ፈልግ

ቦጎታ ፥ ኮሎምቢያ ቦጎታ ፥ ኮሎምቢያ  

የኮሎምቢያ ብፁዓን ጳጳሳት በሀገሪቱ ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ ጥሪ ማድረጋቸው ተነገረ

የኮሎምቢያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ባካሄዱት 120ኛ ምልአተ ጉባኤያቸው ሀገሪቱ እንድትለወጥ እና ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ጳጳሳቱ የሃገሪቱ ዜጐች በመጪው ምርጫ በንቃት እንዲካፈሉ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

120ኛው የኮሎምቢያ ብፁዓን ጳጳሳት ምልአተ ጉባኤ ኮሎምቢያን የሃገሪቷ ጠባቂ ለሆነችው ለቺክዌንክዌይራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት አደራ በመስጠት እና ከህዝቡ ጋር በመሆን እርቅን፣ ፍትህን እና ሰላምን ፍለጋ ላይ በቁርጠኝነት ለመሳተፍ ቃል በመግባት የተጀመረ ሲሆን፥ በቦጎታ ከተማ የተካሄደው ጉባኤው ከአምስት ቀናት ጥልቅ ውይይት በኋላ አርብ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. መጠናቀቁ ተገልጿል።

በብፁዓን ጳጳሳቱ የጸደቀው የመጨረሻው ሰነድ ሕዝቡን ወደ መለወጥ፣ ወደ ውይይት እና በዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ኃላፊነት የተሞላበት ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚጋብዝ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ብፁዓን ጳጳሳቱ በተለይም በጣም አስቸጋሪው የክረምት ወቅት ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ሰዎች ያላቸውን ቅርበት እና ድጋፍ ገልጸው፥ በዚህ ረገድ እሑድ፣ የካቲት 7 ለተቸገሩ ቤተሰቦች በተለይም በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚያደርግ ‘መልካም ክርስቲያናዊ ግንኙነት’ የተባለ ዘመቻ የተጀመረ ሲሆን፥ ይህ ቤተክርስቲያኗ በጣም ለተጎዱት ሰዎች የምታደርገው ዓመታዊ ስብስብ ዘወትር የሚጀምረው በዐቢይ ጾም የመጀመሪያ እሁድ እንደሆነም ጭምር ተነግሯል።

መለወጥ እና እርቅ
የዐቢይ ጾም መግቢያን አስመልክተው ብፁዓን ጳጳሳቱ የሃገሪቱ ህዝቦች “እውነተኛ የመለወጥ እርምጃዎችን” እንዲወስዱ እና ወደ እውነተኛ ወዳጅነት እንዲመለሱ፣ እጅ ለእጅ እንዲያያዙ እና አንድነትን እንዲያጎለብቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበውን ግብዣ እንዲቀበሉ ያሳሰቡ ሲሆን፥ በዚህ አመለካከት እርቅ ረቂቅ ፅንሰ-ሀሳብ ሳይሆን ተጨባጭ የሆነ የግል እና የማህበራዊ ፈውስ መንገድ እንደሆነም አመላክተዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ “ለይቅርታ፣ ለእርቅ እና ለሃገሪቱ ሰላም” የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡ ሲሆን፥ ሁሉም ኮሎምቢያውያን “በልዩነቶች እና ተቃራኒ ሃሳቦች መካከል ድልድይ እንዲገነቡ” በማሳሰብ፥ መገናኘትን፣ መደማመጥን እና የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናችንን ማስተዋወቅ አለብን ብለዋል።

ለካህናት ያላቸው ቅርበት
የኮሎምቢያ ብፁዓን ጳጳሳት የአከባቢው ካህናት በመላው የሃገሪቱ ክልል ውስጥ በመገኘታቸው እና ስለሚሰጡት እጅግ ጠቃሚ አገልግሎት እንዲሁም በአደራ የተሰጣቸውን ማህበረሰቦች እምነት፣ ተስፋ እና የበጎ አድራጎት ሥራ አብረው በመጓዝ ስለሚንከባከቡ ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል።

“የካህናት ምስረታ ከዋና ዋና ተግባራት አንዱ ነው” ያሉት ብፁዓን ጳጳሳቱ፥ በዚህም ምክንያት የምዕመኑን አጠቃላይ ደህንነት ለመንከባከብ እና በአዲስ መልክ አገልግሎታቸውን እንዲያቀርቡ ራሳቸውን በመስጠት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ለህብረተሰብ አባላት ቀጥተኛ ጥሪ
ብፁዓን ጳጳሳቱ በተጨማሪም ኮሎምቢያውያን “የሰላም ምንጭ እና የተስፋ ምስክሮች እንዲሆኑ” ያሳሰቡ ሲሆን፥ ለህፃናት፣ ለወጣቶች እና ለጎልማሶች ባስተላለፉት መልዕክት እነሱን በመውደድ ደስተኛ እንዲሆኑ ካስቻላቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነትን እንዲመሰርቱ እንዲሁም ፍጥረትን እንዲንከባከቡ እና የሚያልሙትን ሀገር እንዲገነቡ መክረዋል።

“የማህበራዊ በጎነት መሰረታዊ ትምህርት ቤቶች” ተብለው የሚገለጹት ቤተሰቦች ህይወትን በመውደድ እና በማገልገል እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት ብፁዓን ጳጳሳቱ፥ ለመንግስት ተቋማት ባስተላለፉት መልዕክት የሰብአዊ መብት መከበር ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የዜግነት ግዴታዎችን እንዲወጡ፣ እንዲሁም የዲሞክራሲና የድጋፍ ሰጪ ተቋማትን እንዲያጠናክሩ ያበረታቱ ሲሆን፥ “እርቅን በብቃት ለማራመድ ብሎም በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ ያለውን ስር ነቀል መከፋፈል ለማስወገድ መንግስት ከሁሉም ጋር የሚደረገውን ውይይት እንዲያጠናክር” አሳስበዋል።

በሃገሪቱ የሚካሄደውን ምርጫ አስመልክተው እንደገለጹት ለከፍተኛ የመንግስት ስልጣን የሚወዳደሩ ሁሉ “ከቃላት ጥቃት እንዲርቁ እና እውነተኛ ሀገራዊ እድገትን፣ እርቅን እና ሰላምን ለማምጣት የሚያስችላቸውን ትክክለኛ መንገዶችን እንዲያቀርቡ” ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ በተመሳሳይ መልኩ ንግዱን የሚመሩ ሰዎች የማህበረሰብ ተሳትፎን እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን እንዲያበረታቱ እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች እና የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ሥራቸውን በኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የመራጮች ተሳትፎ
የኮሎምቢያ ብፁዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም በመጪው መጋቢት ወር በሚካሄደው የፓርላማ ምርጫ እና በግንቦት ወር ውስጥ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ሁሉም ዜጎች በንቃት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ የጋበዙ ሲሆን፥ ያለምንም ሙስና በሙሉ ነፃነት እና ህሊና የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

በኮሎምቢያ ባለስልጣናት ግብዣ መሰረት የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በሃገሪቱ የሚካሄደውን የህግ አውጪ አካላትን እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎችን ለመከታተል ወደ ኮሎምቢያ እንደሚጓዙ የታወቀ ሲሆን፥ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ካጃ ካላስ የአውሮፓ ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን ኢስቴባን ጎንዛሌዝን ዋና ታዛቢ አድርገው መሾማቸው ይፋ ተደርጓል።

16 Feb 2026, 13:58