ፈልግ

የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች እህቶች እና ዶ/ር አናቤል ኢንግ በክላረንስ ሃውስ ከግርማዊት ንግሥት ካሚላ ጋር የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች እህቶች እና ዶ/ር አናቤል ኢንግ በክላረንስ ሃውስ ከግርማዊት ንግሥት ካሚላ ጋር   (© BuckinghamPalace)

ንግሥት ካሚላ ከዓለም አቀፍ የገዳማዊያት የበላይ አለቆች ተወካዮች ጋር ተገናኝተው መምከራቸው ተነገረ

የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት (UISG) ተወካዮች ከዩናይትድ ኪንግደም ንግሥት ካሚላ ጋር የንጉሳዊያኑ መኖሪያ በሆነው በክላረንስ ሀውስ ከተገናኙ በኋላ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ እህቶች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በግጭት ቀጠናዎች እና በአየር ንብረት ለውጥ በተጎዱ ማህበረሰቦች ውስጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ለመጠበቅ እየሰሩ ያሉትን በርካታ ሥራዎች ማካፈላቸው ተነግሯል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ እና ንግሥት ካሚላ ከዚህን በፊት ወደ ቅድስት መንበር ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ወቅት ከዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ተወካዮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የህብረቱ ተወካዮች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ወደ ለንደን በማቅናት በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ተጋላጭ ከሆኑ ማህበረሰቦች መካከል በመገኘት በሚያከናውኑት ተልዕኮ ወቅት ያጋጠሟቸውን ታሪኮች ለንጉሳዊ ቤተሰቡ ማካፈላቸው ተነግሯል።

የበላይ አለቆቹ ተወካዮች ረቡዕ ዕለት በነበራቸው የመጀመሪያ ቀን ቆይታቸው በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አህጉራት የሚያገለግሉት የካቶሊክ እህቶች የሚያከናውኑትን ሥራዎች በተለይም በግጭት፣ በሰዎች ዝውውር፣ በድህነት እና እየተባባሰ በመጣው በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት የተጎዱ ሴቶችንና ልጃገረዶችን ለመጠበቅ ያላቸው ቁርጠኝነት ለማብራራት ዕድል እንዳገኙ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪም የሰው ልጅ ክብርን እና የመቋቋም አቅምን የሚያጎለብቱ ተነሳሽነቶችን በመደገፍ ረገድ በዓለም አቀፍ የሴት ሃይማኖታዊ ማህበራት ህብረት እና በቅድስት መንበር የብሪታንያ ኤምባሲ መካከል ያለውን ቀጣይነት ያለው ትብብር በአጽንዖት የገለጹ ሲሆን፥በቅድስት መንበር የብሪታንያ ኤምባሲ ጊዜያዊ ሃላፊ የሆኑት ዶክተር አናቤል ኢንግ ስብሰባውን አስመልክተው እንደተናገሩት ‘ውይይቱ እጅግ ልዩ እና አስደሳች ክስተት’ እንደነበር ገልጸው፥ ግብዣው ንግሥት ካሚላ የገዳማዊያት ማህበራት እየሰሩ ላለው ሥራ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“እህቶቹ በዚህ ፍጥነት የንጉሳዊያን ቤተሰቡ መኖሪያ ወደሆነው ክላረንስ ሃውስ እንደሚጋበዙ ማንም የጠበቀው አይመስለኝም” ያሉት ዶክተር አናቤል፥ ‘ይህ ግንኙነት ንግሥቲቱ ለእነዚህ ሃይማኖታዊ እህቶች ሥራ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት በግልጽ ያሳያል’ ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ጋር በቅርበት ሲሰሩ የነበሩት ዶክተር አናቤል የእህቶቹን ረጋ ያለ፣ ነገር ግን ደፋር የሆነ የምስክርነት አገልግሎት ማድነቃቸውን ገልጸው፥ ‘ይህ ሥራ አብዛኛውን ጊዜ በጸጥታ፣ ያለ አላስፈላጊ ወሬ እና ትዕይንት በታላቅ ትሕትና በዓለም ላይ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች እንደሚከናወን በግልጽ መታዘባቸውን’ ያመላከቱ ሲሆን፥ የገዳማዊያቱን አገልግሎት ልዩ ከሚያደርጉት ባህሪያት መካከል በአካባቢው ማህበረሰቦች ውስጥ ‘መተማመንን፣ በአካል መገኘትን እና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት’ መሆኑን ጠቅሰው፥ ገዳማዊያቱ ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር በጥልቅ የተዋሃዱ መሆናቸውን እና ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ እንኳን አከባቢውን ለቀው እንደማይወጡ፣ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ለከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋልጡ አስረድተዋል።

ትንቢታዊ መገኘት
የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ዋና ጸሐፊ የሆኑት እህት ሮክሳን ሻሬስ ስብሰባው በጦርነት፣ በመፈናቀልና በችግር ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር አብረው ስለሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ገዳማዊያት እህቶች ለመናገር እድል መስጠቱን ጠቁመው፥ “በዓለም ዙሪያ ያሉ እህቶቻችን በየትኛውም ቦታ ሕዝቡን ለማገልገል በእውነት ይገኛሉ” ያሉ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ በዩኒቨርሲቲ፣ በመዋዕለ ሕፃናት፣ በማኅበራዊ እና ሃዋሪያዊ አገልግሎት ውስጥ በመገኘታቸው ለሚሰሩበት አከባቢ ህብረተሰብ በሙሉ የመጽናኛ፣ የድጋፍና የድፍረት ምንጭ መሆናቻውን ጠቁመዋል።

በዩክሬን፣ ሊባኖስ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ከሚያገለግሉ እህቶች ጋር በቅርቡ የተደረጉ ውይይቶችን ያስታወሱት እህት ሮክሳን፥ በአከባቢው ቀጣይነት ያለው ግጭት ቢኖርም አብዛኛዎቹ ገዳማዊያት እዚያው ለመቆየት መምረጣቸውን ገልጸው፥ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዲት እህት የቦምብ ድብደባ በሚካሄድበት ወቅት የተደናገጡ ህፃናትን ወደ ምድር ቤት በመውሰድ ህፃናቱ የቦምብ ድብባውን ድምጽ እንዳይሰሙ በማሰብ ከቅዱሳት መጻሕፍት የተወሰዱ ጽሑፎችን ስታነብላቸው የነበረበት ሁኔታ በስብሰባው ወቅት በተገለጸበት ወቅት ንግሥት ካሚላ ታሪኩን በሃዘኔታ ተሞልተው ሲያዳምጡ እንደነበር አስታውሰው፥ በእነዚህ ምስክርነቶች ንግስቷ ‘በጥልቅ መነካታቸውን’ የጠቆሙ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ንግስቲቷ ‘በራሳቸው መንገድ እና በርኅራኄ በማዳመጥ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ እህቶች ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ’ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚደረገውን ትግል የሚመሩ ወጣቶች
ከዚህም በተጨማሪ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ የውይይታቸው ማዕከላዊ ሃሳብ እንደነበር የገለጹት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም የሚጥረው የዓለም አቀፉ የካቶሊክ እህቶች ትስስር የሆነው ‘ታሊታ ኩም’ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ የሆኑት እህት አቢ አቬሊኖ በበኩላቸው፥ ብዝበዛን ለመከላከል እና በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ማደራጀት የሆነውን የትስስሩን እያደገ የመጣውን ጥረት ያጋሩ ሲሆን፥ የድህረ ገጽ የቅጥር ማጭበርበሮች በተለይም ሥራ ለሚፈልጉ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ በፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋዎች አንዱ መንስኤ እንደሆነ አብራርተዋል።

ወጣቶች ለኦንላይን የማጭበርበር ተግባራት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን የጠቆሙት እህት አቢ፥ ይሄንን ተከትሎ ‘ታሊታ ኩም’ ወጣት ጎልማሶችን "በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ አምባሳደሮች" እንዲሆኑ በማሰልጠን ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተው፥ በኢስያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተው ፕሮግራሙ በቅድስት መንበር የብሪታኒያ ኤምባሲ ድጋፍ አማካይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን ጠቁመው፥ ተቋሙ ለበርካቶች ድምጽ መሆኑን እና የለውጥ ወኪል መሆኑን ገልጸዋል።

ታሊታ ኩም በስድስት ወር ፕሮግራሙ ከ18 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶችን ስለ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ብዝበዛ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ለእኩዮቻቸው እንዲያስተምሩ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ሃላፊዋ፥ በዚህ ሁኔታ ንቅናቄው እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፥ ታሊታ ኩም በአሁኑ ወቅት በ68 ብሔራዊ እና ክልላዊ ትስስሮች አማካኝነት ከ 110 በላይ በሆኑ ሃገራት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በ 2017 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ባደረገው ተሳትፎ በመከላከል፣ ጥበቃ በማድረግ፣ በትምህርት፣ በተሟጋችነት እና በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በማደራጀት ረገድ ከ 1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ዘንድ እንደደረሰ አመላክተዋል።

ከእያንዳንዱ አሃዛዊ መረጃ በስተጀርባ የሰው ልጅ ሕይወት መኖሩን በአፅንዖት የገለጹት እህት አቢ፥ ‘ከቁጥሮቹ በስተጀርባ በርካታ ታሪኮች’ መኖራቸውን ጠቁመው፥ ከሕገወጥ ዝውውር ከተረፈች በኋላ በአሁኑ ወቅት ሌሎች ወጣቶችን ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እየሰራች ስለምትገኝ አንዲት ሴት ምስክርነት በምሳሌነት አስታውሰዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ እና ሰብዓዊ ክብር
በውይይቱ ወቅት የተነሳው ሌላው ወሳኝ ጭብጥ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግዳጅ ፍልሰት እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መካከል እያደገ ስለመጣው ግንኙነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት የፍትህ፣ የሰላም እና የሥነ ፍጥረት እንክብካቤ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ የሆኑት እህት ማማሊፋር ፖሬኩ በበኩላቸው የአካባቢ መራቆት ተጋላጭ ቤተሰቦችን እንዴት የበለጠ ወደ ድህነት እንደሚገፋቸው በማስረዳት፥ ‘የአየር ንብረት ለውጥ ታሪክ ሳይሆን እውን እየተከሰተ ያለ ተግዳሮት መሆኑን’ ገልጸዋል።

በአንድ ወቅት በእርሻ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ማህበረሰቦች በአሁኑ ወቅት ለረጅም ጊዜያት ለዘለቀ ድርቅ እና ለአስከፊ የጎርፍ አደጋ መጋለጣቸውን ለአብነት ያስረዱት እህት ማማሊፋር፥ በዚህም ምክንያት ሰዎች ለመሰደድ እንደሚገደዱ፣ በስደት ሂደት ውስጥ ደግሞ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚጋለጡ የገለጹ ሲሆን፥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲከሰት ሰዎች ለባርነት እንደሚጋለጡ እና ይህም አደገኛ የሆነ ዑደት እንደሆነ አስረድተው፥ በዚህም ሴቶች፣ ልጃገረዶች እና ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛውን ዋጋ የሚከፍሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አሳስበዋል።

ይሄንን አደገኛ ዑደት ለመቋቋም በርካታ ገዳማዊያት እህቶች ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ እና ህፃናት ልጆችን በትምህርት ቤት እንዲቆዩ የሚያግዙ የመልሶ ማቋቋም አካል የሆኑ ግብርናን፣ የአካባቢ ትምህርትን እና የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን እያስፋፉ መሆኑን ጠቁመው፥ በእነዚህ ፕሮጄክቶች አማካይነት ይሄንን አስከፊ ዑደት እየተከላከሉ እንደሆነ አብራርተዋል።

ተስፋን በጋራ መገንባት
እህት ሮክሳን መጪውን ጊዜ በተስፋ በመመልከት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ለፍትሕ መጓደል ጥልቅ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፥ መንስኤዎቹን መፍታት ካልተጀመረ ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ አሳስበዋል።

የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት በአሁኑ ወቅት ለሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች በጋራ ምላሽ መስጠት የሚያስችል “ዓለም አቀፋዊ እህትማማችነት” በማለት የገለጹትን በአመራር፣ በጥብቅና እና በሲኖዶሳዊነት ረገድ የአቅም ግንባታ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በክላረንስ ሃውስ የተካሄደው ስብሰባ ይህ የጋራ ቁርጠኝነት ከቤተክርስቲያን ባሻገር ሰብዓዊ ክብርን ለመደገፍ መንግስታትን፣ ሲቪል ማህበረሰቡን እና የሃይማኖት ማህበረሰቦችን አንድ ላይ ማምጣት ያስቻለ መሆኑ ተነግሯል።

እህት አቢ በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የእያንዳንዱን ሰው ክብር ለማስጠበቅ ያቀረቡትን ጥሪ በማስተጋባት፥ “በትብብር ካልተሰራ በስተቀር አንድም ሰው ወይም ተቋም ብቻውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መዋጋት አይችልም” በማለት አጠቃለዋል።

17 Jul 2026, 14:39