ፈልግ

የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የዩክሬን ተልዕኮ የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የዩክሬን ተልዕኮ 

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የዩክሬን ተልዕኮአቸውን በመጀመር ጦርነቱ እንዲቆም ጸሎት አቀረቡ

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (CEI) ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ በዩክሬይን ሊቪቭ ክልል በሚገኘው በዛኪድ-1 ማረሚያ ቤት ማዕከል የሚያደርጉትን የአራት ቀናት ጉብኝት ጀምረዋል። ብጹዕነታቸው በዚያም ለሩሲያ ጦር ሲታገሉ ተይዘው ከታሰሩት የሠራዊቱ አባላት ጋር ተገናኝተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ የተላከላቸውን ስጦታ እና መልዕክት ካደረሱ በኋላ ቅዱስነታቸው እንደሚጸልዩላቸው እና በቅርቡ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬይን በሊቪቭ ክልል በሚገኘው ዛኪድ-1 የማረሚያ ቤት ማዕከል ውስጥ ለሚገኙት ታራሚዎች ሦስት ስጦታዎችን ያመጡት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ማሪያ ዙፒ፥ ስጦታውም “በቅርቡ የቤታቸውን በር መክፈቻ ቁልፍን የሚያስቀምጡበት፥ በዚህም ዋና በራቸውን ከፍተው ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንዲገናኙ” የሚል ተስፋ ያለው የቁልፍ መያዣ ሰንሰለት፣ ለክርስቲያኖች የእመቤታችን ምስል ያለበት፣ ለሌሎች በሙሉ የተስፋ ምልክት ያለበት የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ እመቤታችን ማርያም ካርድ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጦርነቱ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን እየጸለዩ መሆኑን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ያለበት እንደሆነ ታውቋል።

ጉብኝቱ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በጦርነቱ ወቅት ወደ ዩክሬን የሄዱበትን የመጀመሪያ ጉዞ ሁለተኛ ተልዕኮ የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል። በመጀመሪያ ጉዞአቸው በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ ጥያቄ መሠረት በሰኔ ወር 2023 ዓ. ም. ወደ ሞስኮ፣ ዋሽንግተን እና ቤጂንግ ከመሄዳቸው በፊት በኪየቭ ከፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እና ከሌሎች የፖለቲካ እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ያደረጓቸውን ስብሰባዎች ያካትታል። ይህ የሰብዓዊነት ተልዕኮ በግዳጅ የተወሰዱ የዩክሬን ህጻናትን ለመመለስ፣ የእስረኞች ልውውጥን ለማመቻቸት እና በውጊያው ወቅት የሞቱ ወታደሮችን ወደ አገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚና እና ድጋፍ ለማሳየት የተደረገ እንደ ነበር ይታወሳል።

ከሐዋርያዊ እንደራሴ እና ከዩክሬን አምባሳደር ጋር ያደረጉት ጉብኝት

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ኪየቭ ከመጓዛቸው በፊት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ እና በቅድስት መንበር የዩክሬን አምባሳደር አንድሪ ዩራሽ ጋር ሆነው የታራሚዎችን የመኖሪያ ክፍሎች፣ ጸሎት ቤት እና ክሊኒክን ጎብኝተዋል። አምባሳደር ዩራሽ እንደተናገሩት ተቋሙ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟላ እና ታራሚዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ማጣራት ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

አቬኒየር የተሰኘ የጣሊያን ጋዜጣ በዝርዝር ዘገባው፥ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ከ50 በላይ አገራት የመጡ በደርዘን ከሚቆጠሩ እስረኞች ጋር ሰላምታ መለዋወጣቸውን፥ በፈረንሳይኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ሲያነጋግሯቸው እና ታሪኮቻቸውን በአጭሩ ሲያዳምጡ እንደ ነበር ይተርካል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ፥ በጦርነቱ ወቅት እግሩን ላጣ የ25 ዓመት እስረኛ ስጋታቸውን ገልጸው፥ በቅርቡም የሰው ሠራሽ አካል እንደሚሰጠው ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ጦርነቱ እንዲቆም ዘወትር ይጸልያሉ

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የጉብኝታቸውን ዓላማ ለታራሚዎቹ ሲናገሩ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተስፋን እንድናመጣላችሁ እኔን እና ሐዋርያዊ እንደራሴውን ልከውናል” ካሉ በኋላ ጦርነቱ ቆሞ እስረኞች ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ይጸልያሉ” ብለዋል።

ስጦታዎችን ለታራሚዎች በግል በሰጧቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በቅርቡ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ የወደፊት ሕይወትን በተስፋ እንዲመለከቱ አሳስበው፥ “ጦርነቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንዲያበቃ አጥብቀን እንጸልያለን” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በጸሎታቸው ማጠቃለያ፥ ወደ ቤቶቻችሁ የምትመለሱበት መንገድ በቅርቡ እንዲገኝ፣ ጦርነቱ እንዲያበቃ እና አዲስ ሕይወት እንዲጀመር እንጸልይ” ብለው፥ ክፉ የሆነውን ሁሉ ከልብ ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበው፥ “እግዚአብሔር ዘወትር ተስፋን በመስጠት ክፋትን ዘወትር እንድናሸንፈው ይረዳናል” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

15 Jul 2026, 17:02