተሃድሶ በባልቤክ ሀገረ ስብከት ውስጥም እንደሚታይ የተገለጸ ሲሆን፥ 20 ወንድሞችና ሦስት ካህናት ከባዶ ተነስተው የቤይት ማሩን ገዳምን መመስረታቸው ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ተገልጿል። አብዛኛዎቹ ከ30 ዓመት በታች የሆኑት እነዚህ መስራቾች ከዩኒቨርሲቲ በኋላ የሚጠብቃቸውን ህይወት በመተው ሙያዊ ክህሎታቸውን ለህብረተሰቡ አገልግሎት ሰጥተዋል።
ከእነዚህም መካከል አንደኛው የጸሎት ቤቱን፣ የገዳማቱን ክፍሎች እና የቤተ ክርስቲያኑን ንድፍ የነደፈ አርክቴክት ሲሆን፥ ከካህናቱ ባሻገር ወንድሞቹ ደግሞ ድንጋይ ጠራቢዎች፣ አናጢዎች እና ግንበኞች በመሆን አብዛኛውን ነገር በገዛ እጃቸው መስራታቸው ተገልጿል።
ወንድም ክሪስቶፎረስ ‘እዚህ የተቋቋመው ነገር የእነሱ ንብረት እንዳልሆነ’ በመግለጽ፥ 3,000 ሰዎች ከሁለት ዓመት በፊት ባደረጉት ዓመታዊ ዝግጅት ላይ እንደተሳተፉ፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ 5,000 ሰዎች እንደተገኙ በማስታወስ፥ የመሰረቱት ገዳም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደሚስብ ገልጿል።
በቅዱስ ማሮን ትህትና እና አንጸባራቂ በሆነ የደስታ ህይወት ከሚኖሩት ከእነዚህ የካቶሊክ ወንድሞች መካከል ሁለቱ ከአውስትራሊያ የመጡ ሲሆን፥ የአውስትራሊያ ቤተክርስቲያን ለፕሮጀክታቸው ከፍተኛ ድጋፍ እንደምትሰጥ እና በግንባታው ቦታ ላይ "መነኮሳት-ሠራተኞች" የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ኤሲኤን የመድን ሽፋን እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
ተለዋዋጭነት፣ ተስፋ እና ጥርጣሬ
በበርካታ ተግዳሮቶች መካከል ያለፈችው የሊባኖስ ቤተክርስቲያን አሁንም ህያው ስትሆን፥ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ችግሮች መካከል፣ ውስብስብ በሆነ አካባቢ በተለይም በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል እና በቤካ ሸለቆዎች አከባቢ፥ አንዳንድ ጊዜ ለክርስቲያኖች መገኘት በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆና ለመፈወስ ትተጋለች።
ክርስቲያኖች በሊባኖስ ውስጥ እንደገና አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ የሚለውን ሃሳብ በተመለከተ መንገዱ ረጅም እንደሆነ እና እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል የገለጹት አባ ሬይመንድ አብዶ፥ ሃገሪቱን ‘በጽንፈኝነት’ እስላማዊ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎችን ማስተዋላቸውን ገልጸው፥ ይሄንን በምሳሌ ለማስረዳት በዱሪስ መንደር ቤታቸው የወደመባቸው ጆሴፍ እና አብዶ ከፍንዳታው በኋላ ሂዝቦላህ የሙስሊም ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በሚል ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገላቸው እና የክርስቲያን ቤተሰቦች ግን ጥቂት መቶ ዶላር ብቻ እንዳገኙ አብራርተው፥ እነዚህ ሰዎች በቀጥታ ባይገፉም፥ ነገር ግን ሂዝቦላህ በእርግጠኝነት እንዲቆዩ አያበረታታቸውም ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የባልቤክ-ዲር ኤል-አማር ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሃና ራህሜ ከሙስሊም “ጎረቤቶቻቸው” ጋር ውይይት ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ የገለጹት ካህኑ፥ “ምክንያቱም አብሮ ከመኖር ሌላ አማራጭ እንደሌለ” አስረድተው፥ ሆኖም አሁን ከእስራኤል ጋር ያለው ውጥረት ይህን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገልጸው፥ በ 2017 ዓ.ም. በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ጳጳሱ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ሙስሊም ቤተሰቦችን ማስጠለላቸውን አስታውሰው፥ ነገር ግን እነዚያን ቤተሰቦች ለእስራኤል ጥቃት ላለማጋለጥ ንቁ የሂዝቦላህ ታጣቂዎች እንዲወጡ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
“ከብፁዕ አቡነ ራህሜ ጋር ስንገናኝ የእስራኤል የስለላ አውሮፕላኖች በአየር ላይ ሲያጓሩ ነበር” ያሉት አባ ሬይመንድ፥ እነዚህ የጦር አውሮፕላኖች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሊባኖስን ለቀው እንደወጡ ተመልሰው መምጣታቸውን አስታውሰው፥ በርካታ ሊባኖሳዊያን ግጭት በማንኛውም ጊዜ እንደገና ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ እንደሆኑ አስረድተዋል።