ፈልግ

የኪየቭ-ሃሊች ዋና ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ የኪየቭ-ሃሊች ዋና ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ   (©UGCC Department of Information)

ሊቀ ጳጳስ ሼቭቹክ ዩክሬናውያን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የሰላም ጸሎት ጋር መተባበራቸውን ገለጹ

በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ዩክሬናውያን በምሥራቃዊያን አቢያተ ክርስቲያናት የትንሣኤ ዋዜማ ዕለት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ የተመራውን የሰላም ጸሎት እንዲቀላቀሉ ጥሪ አድርገው እንደነበረ የገለጹ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ ጦርነት የሌለበት እና ሰላም የሰፈነባት ዓለም እንዲኖር እንዲሁም በዩክሬን እውነተኛ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“በጦርነት አውድ ውስጥ የሰው ልጅ ደካማነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ያሳየውን ዝምታ ያስተጋባል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ነገር ግን በሩሲያ ታግተው የተለቀቁት የዩክሬናዊያን ልጆች ምስክርነት በመካከላችን ያለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥንካሬ እንደሚገልጥ ያሳያል ብለዋል።

የኪየቭ-ሃሊች ሊቀ ጳጳስ እና በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሼቭቹክ ይሄንን የተናገሩት ዩክሬን እሁድ ሚያዝያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በጦርነት ውስጥ ሆና የምታከብረውን አምስተኛው የትንሳኤ በዓልን አስመልክተው ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ በተጨማሪም እሁድ ምሽት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የተደረገውን የሰላም ጸሎት መርሃ ግብር የመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “በጦርነት ማንም አሸናፊ እንደማይሆን እና ህፃናት ልጆች ትክክለኛ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም የማግኘት መብት እንዳላቸው” ያስተላለፉትን መልዕክት በድጋሚ አቅርበዋል።

ብፁዕነታቸው ከአራት ዓመታት በላይ በዘለቀው እና በዩክሬን እየተካሄደ ባለው መጠነ ሰፊ ጦርነት ውስጥ የሚከበረውን የምስራቅ አቢያተ ክርስቲያናት የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው እንደተናገሩት በእርግጥም ይህ በዓል በትልቅ ጦርነት ወቅት የሚከበር አምስተኛው የትንሳኤ በዓል መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፥ የሀሳቦቻችን እና የጸሎታችን ማዕከል ሊሆን የሚገባው ለዩክሬን ሰላም መሆን እንዳለበት አሳስበው፥ የህማማት ሳምንትን ጨምሮ በሚደረጉ መንፈሳዊ አምልኮዎች ወቅት የተኮነነውን፣ የተሰቃየውን፣ የተሰቀለውን፣ የተቀበረውን እና በመጨረሻም ሞትን ድል ነስቶ የተነሳውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማሰላሰል እንደሚገባ አሳስበዋል።

እነዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ የሆነ ፍቅሩን ያሳየበት ጊዜያት በልዩ ሁኔታ በዩክሬናውያን ልብ ውስጥ እንደሚያስተጋቡ የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ምክንያቱም እኛ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአንድ የመስቀል መንገድ እንደምንጓዝ ስለምናውቅ ነው ብለዋል።

‘የተወገዘውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስናስብ ሞት የተፈረደበት ምድራችን እና ህዝባችን እንደሆነ እናውቃለን’ ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ የተፈቱ እስረኞችን ምስክርነት ስናዳምጥ እሱን በሚኮንኑት እና በሚያሰቃዩት ፊት የሚታየውን የእስረኞች ዝምታ ያሳየናል ያሉ ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ ሰዎች ይህ ዝምታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ከፍተኛው የአይሁድ የሕግ አውጪ እንዲሁም የሃይማኖት እና የፍትህ ምክር ቤት በሆነው ‘ሳንሄድሪን’ ፊት ሲቀርብ ያሳየው ዝምታ ጋር እንደሚመሳሰል መረዳታቸውን ጠቁመው፥ ታግተው የተለቀቁትን ዩክሬናዊያን ህፃናት ምስክርነት ስንሰማ እነዚህ ህፃናት እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እና መሳሪያ በታጠቀው ጨቋኝ ፊት ምንም አይነት የመከላከል አቅም የሌላቸው መሆናቸውን በስሜታቸው አጋርተውናል ብለዋል።

በጦርነት አውድ ውስጥ ያለው ይህ የሰው ልጅ ደካማነት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዝምታ መስሏል ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ነገር ግን የእነዚህ ልጆች ደካማነት በመካከላችን ያለውን የክርስቶስን ጥንካሬ መግለጡን ጠቁመው፥ እነዚህ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ፣ ቤታቸውን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ያጡ፣ ነገር ግን የመተሳሰብን እና የተቸገሩትን የመርዳት ችሎታ ያላጡ የበጎ ፈቃደኞቻችንን ምስክርነት ስንሰማ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥንካሬ እንደሚያሳየን ብሎም፥ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች ህይወትን የሚያድኑ እና በድካማቸው ጊዜ የሚወድቁትን መርዳት የሚችሉ የቀሬናው ስምዖን ዓይነት ሰዎች ህያው ተምሳሌት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ምሽት ለሰላም ከተደረገው ጸሎት ቀደም ብለው ሁሉም ሰው በመርሃ ግብሩ ላይ እንዲገኝ መጋበዛቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዩክሬናውያን ከቅዱስ አባታችን ጋር አብረው እንደሚጸልዩ እና ለሰላም ነቅተው እንደሚቆዩ ጠቁመው፥ ይህ ጸሎት ከልባቸው የሚፈልቅ እንጂ ተገደው የሚያደርጉት ጸሎት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

“በዩክሬን በትንሣኤ ተስፋ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ላይ ሆነን በንቃት እንጠብቃለን” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ የሰው ልጅ ንቃተ ኅሊና መነቃቃት፣ መጋበዝ እና አንዳንድ ጊዜ ስለ ሰላም ለመጸለይ መነሳሳት ስለሚፈልግ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ላሳዩት ተነሳሽነት ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ ሁሉ፥ የክርስቶስ ሰላም ጦርነት በሰፈነበት በዛሬው ዓለም ላይ እንደሚያሸንፍ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ ከቫቲካን ኒውስ የተጠየቁት ብፁዕነታቸው፥ ጦርነቱ እንዲያበቃ፣ ህፃናት፣ ወታደሮች፣ ወንዶች እና ሴቶች ወደ ቤታቸው በሰላም እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በመጨረሻም በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን የጦር እስረኞች እንዲፈቱ እና ትንሳኤው በእውነትም ጦርነት የማይታይበት ዓለም አዲስ ጅማሮ እንዲሆን ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም ወደ ሩሲያ ተወስዶ የነበረው እና እናቱ አሁንም ድረስ በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ የምትገኝ አንድ ዩክሬናዊ ህፃን ልጅ ለቅድስት መንበር ሽምግልና ምስጋና ይሁንና አሁን ስለመለቀቁ የተናገረውን አንድ አስደሳች የሆነ ምስክርነት አስታውሰው፥ ይህ ልጅ የዩክሬናዊያን ህፃናትን የሰላም መልዕክት በጣም ግልጽ በሆነ መንገድ መግለጹን ጠቁመው፥ ልጁ ማንም ሰው የጠላትን ሞት እንደማይፈልግ ነገር ግን በዓለም ላይ የሚገኝ አንድም ህፃን ሊሰቃይ እንደማይገባ ወይም ዩክሬናዊያን ልጆች አሁን እያሳለፉት ያለውን መከራ ማለፍ እንደሌለበት ብቻ መናገሩን ያስታወሱ ሲሆን፥ ይህ ምስክርነት የዩክሬን ፖስታ ቤት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ማስታወሻነት ያሰራውን ማህተም ይፋ ባደረገበት ወቅት መሰማቱን ገልጸው፥ ይህ ማህተም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ “በጦርነት ማንም አሸናፊ እንደማይሆን፣ ህፃናት ልጆች ትክክለኛ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም የማግኘት መብት እንዳላቸው” ያስተላለፉትን መልዕክት የሚያስተጋባ መሆኑን ጠቁመው፥ ከዚህም በተጨማሪ በእሳቸው እይታ የዚህ ልጅ ቃል በዩክሬን እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙት ህፃናት የተሸከሙትን ትልቁን የሰላም መልዕክት ያስተጋባል በማለት አጠቃለዋል።

14 Apr 2026, 15:27