አፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ያላት አመለካከት
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በ60ኛው የዓለም የማህበራዊ ግንኙነት ቀን ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ በመንተራስ የቅድስት መንበር የተግባቦት ጽህፈት ቤት ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. 'ለሰው ልጅ ድምጽ እና ፊት ጥበቃ ማድረግ' በሚል ርዕስ ሮም በሚገኘው በጳጳሳዊ ኡርባኒያና ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች የሰውን ልጅ ክብር፣ ትክክለኛ ግንኙነት እና የዲጂታል ዘመን ግንኙነቶችን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተው መወያየታቸው ተገልጿል።
ስለ ጥልቅ ሀሰተኛ ዜናዎች፣ የተዛቡ መረጃዎች፣ የአልጎሪዝም አድልዎ እና የዲጂታል መገለል አደጋን ያስጠነቀቁት ተሳታፊዎቹ፥ ከዚህም በተጨማሪ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አወንታዊ እድሎች በሃላፊነት እና በሞራል እሴቶች መመራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ውይይትን ማዳበር
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት የህብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ በፍጥነት እየለወጠ እና የፈጠራ እድሎች እያመቻቸ ቢገኝም በብዙዎች ዘንድ የሥነ ምግባር፣ የባህል እና የሰብዓዊነት ጥያቄዎችን እያስነሳ እንደሚገኝ በጉባኤው ተመላክቷል።
ከተወያዮቹ አንዷ የሆነችው ዶክተር ጆይ ቡኦላምዊኒ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ጉባኤው ጋዜጠኞችን፣ ሳይንቲስቶችን፣ የሥነ ምግባር ባለሙያዎችን፣ የፖለቲካ ባለሙያዎችን እና ኮሚዩኒኬተሮችን በአንድ መድረክ ማሰባሰቡን እና እስከአሁን ከተሳተፈችባቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውይይቶች መካከል ይሄኛው ጥልቅ ውይይት የተደረገበት ጉባኤ መሆኑን ገልፃ፥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት እያደጉ በመጡበት በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስባለች።
በጉባኤው ወቅት ከተነሱት አጀንዳዎች መካከል አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የፊት መለያ ሥርዓቶችን፣ ጥልቅ የሆኑ ሃሰተኛ መረጃዎችን እና አውቶማቲክ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቶችን የመጠቀም አዝማሚያ እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።
ዶክተር ጆይ “ኤክስ ኮድድ” (X-coded) ብላ የገለጸችው አንድን ግለሰብ በሰው ሰራሽ አስተውሎት መገልገያ ሥርዓት በጣም እየተጎዳ፣ እየተገለለ እና ሰብዓዊነቱ ለአደጋ እየተጋለጠ መምጣቱን ጠቁማ ማንኛውም ሰው ከዚህ አደጋ ነጻ እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥታ የገለጸች ሲሆን፥ በምሳሌ አስደግፋ ይሄንን ተግባር ስታስረዳ የታዋቂ ሰዎችን ምስሎች በማስምሰል ሃሰተኛ መረጃዎችን ማቅረብ እንዲሁም ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ያነጣጠረ ጥልቅ የሆኑ ሀሰተኛ መረጃዎችን ጠቅሳለች።
ከዚህም በተጨማሪ ማንነታቸው፣ ድምፃቸው እና ጥበባዊ ሥራቸው ያለፈቃድ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች በድጋሚ ሊሰሩ ለሚችሉ ግለሰቦች የባዮሜትሪክ መብቶች እና የፈጠራ መብቶች ጠንካራ የሆነ ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት የወደፊት ሁኔታን በመቅረጽ ረገድ የአፍሪካ ድርሻ
የጉባኤው ተሳታፊዎች አፍሪካ በሌሎች ቦታዎች የተሰራውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ብቻ ሳይሆን በራሷ አቅም ቴክኖሎጂውን በንቃት የማበልጸግ አስፈላጊነትን የጠቆሙ ሲሆን፥ በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ ከተማ የሚገኘው ዊት-ዋተስራንድ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ቤንጃሚን ሮዝማን ይሄንን ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት አፍሪካ በዓለም አቀፉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ውስጥ የመሳተፍን አስፈላጊነት ገልፀው፥ አፍሪካ ልዩ ፈተናዎች እንደሚገጥሟት በመጠቆም፥ በተለይም የቋንቋ ብዝሃነት፣ የጤና አጠባበቅ፣ ትምህርት እና ግብርናን የመሳሰሉትን ጉዳዮች ጠቅሰዋል።
በአህጉሪቱ ከ2,000 በላይ ቋንቋዎች እንደመነገራቸው መጠን እና ከእነዚህም ውስጥ በርካቶቹ “ዝቅተኛ ግብአት ያላቸው ቋንቋዎች” እንደመሆናቸው መጠን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን በብቃት ለማሰልጠን በቂ መረጃ እንደሌለ የገለጹት ፕሮፌሰሩ፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በቀላሉ ቴክኖሎጂን ማግኘት የመቻል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ማን እንደቀረፀው እና በውስጡም የእነማን እሴቶች ተካተው እንደሚገኝ ማወቅ የሚያስችል ሥርዓት እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።
‘ኢንዳባ የትምህርት ተነሳሽነቶች’ በመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች አፍሪካውያን ተመራማሪዎች እና ፈጣሪዎች ከሥነ ምግባራዊ እና ከባህላዊ ሁኔታ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን ለመፍጠር ያለመ ጠንካራ የፓን አፍሪካ ትብብርን በመገንባት ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ዶክተር ጆይ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ የአፍሪካ ዲጂታል ዳታ ተለይቶ የሚወጣበት እና የሀገር ውስጥ ማህበረሰቦችን ሳይጠቅም የውጭ ኮርፖሬሽኖችን ብቻ ለማበልጸግ በሚደረገው “ሁለተኛው የዳታ ቅኝ ግዛት” አሰራርን በማስጠንቀቅ ተመሳሳይ ስጋቶች እንዳሉ አስተጋብተዋል።
የአፍሪካ መንግስታት እና ተቋማት የዲጂታል ሀብቶችን እንዲጠብቁ እና የአፍሪካ ድምፆች በቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ እንዲወከሉ የጠየቁት ዶክተር ጆይ፥ እንደ ‘ፋርመርላይን’ ባሉ ኩባንያዎች የተገነቡትን እና አርሶ አደሮች በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የግብርና ምርታማነትን እና ኑሮን ለማሻሻል የሚረዱትን በአፍሪካ የበለጸጉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎችን ጠቁመዋል።
ቤተክርስቲያን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎትሥነ-ምግባራዊ አጠቃቀም
አባ ፋውስቲን ፋራህ የተባሉ ካህን በ60ኛው የዓለም የተግባቦት ቀን ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያስተላለፉት መልዕክት ላይ በማንፀባረቅ፥ የሰው ፊት እና ድምጽ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ ቅዱስ ስጦታዎች መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የምትመለከተው የሰውን የማሰብ ችሎታ ወይም መንፈሳዊ አገልግሎት ከመተካት ይልቅ እንደ አንድ መጠቀሚያ መሳሪያ መሆኑን አመላክተዋል።
የቫቲካን ሰነድ የሆኑትን ‘አንቲኳ’ እና ‘ኖቫን’ በመጥቀስ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የወንጌል ስርጭትን እና ግንኙነትን እንደሚደግፍ ነገር ግን እውነተኛ የሰዎች መስተጋብርን፣ ጥበብን እና የሃዋሪያዊ አገልግሎት መገኘትን ሊተካ እንደማይችል ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በሮም ከተማ ትምህርት ላይ የሚገኘው ናይጄሪያዊው ሜሶዬ ጦሂብ በበኩሉ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰውን ልጅ ከመተካት ይልቅ የሰውን ሥራ ማሳደግ እንዳለበት አበክሮ በመግለጽ፥ ወጣቶች በተለይ አዲሱ ትውልድ ለፈጠራ እና ለሂሳዊ አስተሳሰብ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ እንዳይሆኑ አስጠንቅቋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በፕሮግራም የተነደፈ እና የተገደበ ቢሆንም የሰው አቅም ግን ሊለካ የማይችል እንደሆነ ጠቅሶ፥ ወጣቶች ማንነታቸውን ወይም የፈጠራ ችሎታቸውን ሳያጡ እውነተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በኃላፊነት እንዲጠቀሙ ያበረታታ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ግልጽ የሆኑ የሥነ ምግባር ድንበሮች መኖር እንዳለባቸው እና በተለይም ሰብዓዊ ግንኙነቶችን፣ መንፈሳዊ መመሪያን እና የሞራል ውሳኔ አሰጣጥን በሚያካትቱ አካባቢዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ላይ ገደብ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
ኡቡንቱ፣ ፍትህ እና የአፍሪካ ድምፆች ጥበቃ
አናስታንቺያ ማኩኑ የተባለችው ሌላኛዋ የጉባኤው ተሳታፊ በበኩሏ ‘እኔ ያለሁት እኛ ስላለን ነው’ የሚለውን ‘ኡቡንቱ’ የተሰኘ የአፍሪካዊያን ፍልስፍናን በማስታወስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውይይቱን ከህግ እና ከተግባቦት አንፃር በማየት ሃሳቧን ያካፈለች ሲሆን፥ የአፍሪካ ማህበረሰቦች በግንባር ቀደም ግንኙነት፣ በሥነ ምግባር ታሪክ እና በጋራ መደማመጥ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን አመላክታ፥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈጠሩ ድምጾች፣ ቦቶች እና ምናባዊ እውነታዎች ትክክለኛውን የሰው ልጅ ግንኙነቶች ሊያዳክሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቃለች።
ማኩኑ ከዚህም ባሻገር የአፍሪካዊያን ነባራዊ እውነታዎች፣ ባህሎች እና እሴቶችን ማንፀባረቅ በማይችሉት በምዕራቡ ዓለም በበለጸጉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያለው ጥገኝነት እያደገ መምጣቱ እንዳሳሰባት ገልፃ፥ የአልጎሪዝም አድልዎ፣ ግላዊ ነፃነት ማጣት፣ መረጃን በመመጠን የአፍሪካዊያንን ጉልበት መበዝበዝ እና በተጋላጭ ማህበረሰቦች ውስጥ በተቋቋሙ የመረጃ ቋቶች የሚፈጠሩ የአካባቢ ችግሮችን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በአጽንዖት አንስታለች።
ከህግ አንፃር አድልዎ የሚታይባቸው ፊትን የመለያ ሥርዓቶች በተለይም በጥቁር ማህበረሰቦች እና ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ኢፍትሃዊነት እንደሚያጠናክር ያስጠነቀቀች ሲሆን፥ የሰው ልጅ ክብርን፣ ሰብዓዊ መብቶችን እና ባህላዊ ማንነትን የሚጠብቅ አፍሪካን ያማከለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር እንደሚያስፈልግ አሳስባለች።
ከዚህም በተጨማሪ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ የሚሰጠውን አወንታዊ አቅም በማስታወስ፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ውስብስብ የሆኑ የህግ ፖሊሲ ሰነዶችን ለማቃለል፣ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሻሻል፣ የቋንቋ ተግዳሮቶችን ለማቃለል እና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ እድሎችን እንዲያገኙ ለማገዝ እንደሚረዳ ማኩኑ ጠቁማለች።
ቴክኖሎጂ እያደገ ሲሄድ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰው ልጆችን ለማገልገል መዋል እንዳለበት፣ ትክክለኛው የሰው ድምጽ፣ ፊት፣ ባህል እና ግንኙነት መጠበቅ ለህብረተሰቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስፈላጊ መሆኑን በማሳሰብ ጉባኤው በጠንካራ መግባባት ተጠናቋል።