የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአልጄሪያ ጉብኝት የበለጠ ወንድማማችነትን እንደሚያበረታታ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ አልጄሪያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ እዚያ ያሉት ካቶሊኮች የብፁዕነታቸው ጉብኝት ትልቅ ማበረታቻ እንደሆነ ጠቁመው፥ ከዚህም ባለፈ አብዛኛውን የሃገሪቱን ሕዝብ ከሚወክሉት ከሙስሊሞች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደ መልካም አጋጣሚ አድርገው እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአልጄሪያ ጉብኝት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አባ ጆሴ ማሪያ ካንታል የተባሉ አንድ በአከባቢው የሚያገለግሉ አፍሪካዊ ካህን ሃዋሪያዊ ጉብኝቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ጉዞው በአካባቢው ያሉ ክርስቲያን ማህበረሰቦች “በዚህች ምድር የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች” ሆነው እንዲቀጥሉ ለማበረታታት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አስረድተው፥ ከዚህም በተጨማሪም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “እንደ ርዕሰ መስተዳድር” እና “የቤተክርስቲያን መሪ” ሆነው በሚያደርጉት ድርብ ጉብኝት፥ እንዲሁም እንደ አንድ “የሥነ ምግባር ስብዕና የተላበሰ ሰው እና መንፈሳዊ መሪ" ሃዋሪያዊ ጉብኝት እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት በአከባቢው ባለስልጣናት የተደረገላቸውን ድርጅታዊ የአቀባበል ጥረት አሞግሰዋል።
የአከባቢው ባለሥልጣናት ሁለቱንም ፕሮቶኮሎች በመምራት እና በማስተባበር ረገድ በጣም ጉልህ ተግባር እንደፈጸሙ የገለጹት ካህኑ፥ ምን ያህሉ የአልጄሪያ ሙስሊሞች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ማን እንደሆኑ ወይም ከቅዱስ አውገስጢኒዮስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሆነ እንዲሁም “እንደ አንድ አልጄሪያ ሙስሊም መደበኛ ሕይወታቸው” ምን እንደሆነ በግልጽ እንደማያውቁ ገልጸዋል።
ይህም በመሆኑ ምክንያት ይህ ሃዋሪያዊ ጉብኝት መንፈሳዊ መሪ በሆኑት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና በህዝበ ሙስሊሙ መካከል መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ብሎም እርስ በእርስ ለመማማር የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት እና በሁላችንም ዘንድ የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር የሚያነሳሳ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የተሻለ ወንድማማችነት የሰፈነባት ዓለምን ማስተዋወቅ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰኞ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ከአልጄሪያ ማኅበረሰብ ጋር የተገናኙበት የአፍሪካ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ቆሞስ የሆኑት አባ ፒተር ክላቨር በበኩላቸው ይህች ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ መድረክ በመሆን ለካቶሊኮች ብቻ ሳይሆን በርካታ የተለያዩ ሰዎችን አንድ ላይ እንዳሰባሰበች በማስረዳት፥ ብዙ ጊዜ ክርስቲያን ያልሆኑ፥ ነገር ግን ከቤተክርስቲያኗ ጋር ቁርኝት ያላቸው በርካታ ሰዎች ወደዚህ ባዚሊካ ለመጸለይ እንደሚመጡ እና በዚህም ሰላም እንደሚያገኙ መናገራቸውን ያስታወሱ ሲሆን፥ እኛ እንደ አንድ ክርስቲያን እንደምናደርገው ሁሉ፥ እነሱም እመቤታችን ድንግል ማርያምን ለፍላጎቶቻቸው መልስ እንድትሰጣቸው ወደ ስፍራው መጥተው ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት በባዚሊካው ውስጥ ባለው የመሠዊያ ስፍራ በላይ ያለው ጽሑፍ “የአፍሪካ እመቤታችን ሆይ ለእኛ እና ለሙስሊሞች ለምኚልን” ተብሎ መፃፉ ተገቢ ይመስላል የተባለ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሚያዝያ 5 ከአልጄሪያ ማህበረሰብ ጋር በተደረገው ስብሰባ የአልጄርስ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ፖል ቬስኮ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር ከ10 ቱ የቤተክርስቲያኑ ጎብኚዎች 9ኙ ሙስሊሞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“ይህ ባዚሊካ ሁል ጊዜ የስበት ማዕከል ነው” ያሉት አባ ኮግ በበኩላቸው ከባዚሊካው አስፈላጊነት የተነሳ ወደዚህ ሥፍራ የሚመጡ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመው፥ በአብዛኛው የሙስሊም ሃገራት የሳምንቱ የእረፍት ቀን በሆነው ዕለተ ቅዳሜ እና የበዓል ቀናት ይህች ቤተክርስቲያን በቀን እስከ 1000 ጎብኝዎችን እንደምታስተናግድ አስምረውበታል።
የእሳቸው ባዚሊካ የተለያዩ ሰዎች የሚገናኙበት ቦታ እንደመሆኑ ሁሉ፥ አባ ኮግ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአልጄሪያ ጉብኝት ግንኙነታቸው እና ጥረታቸው ሁሉ የውይይት፣ አብሮ የመኖር፣ የመቻቻል፣ የሰላም እና የመገናኘት ጊዜ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
አባ ኮግ በመጨረሻም ይህ ጉብኝት ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤው ያልነበራቸው በርካታ ሰዎች ‘በእርግጥ የተሻለ ዓለም፣ ይበልጥ ወንድማማችነት የሰፈነበት ዓለም እንፈልጋለን!’ ብለው እንዲናገሩ ይረዳቸዋል በማለት አጠቃለዋል።