ፈልግ

አንዲት ፊሊፒናዊት ምዕመን ዐቢይ ጾም በተጀመረበት ዕለት በማኒላ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሻማ ስታበራ አንዲት ፊሊፒናዊት ምዕመን ዐቢይ ጾም በተጀመረበት ዕለት በማኒላ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሻማ ስታበራ   (AFP or licensors)

በማይናማር በዐቢይ ጾም ወቅት በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የጸሎት እና የአብሮነት ጥሪ መደረጉ ተነገረ

የላቲን ሥርዐተ አምልኮ በምትከተለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሥርዐተ አምልኮ ደንብ መሰረት የዐብይ ጾም የሚጀምረው ረቡዕ ዕለት ካህናት የምዕመናንን ግንባር በአመድ የመቀባት ሥርዐት ካከናወኑ በኋላ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በመላው ኢስያ የሚገኙ የክርስቲያን መሪዎች ምዕመናን በግጭት ምክንያት ስቃይ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር በጸሎት፣ በጾም እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች እንዲተባበሩ መጋበዛቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በመላው ኢስያ የሚገኙ የቤተክርስቲያን መሪዎች በዚህ የዐቢይ ጾም ወቅት ምእመናን ጸሎትን፣ ጾምን እና የበጎ አድራጎት ተግባራትን አንድ ላይ በማስተባበር በግጭት ምክንያት ከሚሰቃዩ ሰዎች ጋር ህብረት እንዲያደርጉ ያሳሰቡ ሲሆን፥ በተለይም በማይናማር በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ምክንያት ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ከገባች ከአምስት ዓመታት በኋላም የሰላም ተስፋ ደካማ እንደሆነ በማስታወስ ለሃገሪቷ ጸሎት እንዲደረግ አሳስበዋል።

በማይናማር የኢየሱሳዊያን ማህበር የበላይ አለቃ የሆኑት አባ ጊሪሽ ሳንቲያጎ እ.አ.አ. የካቲት 1 ቀን 2021 ዓ.ም. የተደረገው መፈንቅለ መንግስት በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኙ እና አሳዛኝ የለውጥ ነጥቦች ውስጥ አንዱ እንደሆነ አስታውሰው፥ በዕለቱ ወታደራዊው ቡድን የሃገሪቱን ስልጣን በመቆጣጠሩ ለአስር ዓመታት የዘለቀው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በድንገት አብቅቶ በመላ ሀገሪቱን አለመረጋጋትና ግጭት ማስከተሉን አስታውሰዋል።

ከአምስት ዓመታት በኋላ በአሁኑ ወቅት የዚህ መፈንቅለ መንግስት መዘዝ በመላው ሃገሪቷ ባሉ ማህበረሰቦች ላይ ከባድ ችግር እያደረሰ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፥ አባ ጊሪሽ መፈንቅለ መንግስቱ የፖለቲካ ተስፋን ከማጨለሙም በላይ መፈናቀል፣ ኢኮኖሚያዊ ችግር እና ጥልቅ ማህበራዊ መከፋፈል የታየበት ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉን ጠቅሰው፥ “ለበርካታ ማህበረሰቦች ይህ ቀን በፍርሃትና በህሊና መካከል ያለውን ምርጫን፣ ሞራላዊ ተቃውሞ እንደገና መነቃቃቱን እና ለእውነት፣ ለፍትህ እና ለሰብአዊ ክብር መቆም የሚያስከፍለውን ዋጋ ያመለክታል” ብለዋል።

ካህኑ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ቀን የሚያስታውሰን የሰው ህይወት እና ዲሞክራሲ የጠፋበት የሀዘን ቀን መሆኑን፣ እንዲሁም ፍትህ አልባ ሰላም ደካማ መሆኑን የሚያስታውሰን ቀን ነው ሲሉ ገልፀውታል።

በፓስፊክ ኢሲያ የኢየሱሳዊያን ጉባኤ የተዘጋጀው የኢየሱሳውያን ማህበር መሪዎች ለዓመታዊ የበላይ አለቆች ጉባኤ በተሰበሰቡበት ወቅት ይህ ሃሳብ የተጋራ ሲሆን፥ ስብሰባው የተካሄደው በሆቺሚን ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው የባህር ዳርቻ ከተማ በሆነችው ቩንግ ታው ሲሆን፥ በዚህም ጉባኤ ላይ የተገኙት ከተለያዩ የኢስያ-ፓስፊክ ተልዕኮዎች የተወከሉ መሪዎች መሆኑ ተነግሯል።

ጉባኤው የምስረታ ፕሮግራሞችን፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል ትብብርን፣ የጤና እንክብካቤን እና የወጣቶች ተነሳሽነትን ጨምሮ ተጨባጭ የሆኑ ስጋቶች የተነሱበት ቢሆንም፥ በማይናማር የሚታየው ቀጣይነት ያለው ስቃይ በተደረገው የጋራ ጸሎት እና ማሰላሰል ውስጥ ቁልፍ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ተነስቷል።

ተሳታፊዎቹ ሃዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልዕክት “እኔ ተከልኩ አፖሎስም አጠጣ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር አሳደገው” በማለት በተናገረው ቃል ላይ ያሰላሰሉ ሲሆን፥ ይህም የእያንዳንዱ ተልእኮ መጨረሻው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንደሚያሳስብ ተገልጿል።

የተልዕኮ ትብብር ድርጅታዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትን፣ ትህትና እና የጋራ ኃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን ጉባኤው ያረጋገጠ ሲሆን፥ መሪዎች እንደተናገሩት በኢየሱሳዊያን ማኅበር ውስጥ በአሁኑ ወቅት ተልዕኮ ከግለሰብ አገልግሎት በዘለለ ወደ ባህሎች እና ጥሪዎች የጋራ አገልግሎት መሸጋገር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

በዚህ መንፈስ፣ የኢየሱሳውያን ጉባኤ የማይናማር ህዝብ ሰላምን፣ እርቅን እና ክብርን ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚፈልጉበት በአሁን ወቅት አጋርነቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ሲሆን፥ አባ ጊሪሽ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ማይናማር አሁን ያለችበት ሁኔታ ፖለቲካዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን፥ ነፃነት እና እርቅ አንድ ቀን ሊሰፍን ይችላል የሚል ተስፋ ያነገበ መንፈሳዊ ቁስልም ጭምር እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ክርስቲያኖች በጸሎት፣ በጾም እና በምጽዋት ለማሳለፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለ40 ቀናት በሚመላለሱበት የዐቢይ ጾም ወቅት ይህ መልዕክት በጣም ወሳኝ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የዐቢይ ጾም አማኞች የግል ምቾታቸውን እንዲተዉ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ የልብ ለውጥ እንዲያደርጉ እንዲሁም ለፍትህ እና ርህራሄ ራሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ጥሪ የሚያደርግ ወቅት እንደሆነ የገለጹት የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ፥ የዘንድሮው የዐቢይ ጾም ጉዞ በጦርነት፣ በስደት፣ በኢኮኖሚያዊ ችግር እና በበርካታ የኢስያ ክፍሎች ላይ በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል እንደሚካሄድ አስታውሰዋል።

በማይናማር የተከሰተው የተራዘመ ስቃይ በተለየ ሁኔታ የወቅቱን ጥሪ አስቸኳይ እንደሚያደርገው የገለጹት መሪዎቹ፥ ይህ የጾም ወቅት አማኞች በተሰቃዩት እና በተፈናቀሉ መካከል የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መገኘት እንዲገነዘቡ እና ጸሎትን ወደ ተጨባጭ የትብብር ተግባራት እንዲቀይሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለስደተኞች የሚደረገው እርዳታ፣ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ እና ሰለ ሰላም መሟገት በአስቸጋሪ ጊዜያት የሚታዩ የእምነት መግለጫዎች ተደርገው ይወሰዳሉ ተብሏል።

በመሪዎቹ የተደረገው ጥሪ ክርስቲያኖችን ለድሆች እርዳታ እንዳያደርጉ መከልከል ራሱ የፍትሕ መጓደል እንደሆነ የሚያስተምረውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ የተጠቀሰውን የቅዱስ ዮሐንስን ትምህርት እንደሚያስተጋባ ተገልጿል።

የዐቢይ ጾም በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት በመላው ኢስያ የሚገኙ የኢየሱሳዊያን መሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች ምዕመናን ማይናማርን በጸሎት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የርህራሄ እና የአብሮነት ምልክቶች እንዲያስታውሱ የጋበዙ ሲሆን፥ ግጭት እና ተስፋ መቁረጥ በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ ተስፋን መዝራት እና መንከባከብ እንደሚገባ እና እግዚአብሔር በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሃገራት እና ለደከሙ ማህበረሰቦች ጊዜው ሲደርስ እድገት እና ፈውስ እንደሚያመጣ መተማመን እንደሚገባ መክረው፥ ማይናማር ውስጥ ለሚኖሩ በርካታ ሰዎች ይህ ተስፋ ጸሎትም ሆነ ቃል ኪዳን ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

20 Feb 2026, 13:34