በፓኪስታን በሃይማኖቶች መካከል የሚወሰደው ገንቢ እርምጃ በክርስቲያን ቤተሰብ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ይከላከላል ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የፓኪስታን ትልቋ ከተማ በሆነችው ካራቺ ቁራንን አርክሰዋል የሚል ሃሰተኛ ውንጀላን ተከትሎ በተከሰተው ውጥረት እና ጥቃት ከአካባቢው ባለስልጣናት፣ ከሙስሊም የሃይማኖት መሪዎች፣ ከእስልምና የትምህርት ማህበራት የተውጣጡ ተማሪዎች እና የማህበረሰቡ አባላት ባደረጉት ፈጣን ጣልቃ ገብነት በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያን ቤተሰቦች ላይ ሊፈጸም የነበረውን ጥቃት መከላከል እንደቻሉ ተነግሯል።
በፓኪስታን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰላም እና የፍትህ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ናኢም ዩሳፍ ጊል ጉዳዩን አስመልክተው ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. በባልዲያ ከተማ ተከስቶ ለነበረው ውጥረት የተሰጠው ወቅታዊ የሆነ እርምጃ እና በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ትብብር ሊከሰት የነበረውን አስከፊ አደጋን ለመከላከል እንዴት እንደቻሉ በመጥቀስ፥ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ በፓኪስታን የሚገኙ ክርስቲያኖች ‘የሃይማኖታችንን ክብር የሚነካ ንግግር ወይም ድርጊት ፈጽመዋል’ የሚል ክስ በሚነሳበት ጊዜ ሁሉ ለጥቃት ተጋላጭ የመሆን ስሜት እንደሚሰማቸው አስጠንቅቀዋል።
አቶ ጊል እንደተናገሩት የብጥብጡ መነሻ “አንድ ሰው ከቅዱስ ቁርዓን ላይ የተቀደደ ገጽ በአካባቢው ለሚገኝ የሱቅ ባለቤት በፖስታ መላኩን” ሪፖርቶች እንደሚያሳዩ ጠቁመው፥ ይህ ከቁራን የተቀደደ ገጽ ክርስቲያን የሆኑ እና በባልዲያ ከተማ ቃዛፊ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ነዋሪ የሆኑ አዚም ጃቬድ የተባለ ሰው እና የእናቱን ፎቶግራፎች ይዟል መባሉን አመላክተው፥ ይህ ፖስታ ከመድረሱ አፍታም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች የአዚምን መኖሪያ ቤት መክበባቸውን አስረድተዋል።
ሁኔታው በቁጥጥር ስር የዋለው ‘መንግስትና አስተዳደሩ በወቅቱ እርምጃ በመውሰድ ፖሊስ ጥልቅ ምርመራ እንደሚያደርግና ወንጀለኞቹን እንደሚከታተል’ በማረጋገጡ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ጊል፥ በዚህም ምክንያት አመጹ በጊዜ መቆሙን ተናግረዋል።
የአንድነት ማሳያ
አቶ ጊል አክለውም እነዚህን ክርስቲያን ቤተሰቦች ከጥቃት ለመጠበቅ የሙስሊም የሃይማኖት መሪዎች፣ የእስልምና መንፈሳዊ ትምህርት ተማሪዎች እና የአካባቢ ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት ያልተጠበቀ እንደነበር ገልጸው፥ በዚህም ተግባር በጣም መደሰታቸው እና መደነቃቸውን ጠቁመው፥ “ይህ ክስተት በማህበረሰቦች መካከል መልካም ግንኙነት ለመገንባት ቀስ በቀስ መንገድ ይከፍታል” በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።“በባልዲያ ከተማ የተከሰቱት ክስተቶች በችግር ጊዜ የቆራጥ አመራር አስፈላጊነትን ያጎላሉ” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በፓኪስታን ከዚህ ቀደም የተፈጸሙትን በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠሩ የጥቃት ድርጊቶችን በመጥቀስ አስተዳደሩ እና የሃይማኖት ተቋማቱ አመራሮች በጥበብ እና በብልሃት እርምጃ ከወሰዱ በጃራንዋላ እና ጎጅራ የተከሰቱ ግጭቶችን ማስወገድ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ጥንቃቄ የተሞላበት ግምገማ
ይህ ክስተት ሰላማዊው ውጤት ቢኖረውም፣ ለህግ የበላይነት ካለው አመለካከት አንጻር ሰፊ የለውጥ ማሳያ አድርጎ ከመተርጎም እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀው፥ እሁን በተወሰደው እርምጃ ብቻ የሕግ የበላይነት እየጠነከረ መጥቷል ተብሎ መናገር እንደማይቻል እና አሁንም ብዙ እንደሚቀር ያሳሰቡ ሲሆን፥ በአከባቢው የሚገኙ ክርስቲያን ማህበረሰቦች ሃሰተኛ ክሶች በሚነሱበት ጊዜ ሁሉ በጣም እንደሚጨነቁ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
በፓኪስታን ውስጥ የክርስቲያን ማህበረሰቦች በተደጋጋሚ በሚደርሱ ክስተቶች ምክንያት የጥበቃ ማጣት እና ተጋላጭነት ስሜት እንደሚሰማቸው የጠቆሙት አቶ ጊል፥ ክሱ የቀረበው በአንድ ሰው ላይ ቢሆንም ተከሳሹ ክርስቲያን ከሆነ መላው ማህበረሰብ ዋጋውን እንደሚከፍል አስረድተው፥ የማህበረሰቡን እምነት ወደነበረበት ለመመለስ ጊዜ እንደሚወስድ አመላክተዋል።
የግንኙነቶች ዋጋ
አቶ ጊል አክለውም የካቶሊክ የሰላም እና የፍትህ ኮሚሽን በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ስላለው በፍጥነት ምላሽ መስጠት እንደቻለ ያብራሩ ሲሆን፥ ጥቃት ሊፈጸምበት ከነበረው ቤተሰብ አከባቢ የሚኖር የቀድሞ ሰራተኛ ለኮሚሽኑ አስተባባሪ ጥቆማ እንደሰጠ አስታውሰው፥ ይሄንን ጥቆማ ተከትሎ የኮሚሽኑ አስተባባሪ ወዲያውኑ ምክትል አፈ ጉባኤውን ናቪድን ጨምሮ ከአካባቢው ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ከሌሎች ባለስልጣናት እና ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው የሃይማኖት አባቶች ጋር ግንኙነት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ለበርካታ ዓመታት በዚያ አካባቢ ስለ ሃይማኖት አንድነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ሲሰጥ እንደነበር እና ከአብዛኛዎቹ ማህበረሰቦች ጋር ጥሩ ትስስር መፍጠሩን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፥ ይህ ተነሳሽነት የክርስቲያን ማህበረሰብን ለመጠበቅ በርካታ መልካም ሰዎችን በማነቃቃት ረገድ ጥሩ ሚና መጫወቱን አስረድተው፥ ክስተቱ በእምነት ማህበረሰቦች መካከል የውይይት አስፈላጊነትን የሚያሳይ ተጨባጭ ምሳሌ እንደሆነ ያስታወሱ ሲሆን፥ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ውይይት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመው፥ ይህ ውይይት በርካታ እንቅፋቶችን ስለሚያስወግድ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ሊመጣ የሚችለውን ግጭት መከላከል
ወደፊት ሃይማኖታችንን አዋርደዋል የሚሉ ሃሰተኛ ክሶች ወደ ለየለት ግጭት እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል በህዝቡ ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር ጥሪ ያቀረቡት አቶ ጊል፥ መንግስት በሁሉም መንገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ መጀመር እንዳለበት ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ዘመቻ በፍፁም እንዳልተጀመረ ገልጸዋል።
በመማሪያ መጽሐፍት፣ በቴሌቪዥን ድራማዎች፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች እና አጫጭር መልዕክቶች አማካኝነት ሰዎች እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ በጥበብ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው ማስተማር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፥ በካራቺ የተደረገውን ሰላማዊ መፍትሄ በጥሩ ጎኑ እንደሚቀበሉ ገልጸው፥ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ በፓኪስታን ውስጥ በርካታ ክርስቲያኖች መድልዎ እንደሚደርስባቸው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አስታውሰዋል።
“በፓኪስታን ውስጥ ያሉ ካቶሊካዊያን አስቸጋሪ ሕይወት እየኖሩ ነው” ያሉት አቶ ጊል፥ በሁሉም የሕይወት ዘርፎቻቸው መድልዎ፣ ውርደት እና ጥላቻ እያጋጠማቸው እንደሆነና አሁንም ድረስ በክብር ለመኖር እየታገሉ እንደሆነ አስታውሰው፥ አሁን የተፈጠረው ክስተት ተስፋ የሚሰጥ ነገር መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በመጨረሻም "ይህ ክስተት የተከሰተው በሲንዲ ግዛት እንደሆነ እና ሲንዲ ከፑንጃብ የበለጠ ታጋሽ የሆነ ማህበረሰብ እንደሚገኝባት ጠቁመው፥ “ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ በክርስቲያኖች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በፑንጃብ ክልል የደረሱ ናቸው” በማለት አጠቃለዋል።