ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማክሪካስ በካምፖ ማርዚዮ በሚገኘው የቅዱስ አውገስጢኖስ ባዚሊካ ብፁዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማክሪካስ በካምፖ ማርዚዮ በሚገኘው የቅዱስ አውገስጢኖስ ባዚሊካ 

ቅዱስ አውገስጢኖስ እንደሚያስተምረው ‘ቤተክርስቲያን ለሁሉም ክፍት መሆን እንደሚገባ’ ተነገረ

ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በሮም በሚገኘው የቅድስት ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ የሂፖውን ጳጳስ ቅዱስ አውገስጢኖስን ለማሰብ በተዘጋጀው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ብፁዕ ካርዲናል ሮላንዳስ ማክሪካስ ‘ቤተክርስቲያንን በጥልቅ ይወድ’ የነበረውንና እሷን በማገልገል ፈጽሞ ያልሰለቸውን፣ እንዲሁም «የጸጋ መምህር» በመባል የሚታወቀውን ቅዱስ አውገስጢኖስን መንፈሳዊ ጉዞ በማሰላሰል አስተንትኖ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ቅዱስ አውገስጢኖስ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው ይፈልጉ ነበር” ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ እርሱንም ካገኙ በኋላ፣ በጥልቅ ይወዳት ለነበረችው እና ‘ለማገልገል፣ ለመስበክ፣ ክርስቲያኖችን ለማነጽና የእምነትን እውነት ለመግለጥ’ ፈጽሞ ለማይሰለቹባት ቤተክርስቲያን ህይወታቸውን እንደ ስጦታ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

የቅድስት ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ማክሪካስ፣ በሮም በሚገኘውና በሂፖው ጳጳስ ቅዱስ አውገስጢኖስ በተሰየመው ባዚሊካ ውስጥ ነሐሴ 22 ቀን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የቅዱሱን ህይወትና ምስክርነት ያነሱ ሲሆን፥ ‘የእምነትና የውስጣዊ ህይወት መምህር’ የሆነው አውገስጢኖስ፣ እውነትን ከመፈለግ ፈጽሞ እንዳንሰለች እና በክርስቶስ እንድንገኝ ወይም እርሱ እንዲያገኘን እድል መስጠት እንደሚገባን ያስተምረናል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ እንደተናገሩት እርሱን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፣ “የእግዚአብሔር ቃል የሚሰማበት፣” “ቅዱስ ቁርባን በእምነት የሚከበርበት፣” “ድሆች በደስታ የሚስተናገዱበት” እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው እንደተፈለገና እንደተወደደ ሊሰማው የሚችልበት “ቤት፣ ማኅበረሰብ እና ቤተሰብ መሆን የምትችል ቤተ ክርስቲያንን” ከእግዚአብሔር ልንለምን ይገባል ብለዋል።

ቅዱስ አውገስጢኖስ አስተምህሮ የምትመስል ቤተክርስቲያን
በበዓሉ ላይ የቅዱስ አውገስጢኖስ ማህበር ካህናት እና ገዳማዊያት እንዲሁም የቅዱስ አውገስጢኖስን ደንብ በሚከተሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ሴት መነኮሳት፣ ብሎም ከተለያዩ የቅዱስ አውገስጢኖስ ማህበረሰቦች እና ተቋማት ጋር ግንኙነት ያላቸው ምዕመናን የተገኙ ሲሆን፥ በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ሰዎች በቅዱስ አውገስጢኖስ ባዚሊካ የካህናት ማህበረሰብ የበላይ አለቃ በሆኑት አባ ፓስኳል ኮርሚዮ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ ከክብረ በዓሉ አባላት መካከል ወንጌልን የሰበኩት የሐዋሪያዊ ቤተ መቅደስ ጠባቂ አባ ብሩኖ ሲልቬስትሪኒ እንደሚገኙበት ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናል ማክሪካስ በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን በወንጌል እና በሌሎች የዕለቱ ምንባባት ላይ በማሰላሰል እነዚህ ምንባባት በአንድ ላይ የታላቁን የቤተክርስቲያን አባት ‘መንፈሳዊ ምስል’ እንደሚያሳዩ በመግለጽ፥ የመጀመሪያው የክርስቲያን ማህበረሰብ «በእግዚአብሔር ቃል፣ በቅዱስ ቁርባን፣ በወንድማማችነት እና በጸሎት የምትኖር ቤተክርስቲያን» ተብሎ የቀረበበት የሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍ የቅዱስ አውገስጢኖስን ታላቅ የእረኝነት ጥልቅ ግንዛቤ በሚገባ ይገልፃል ብለዋል።

ቅዱሱ ቤተክርስቲያን በጸጋ የተሰበሰበ ማህበረሰብ የሚገኝበት እንጂ እንደ መዋቅራዊ ወይም ተቋማዊ ስብስብ ብቻ አድርጎ ፈጽሞ እንደማያስብ ጠቁመው፥ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሀብቱንና ህይወቱን ማካፈል የሚያውቅ ማህበረሰብ እንደሚገኝ ይናገር እንደነበር አስታውሰዋል።

እምነትና ምክንያታዊነት
ቅዱስ አውገስጢኖስ እውነትን በመፈለግ ሂደት ውስጥ “በርካታ ጥናቶችን፣ ምርምሮችን እና ውይይቶችን ማድረጉን፥ እንዲሁም የጥርጣሬ እና የጭንቀት ቀናትን ማሳለፉን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ማክሪካስ፥ በመጨረሻም ክርስቶስን ባገኘበት ወቅት የክርስትና እውነት ማለት አንድን ሰው ማወቅ ብቻ በቂ ሳይሆን መውደድም እንደሚገባ መረዳቱን አስገንዝበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ አውገስጢኖስ እምነትን እና ምክንያታዊነትን ማዋሃዱን የገለጹት ካርዲናሉ፥ እርሱ የሚያስተምረን በእውቀትና በማስተዋል አማካይነት እግዚአብሔርን መፈለግ እንደምንችል፣ በተመሳሳይ ጊዜም በምሥጢራቱ ፊት በጉልበት ተንበርክከን ማምለክ እንደምንችል ነው ያሉ ሲሆን፥ እኛም መማርና ትሑት ሆነን መቀጠል፥ እንዲሁም እምነታችንን ሳናጎድል ጥያቄዎችን መጠየቅ እንችላለን ብለዋል።

ክርስቶስ መልካም እረኛ፣ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት መሆኑ  
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ መልካም እረኛ እና ጠባቂ አድርጎ የሚያቀርበው የዮሐንስ ወንጌል፣ የሂፖው ጳጳስ ቅዱስ አጎስጢኖስ በመጨረሻ ከደረሱበት መድረሻ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ያመላከቱት የጳጳሳዊ ባዚሊካ ዋና ካህን፥ በርካታ መንገዶችን ከመረመሩ፣ ብዙ ድምፆችን ካዳመጡ እንዲሁም የባህልን፣ የፍልስፍናንና የሰው ልጅ ምኞቶችን ማራኪነት ከተለማመዱ በኋላ መልካሙ እና እውነተኛው እረኛ የሆነው ክርስቶስ ለልባቸው ሊሰጥ ከሚችለው ነገር ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ዓይነት ድምፅ እንደሌለ መረዳታቸውን አስረድተዋል።

ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት እና እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ወደ ክርስቶስ ሊያመለክቱ እንደሚገባ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ማክሪካስ፥ እነዚህ ሰዎች እውነተኛ አገልጋዮች የሚሆኑት ከክርስቶስ ጋር ተባብረው ሲቆዩ እና ሰዎችን ወደ ራሳቸው ሳይሆን ወደ እርሱ ሲመሩ እንደሆነ ጠቁመው፥ ቤተክርስቲያን ራሳቸውን የሚፈልጉ እረኞችን ሳይሆን፣ ይልቁንም ወደ በሩ የሚያመለክቱ እና ክርስቶስ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት እንደሆነ በራሳቸው ሕይወት አማካኝነት በተግባር የሚያሳዩ ሰዎች ያስፈልጓታል ብለዋል።

ከእረፍት ማጣት ወደ እግዚአብሔር
የአውገስጢኖስ ጉዞ የሚያስተምረን “እረፍት ማጣት፣ ስህተቶች፣ ጥያቄዎች እና ተቃውሞዎቻችን እንኳን ሳይቀር እግዚአብሔር እኛን ፍለጋ የሚመጣባቸው መንገዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ያሉት ካርዲናሉ፥ የሂፖው ጳጳስ “እረፍታቸውን በእግዚአብሔር” እስኪያገኙ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የእረፍት ማጣት ስሜት ይሰማቸው እንደነበር፥ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በቃላት፣ በምስሎች፣ በአመለካከቶች እና በድምፆች በተሞላው የዛሬው ማህበረሰብ ውስጥ፥ በብዙ ነገሮች በመከፋፈላችን የተነሳ የመልካሙን እረኛ ድምፅ ያለመለየት አደጋ ውስጥ ልንወድቅ ይችላል ያሉ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት፣ ምዕመናን ልቦቻቸው በእግዚአብሔር እስኪያርፉ ድረስ እረፍት እንዳያገኙ፤ እንዲሁም እርሱን ወደ ክርስቶስ የመራውን መንፈሳዊ ጉዞ ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት ቅዱስ አውገስጢኖስን እንዲጠይቁ ጋብዘዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅርቡ ለቪላኖቫው ቅዱስ ቶማስ የአውገስጢኖሳዊያን አውራጃ አባላት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ፣ ይሄንን የቅዱስ አውገስጢኖስ የሕይወት ጉዞ ገጽታ አጉልተው በማሳየት፥ ‘ቅዱሱ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ በእናቱ በሞኒካ ጸሎት እና በዙሪያው በነበሩት መልካም ሰዎች አማካኝነት ለተረበሸው ልቡ የሰላምን መንገድ ማግኘት ችሎ ነበር’ ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ማክሪካስ በመጨረሻም ምዕመናን ወደ ቅዱስ አውገስጢኖስ በመመልከት እንደ መኖሪያ ቤት፣ እንደ ማኅበረሰብ እና እንደ ቤተሰብ መሆን የምትችል ቤተ ክርስቲያን እንዲኖራቸው እግዚያብሔርን እንዲለምኑ ያበረታቱ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው የበዓሉ ማጠቃለያ ላይ፣ የሂፖው ጳጳስ ቅዱስ አውገስጢኖስ ለሰላም በሚደረገው ጥረት እና “የእግዚአብሔርን ከተማ” በመገንባት ሂደት ውስጥ የሰው ልጆችን እንዲያጅቡ ምዕመናኑን በመምራት ጸሎት አድርሰዋል።

31 Aug 2026, 14:38