ፈልግ

የኡሳምባራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል እህቶች የኡሳምባራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል እህቶች 

የታንዛኒያ ገዳማዊያት እህቶች በቴሌቪዥን እና በማህበራዊ ሚዲያ ወንጌልን እየሰበኩ እንደሚገኝ ተገለጸ

ቴክኖሎጂ እና የእርስ በርስ ግንኙነት እየተሻሻሉ በሄዱበት በአሁኑ ወቅት በታንዛኒያ የሚገኘው የኡሳምባራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እህቶች ጉባኤ አባላት የሚዲያ መድረክን የወንጌል አገልግሎት መሣሪያ አድርገው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀሙበት እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ እህቶቹ በቴሌቪዥን እና በማህበራዊ አውታረ መረቦች ወንጌልን ለማካፈል፣ ወጣቶችን ለማሳተፍ እና ስለ ካቶሊክ እምነት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ 1954 ዓ.ም. የሮዝሚኒያ አባቶች ማህበር አባል በሆኑት ሞንሲኞር ዩገን አርተርስ የተመሰረተው የኡሳምባራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እህቶች ጉባኤ በወንጌላዊነት እና በትምህርት ላይ የተመሰረተ የሀገረ ስብከት ጉባኤ ሲሆን፥ በ 1958 ዓ.ም. ሞንሲኞር አርተርስ የመጀመሪያው የታንጋ ካቶሊክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው መሾማቸው እና እህቶቹ ደግሞ መጀመሪያ የተቋቋሙት በክቡር ደም ሚስዮናዊያን እህቶች ማህበር አማካይነት እንደሆነ፥ እንዲሁም የመጀመሪያዋ የበላይ ኃላፊያቸው እህት ዊሊባልዳ ጂስበርስ እንደነበሩ ተገልጿል።

የጉባኤው አባላት ተልዕኮአቸውን በራንግዊ ጀምረው በኋላም በታንጋ ክልል ውስጥ በሚገኘውው ኮሮግዌ ከተማ፣ በመቀጠልም ወደ ክዋምዶልዋ የተዛወሩ ሲሆን፤ ራንግዊ ያለው መኖሪያ ቤታቸው የመጀመሪያው ዋና ቤታቸው ሆኖ መቆየቱን፥ ከጊዜ በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ኮሌጅ ድረስ በሁሉም ደረጃዎች በሚገኝ የትምህርት ዘርፍ ላይ፣ እንዲሁም የሃይማኖት ትምህርት እና የወጣቶች ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገልጿል።

ለወንጌል ስርጭት አዲስ መንገድ
ገዳማዊያን እህቶቹ ለጊዜው ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምላሽ ለመስጠት በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ሰዎችን መድረስ አስፈላጊ መሆኑን የተገነዘቡ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በ 2016 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ላይ በታንጋ ክልል ሉሾቶ ከተማ ኡሳምባራ ማውንቴን ቲቪ (UMTV) የተሰኘ የሚዲያ ተቋም መቋቋሙ ተነግሯል።ይህ ተነሳሽነት በእምነት ጉዳዮች ላይ ወንጌልን የመስበክ፣ የትምህርት እና የውይይት አገልግሎትን የሚደግፍ ይዘት ለማቅረብ ያለመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን በማስመልከት የኡሳምባራ ማውንቴን ቲቪ ዳይሬክተር የሆኑት እህት ፓውሊና ምሻና እንደተናገሩት “በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት አማካኝነት ከማህበረሰቦቻችን ርቀው የሚገኙ ሰዎችን ማግኘት ችለናል” ያሉ ሲሆን፥ ይህ ወንጌልን የማካፈል እንዲሁም ሰዎችን፣ በተለይም ወጣቶችን፣ እግዚአብሔርን ይበልጥ እንዲያውቁና እንዲወዱ የማበረታታት ተልዕኳችንን ያጠናክራል ብለዋል።

በርካታ ወጣቶች የኡሳምባራ ማውንቴን ቲቪን በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች እና በዩ ቲዩብ በኩል እንደሚከተላሉ የተነገረ ሲሆን፥ ቻናሉ በዶን ቦስኮ መንፈሳዊነት ላይ የተመሰረቱ ተነሳሽነቶችን ጨምሮ በወጣቶች፣ በእምነት እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን እንደሚያቀርብም ተነግሯል።

ይዘት እና ተደራሽነት
የኡሳምባራ ማውንቴን ቲቪ የሃይማኖት ትምህርትን፣ ስለ እምነት የሚደረጉ አስተንትኖዎችን እንዲሁም ስለ ወጣቶችና ማህበረሰብ የሚደረጉ ውይይቶችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚያሰራጭ ሲሆን፥ በእነዚህ ተነሳሽነቶች አማካኝነት፣ እህቶቹ የዕለት ተዕለት ሕይወትን ይበልጥ እየቀረጸ በመጣው የሚዲያ ዓለም ውስጥ፣ ያላቸውን ልዩ መንፈሳዊ ስጦታ እና ተልዕኮ ይበልጥ ለማጉላት እንደሚፈልጉም ተገልጿል።

ይህ መድረክ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለይም የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ተደራሽነትን ማግኘቱ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ እያደገ የመጣ ተሳትፎ፤ ትምህርትን፣ አስተንትኖን እና በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል ግንኙነትን የሚያጣምር ይዘት ለማግኘት ያለውን ፍላጎት ያንፀባርቃል ተብሏል።

እህት ፓውሊና፣ በሚዲያ ዘርፍ መሥራት ማኅበሩ በአካል መገኘት በማይችልበት ማኅበረሰቦች ዘንድ ተደራሽ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ገልጸው፥ “ምንም እንኳን በርካታ ሰዎች በካሜራ ሙያ መሥራት የወንዶች ሥራ ብቻ አድርገው ቢያስቡም በዚህ ሥራ በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ” ያሉ ሲሆን፥ ገዳማዊያት እህቶችም ይህንን ሚና ወስደው ወንጌልን ለሰፊው ማህበረሰብ ማስተላለፍ እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል።

ትብብር እና ተፅዕኖ
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ተነሳሽነት ከቤተክርስቲያኒቱ ሌሎች አባላት ጋር በመተባበርም ተጠቃሚ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ለኡሳምባራ ማውንቴን ቲቪ አስተዋፅዖ ከሚያበረክቱ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ወንድም ሉካስ ማሳሲ ፕሮጀክቱ በእምነት ላይ የተመሠረተ ይዘትን በማስተዋወቅ እና በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጥን ትምህርት በመደገፍ ረገድ ያለውን አስፈላጊነት አጉልተው በመግለጽ፥ ከቀላል የዩቲዩብ ቻናልነት በመነሳት ይበልጥ ወደተደራጀ የቴሌቪዥን መድረክ ያደገበትን ሂደት ሲከታተሉ እንደነበርም ገልጸዋል።

የቴሌቭዥን ጣቢያው በፕሮግራሞቹ አማካኝነት እንደ ባህል፣ ሙዚቃ፣ መንፈሳዊነት እና መሰረታዊ የህይወት ክህሎቶች በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ከቤት ሆነው እንኳን መከታተል የሚቻሉ ይዘቶችን በማቅረብ በአካባቢው ማህበረሰቦች ዘንድ ለትምህርት ዘርፉ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግም ጭምር ተነግሯል።

ተግዳሮቶች እና ገደቦች
እንደ በርካታ አዳዲስ ተነሳሽነቶች ሁሉ ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥመው የተነገረ ሲሆን፥ ከእነዚህም ተግዳሮቶች መካከል የመገልገያ መሳሪያዎች እና የፋይናንሻል ሀብቶች ውስንነት ዕለታዊ የስርጭት ሂደቱን ፈታኝ እንደሚያደርገው፣ በሌላ በኩል ለበርካታ ተመልካቾች አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት እጥረት እና የዲጂታል መሣሪያዎች ዋጋ መናር እንቅፋት ሆነው መቀጠላቸው ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ በቂ የመጠባበቂያ ሥርዓቶች አለመኖር የሥራ እንቅስቃሴን ስለሚያስተጓጉል የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የስርጭቶችን መደበኛነትን እንደሚያዛባ፥ እንዲሁም ሁሉም የጉባኤው አባላት ወንጌልን ለማዳረስ የሚያግዘውን የሚዲያ አስፈላጊነት በመጀመሪያ ደረጃ ባለመገንዘባቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ቀጣይነት ያለው ስልጠና እና ግንዛቤን እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

መጪውን ጊዜ መመልከት
እነዚህ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ገዳማዊያት እህቶቹ ሚዲያን ለወንጌል ስርጭት እና ምስረታ መድረክ አድርገው ለመጠቀም ቁርጠኛ ሆነው መቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን፥ የእህቶቹ ዓላማ ሰፊ ተመልካች ወይም አድማጭ ዘንድ መድረስ፣ እንዲሁም ወጣቶች ትርጉምንና እምነትን በሚፈልጉበት ሂደት ውስጥ ከዲጂታል መሣሪያዎች ጋር የበለጠ ግንዛቤ የተሞላበት ግንኙነት እንዲፈጥሩ መርዳት እንደሆነም ተነግሯል።

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10፡ ቁጥር 2 ላይ “እነሆ መከሩ ብዙ ነው፥ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ለመከሩ ሥራ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት” በሚለው የወንጌል ቃል ላይ በመነሳሳት፣ እህቶቹ በቴሌቪዥን፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና በትምህርታዊ ይዘቶች አማካኝነት ክርስቶስን የማሳወቅ ተልዕኳቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።

27 Aug 2026, 14:34