ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን - የማህደር ምስል ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን - የማህደር ምስል  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የ 2018 ዓ.ም. ዐቢይ ጾምን አስመልክተው መልዕክት አስተላለፉ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕረዚዳንት እና ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የ 2018 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም መግቢያን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የመልዕክቱን ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርባለን፦

“አንተ ግን ስትጾም ራስህን ተቀባ፣ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር ላለው አባትህ እንጂ በሰዎች ዘንድ ጾመኛ ሆነህ እንዳትታይ፤ በስውር የሚያይ አባትህ ይከፍልሃል።” (ማቴዎስ 6: 17-18)

የተወደዳችሁ ካቶሊካውያን ምእመናን
በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙ ሁሉ
እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሰዎች በሙሉ

የእግዚአብሔር አምላክ ጸጋ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡-

በቅድሚያ እንኳን ለ2018 ዓ.ም. የዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።

የጾም ወቅት ከተለመደው አለማዊ ውሏችን ገለል በማለት የመለወጥን ጉዞ ለማጠናከር ወይም ለመጀመር ቤተክርስቲያናችን የምትሰጠን የጸጋ ወቅት ነው። በዚህ ቅዱስ ወቅት ራሳችንን በመግዛት፣ በሥነ-ምግባር በመጠንከር፣ ህሊናችንን በማዳመጥና በመመርመር ክርስቲያናዊ መታደስን ልንለማመድ ይገባል።
የዐቢይ ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ህማማት፣ ሞትና ትንሳኤውን በጥልቅ ማሰብ እና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳችንን ለማዘጋጀት የተሰጠን የጸጋ ጊዜ ነው። በፈተና በተሞላው ዘመናችን ክርስትናችንን በጸሎት፣ በጾም እና በምጽዋት ለማጠናከር የምንተጋበት ቅዱስ ወቅት ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጸለይን በቃል ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ አስተምሮናል። “አባታችን ሆይ” በማለት ያስተማረን ጸሎት እንዲሁም በጸሎት የኖረው ሕይወቱ የእውነተኛ ጸሎት መሠረታዊ ባህሪያትን ያሳያል። በዚህ ዓይነት፣ ከይዘቱ በተጨማሪ፣ ለማንኛውም እውነተኛ ጸሎት አስፈላጊ የሆኑትን ባህሪያት ያስተምረናል። እነዚህም ባህሪያት የእግዚአብሔርን መንግስት የሚሻውና ጠላቶችን ይቅር የሚል የልብ ንጽሕና፣ ከስሜታችንና ከግንዛቤአችን ባሻገር ርቆ የሚሄድ ግልጽና የልጅነት እምነት እንዲሁም ደቀመዝሙሩን ከፈተና የሚጠብቀው ንቃት ናቸው። (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁጥር 2608)

በዚህ በዐቢይ ጾም ወቅት የምናቀርበው ጸሎት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የበለጠ የሚያቀራርበን፤ ወደ እግዚአብሔር አብ የሚወስደን እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእምነት እና በተግባር የተሞላ ሊሆን ይገባል። በጸሎታችንም ከራሳችን አልፈን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ ለተጨነቁ ነፍሶች፣ በሀዘን በስቃይ እና በጦርነት ላሉ ወገኖቻችን፣ ለሀገራችን እና ለመላው ዓለም እንድንጸልይ አደራ እላለሁ።

የጾም ወቅት በሥጋዊ ሕይወታችን ከምግብ ከመቆጠብ ባሻገር ራሳችንን፤ ፈጣሪያችንን እና ሌሎች ወገኖቻችንን ለማድመጥ እድል የሚሰጠን ወቅት ነው። በማዳመጥ ውስጥ ሰላም አለ፤ በማዳመጥ ውስጥ እረፍት አለ፤ በማዳመጥ ውስጥ መግባባት አለ፤ በማዳመጥ ውስጥ ፍቅር ያብባል፣ በፍቅር ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለ።

የቤተክርስቲያናችን 266ኛው የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾችና እህትማማቾች ነን” በተሰኘው የሐዋርያዊ ማነቃቂያ መልዕክታቸው ውይይት ከልብ በማዳመጥ እና የሰውን ልጅ ሰብዓዊ ክብር ከመጠበቅ እንደሚጀምር ይገልጻሉ።

ህሊናውን የሚያዳምጥ አስተዋይ ሰው የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ይችላልና ሁላችንም ቆም ብለን በግብረገባዊ ንቃተ ህሊና ፈጣሪያችንን እናዳምጥ። በዙሪያችን የሞላውን ረብሻ፣ የውሸት ዜና፣ ሀሜት እና ምድራዊ ፍርድ ትተን በይቅርታ መንፈስ የዘለዓለማዊ ሕይወትን መንገድ እንጓዝ።
በወቅታዊ ሀገራችን ሁኔታ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን፣ መሪዎቻችን በጥበብ እንዲመሩ፣ ከተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እንዲሰውረን፣ የታሰሩ ምህረትን እንዲያገኙ፣ እና በእነዚህ ጊዜያት በመጾምና በመጸለይ በእምነታችን እንጽና።

በክርስቶስ የተወደዳችሁ መላው ካቶሊካውያን እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፣ በዚህ የዐቢይ ጾም ዘመን ቤተክርስቲያናችን የምታበረታታውን እውነተኛ ጾም እንድንጾም አደራ እላለሁ። ይህም ጎረቤቶቻችንን በንግግር ባለማሳዘን፣ ከሀሜት በመቆጠብ፣ ክርስቲያናዊ የፍቅር ሥራዎችን በመሥራት፣ የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር በመጠበቅ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ እና በእርሱ መኖር፣ በንስሃ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ በማስቀደስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ንቃት እንጹም።

የእመቤታችንና የመላእክት አማላጅነት፣ የሰማዕታትንና የቅዱሳን ጸሎት አይለየን!

+ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ/ም

17 Feb 2026, 12:07