ፈልግ

በጅቡቲ በረሃማ አካባቢ በጉዞ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በጅቡቲ በረሃማ አካባቢ በጉዞ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች   (AFP or licensors)

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት የስደተኞች ደኅንነት እና ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ ጥሪ አቀረቡ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ይፋ ባደረገው ሐዋርያዊ መልዕክቱ፥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአፍሪካ ውስጥ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት የስደት ጉዞ ለሚገጥማቸው ከፍተኛ አደጋ አስቸኳይ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪውን አቅርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፥ “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና” (ማቴ. 5:7) የሚለውን የወንጌል ክፍል በመጥቀስ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ “ለብዙ ኢትዮጵያውያን ስደት ምርጫቸው ሳይሆን በሕይወት የመቆየት ጉዳይ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ከአገራቸው የሚሰደዱት ለሥራ ፍለጋ፣ ክብራቸውን ለማስጠበቅ እና ወላጆቻቸውን ለመደገፍ መሆኑን ጉባኤው አስታውቋል።

“ሆኖም ግን ብዙ ስደተኞች ያሰቡት ሳይሳካላቸው ቀርቶ ብዝበዛ፣ ዓመጽ እና ጥቃት ሲገጥማቸው ይስተዋላል” ያሉት ጳጳሳቱ፥ ስደተኞች በምንም መልኩ በቁጥር ወደ መታየት ደረጃ ዝቅ ማለት እንደሌለባቸው አጥብቀው በመናገር፥ የስደተኞች ሰብዓዊ ክብር በድንበር፣ በሕግ ረገድ ወይም በኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ጥሰት ሳይደርስበት ዘወትር ቅዱስ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ በሳውዲ አረቢያ መንግሥት የታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለሞት አደጋ መጋለጣቸውን በተረዱ ጊዜ የተሰማቸውን ጥልቅ ስጋት ገልጸው፥ “እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ቆሞ ምሕረት እንዲደረግላቸው” በማለት ለባለሥልጣናቱ ቀጥተኛ እና አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።

የምሕረትን የሞራል ግዴታ በአጽንዖት ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ የፍትህ ዋጋ በምሕረት እንደማይቀንስ ነገር ግን ይበልጥ እንደሚጨምር ተናግረው፥ ተስፋ መቁረጥ ባለበት ተስፋን እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

በቀይ ባሕር እና በየመን በኩል የሚጓዙ ስደተኞችን በደል፣ ብዝበዛ እና የሞት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው እና ይህን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን፥ በሊባኖስ የተከሰተው ዘላቂ አለመረጋጋት ብዙ ስደተኞችን አደጋ ውስጥ መጣሉ፥ ይህም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚቀርብ ጥሪ እንዲጨምር ማድረጉ ታውቋል።

በበርካታ የባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ የተከሰቱ ውጥረቶች በስደተኛው ማኅበረሰብ ድኅንነት ላይ አደጋን መደቀኑ ታውቋል። በደቡብ አፍሪካ ውስጥም በውጭ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ በዓመፅ የታገዙ ጥቃቶች ሕይወትን እና የኑሮ ሁኔታን አደጋ ላይ መጣሉ ታውቋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተለይም የሱዳን በረሃን አቋርጠው በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ እስር፣ የግዳጅ ሥራ እና አደገኛ የሆነ የባሕር ላይ ጉዞ እንደሚያጋጥማቸው ብጹዓን ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ ጠቅሰው፥ አደገኛ በሆኑ እነዚህ ጉዞዎች ብዙዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ እና ጥቂቶች ብቻ ወደ ጣሊያን ደሴት ላምፔዱሳ የባሕር ዳርቻ እንደሚደርሱ ገልጸዋል።

የቤተ ክርስቲያን የዕርዳታ ማድረግ ምስክር

ቤተ ክርስቲያን ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያዊዎች ያላትን ዘላቂ ቁርጠኝነት ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን የወደብ ከተማ ወደ ሆነች ላምፔዱሳ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት በመጥቀስ፥ ወደ ሥፍራው ሲደርሱ በባሕር ላይ ጉዞ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞችን በጸሎታቸው አስታውሰው የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸው ከፍተኛ የርህራሄ እና የአጋርነት ምልክት እንደ ነበር ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት በተጨማሪም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላምፔዱሳ ለማድረግ ያቀዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከስደተኞች ጎን ቆማ በዓለም አቀፍ መድረክ ክብራቸውን የመጠበቅ ተልዕኮዋን የሚያስቀጥሉበት እንደሆነ አስረድተዋል።

ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበ ጥሪ

ብጹዓን ጳጳሳቱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን በመጥቀስ፥ የበለጸጉ አገራት ለደኅንነታቸው ሲሉ እና ኑሮአቸውን ለማሻሻል ፈልገው የሚሰደዱ ሰዎችን በክብር የመቀበል የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው (CCC 2241) በድጋሚ ተናግረው፥ ለአብሮነት፣ ለፍትህ እና ለኃላፊነት አዲስ ዓለም አቀፋዊ ቁርጠኝነት እንዲደረግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

እንደዚሁም ድህነትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ግጭትን፣ የአካባቢ መራቆትን እና የወጣቶች የወደፊት ዕድል መጨለምን ጨምሮ የስደት ዋና መንስኤዎችን የመፍታት አስቸኳይ አስፈላጊነትን ተናግረው፥ እነዚህን ጉዳዮች ችላ ማለት ቀውሱን የበለጠ ያባብሰዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት የሰብዓዊነት እና የሥልጣኔ ትክክለኛ መለኪያው፥ ማኅበረሰቡ እጅግ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን የሚይዝበት መንገድ እንደሆነ በመልዕክታቸው ላይ በማረጋገጥ፥ የስደት ቀውስን ለመፍታት የጋራ ውይይት፣ ምሕረት እና ጥበብ እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ ጥሪያቸውን አጠቃልለዋል።

በመጨረሻም፥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ውሳኔ ሰጪዎችን በሙሉ ለልዑል እግዚአብሔር ምሕረት እና መሪነት አደራ በመስጠት፥ መከራው ተወግዶ በርኅራኄ ብዛት የሰው ልጅ ክብር ዘወትር እንዲጠበቅ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

23 May 2026, 11:23