ፈልግ

የሉትስክ ጳጳስ እና የላቲን ሥርዓት ተከታይ የሆነው የዩክሬን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ቪታሊጅ የሉትስክ ጳጳስ እና የላቲን ሥርዓት ተከታይ የሆነው የዩክሬን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ቪታሊጅ  

የዩክሬን ጳጳስ ‘በሚደረግልን የአጋርነት ስሜት ውስጥ ጥንካሬንና ተስፋን እናገኛለን’ ማለታቸው ተነገረ

በዩክሬን የሉትስክ ጳጳስ እና የላቲን ሥርዓት ተከታይ ዩክሬን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ቪታሊጅ ስኮማሮቭስኪጅ ሃገሪቷ ከሶቪየት ኅብረት ነፃ ከወጣች ያለፉትን 35 ዓመታትን በማስታወስ “ዛሬ እውነተኛ የሆነ የህሊና ነፃነት አለን” ያሉ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው አክለውም ‘አሁን ያለው ጦርነት ሰላም ለማንኛውም ሀገር ምን ያህል በዋጋ የማይተመን ጠቀሜታ እንዳለው እንድገነዘብ አድርጎኛል’ ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ 

ለዩክሬን ሕዝብ እውነተኛና በተግባር የሚታይ የሃይማኖት ነፃነትን ያመጣው ከሶቪዬት ህብረት ነፃ ከተወጣ 35 ዓመታት በኋላ፣ ሀገሪቱ አሁንም ከባድ የጦርነት ፈተናን እየተጋፈጠች እንደምትገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን በማስመልከት የሉትስክ ጳጳስ እና የላቲን ሥርዓት ተከታይ የሆነው ዩክሬን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ቪታሊጅ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሃገራቸው አሁን ያለችበትን አስከፊ እውነታ እና ሕዝቡ ሀገሩን ለመጠበቅ እየከፈለ የሚገኘውን ከፍተኛ መስዋዕትነት የገለጹ ሲሆን፥ ጳጳሱ ጦርነት ታላቅ መቅሰፍት መሆኑን የገለጹትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በማስታወስ፥ ለሃገራቸው ከመላው ዓለም እየተደረገ ያለውን አስደናቂ እና ቀጣይነት ያለው የአብሮነት ሰንሰለት፣ እንዲሁም ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍ አጉልተው አሳይተዋል።

ከታሪካዊ እይታ አንጻር 35 ዓመታት በጣም ረጅም ጊዜ እንዳልሆነ የጠቀሱት ጳጳሱ፥ ነገር ግን እዚህ ዩክሬን ውስጥ ሆነው በዚህ ወቅት ያሳለፉትን ነገሮች ሲመለከቱ፣ እጅግ ረጅም እና ብዙ ክስተቶች የተከናወኑበት ጊዜ ሆኖ እንዳገኙት የጠቆሙ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 1990ዎቹ የነበረውን ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ከዚያ በኋላ ለማገገም የተደረገውን ጥረት አስታውሰው፥ አሁን ደግሞ ከ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተጨባጭ ሁኔታ በጦርነት ውስጥ እንደሚገኙ እና በ 2022 ደግሞ ወደ ሙሉ ወረራ እንደተሸጋገረ ጠቁመው፥ “ምንም እንኳን በሺህ ዓመታት ታሪካችን ውስጥ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ ለእኛ ግን እጅግ ሰፊ የሆነ ጉዞን የያዘ ነው” ብለዋል።

ነፃ መውጣት ለዩክሬናውያን መንፈሳዊ ሕይወት የነበረውን ትርጉም የተጠየቁት ጳጳሱ፥ ዛሬ ነፃ በሆነ ሀገር ውስጥ እንደሚኖሩ እና በወረቀት ላይ ብቻ የተጻፈ ሳይሆን እውነተኛ የሆነ የህሊና ነፃነት እንዳላቸው ጠቁመው፥ እያንዳንዱ ሰው እምነቱን የመግለጽ እና የመመስከር ዕድል እንዳለው የገለጹ ሲሆን፥ እንደማንኛውም ሀገር ሁሉ ቢሮክራሲያዊ ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም፣ የህሊና ነፃነት በዩክሬን ሕገ መንግሥት የተረጋገጠ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በተግባር የሚታይ እውነታ መሆኑን አስታውሰው፥ “ለእኛ፣ በተለይም ያለፈውን ስንመለከት፣ ይህ ስጦታ እጅግ አስደናቂ እና ልዩ ነው ብለዋል።

ሶቪየት ኅብረት በሕገ መንግሥቱ የህሊና ነፃነት መብትን በይፋ እውቅና ሰጥቶ የነበር ቢሆንም፤ ሆኖም ግን በተለያዩ አመለካከቶች ምክንያት ቤተ ክርስቲያን እና ሃይማኖት ስልታዊ በሆነ መንገድ ይጨቆኑ እንደነበር ያስታወሱት ጳጳሱ፥ አንዳንድ ጊዜ ይህ ጭቆና እጅግ አረመኔያዊ እንደነበር፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ በተዘዋዋሪ ወይም በስውር መንገድ ይፈጸም እንደነበር ጠቁመው፥ አማኞች ይታሰሩ እንደነበር፤ አንዳንዶቹም ስለ እምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፤ ሌሎች ደግሞ ምንም ዓይነት የእድገት ዕድል እንዳያገኙ ይደረግ እንደነበር፤ ማለትም መምህር ወይም ሐኪም መሆን ወይም የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎችን መያዝ እንደማይቻል እና ያ ወቅት እውነተኛ ፈተና የሞላበት ጊዜ እንደነበር ገልጸዋል።

በቀድሞዎቹ የዛሪያን አገዛዝ ዘመን እንኳን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወይም በወቅቱ የንጉሠ ነገሥታዊት ሥርዓት የሚከተለው ሩሲያ የመንግሥት ቤተ ክርስቲያን የነበረችው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ገደቦች ይገጥሟቸው እንደነበር ያስታወሱት ጳጳሱ፥ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተልዕኮዋን በነፃነት እንዳታከናውን በሚያግደው እና የመታፈን ስሜት በሚፈጥር ሁኔታ ውስጥ ተይዛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ በመሆኑም ምክንያት እነዚህ የ35 ዓመታት የሰብዓዊ እና የሃይማኖት ነፃነት ጊዜያት ለሃገራቸው እጅግ ልዩ የሆነ ተሞክሮ መሆኑን ጠቅሰው፥ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ፈተናዎች እና ከዚህ በፊት ታይተው የማያወቁ ችግሮች ቢያጋጥሟትም፤ ነገር ግን የነፃነት ቀንን በሚያከብሩበት ወቅት ሁሉ፣ ማኅበረሰቡ በዋጋ ለማይተመነው የነፃነት ስጦታ እግዚያብሔርን እንደሚያነሰግን ገልጸዋል።

ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው፣ በጭቆና ዘመናት ሰዎች በመከራ ስለሚፈተኑ እምነታቸው ጠንካራ እንደሚሆና በአንጻሩ ደግሞ፣ ዛሬ አብያተ ክርስቲያናት ክፍት በሆኑበት እና ሰዎች ወንጌልን በነፃነት በሚሰብኩበት ወቅት፣ እምነት የተዳከመ የሚመስልበትን ምክንያት የተጠየቁት ብፁዕ አቡነ ቪታሊጅ፥ ትልቁ እውነታ ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ መለወጡን ጠቁመው፥ ቀደም ሲል በነበሩት የጭቆና ዘመናት፣ በሥራ ቦታ ላይ ሊደርስባቸው የሚችለውን የበቀል እርምጃ በመፍራት በርካታ ሰዎች ልጆቻቸውን ለማስጠመቅ ይፈሩ እንደነበር አስታውሰው፥ ዛሬ ግን፣ በእርግጠኝነት እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ማንም እንደማይከለክል አስረድተዋል።

ሆኖም፣ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ለሌሎች እና ለእግዚአብሔር የሚሆን ጊዜን በመዘንጋት መላ ሕይወታቸውን ለሙያቸው ወይም ለቁሳዊ ደህንነታቸው በመስጠታቸው በመጨረሻም እምነትን አስፈላጊ እንዳልሆነ ነገር አድርገው የመመልከት አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቁመው፥ ከራሳቸው ተሞክሮ ላይ በመነሳት በሰጡት አንድ ምሳሌ፣ በሶቪየት ህብረት ዘመን በዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሠሩ በነበረበት ወቅት፣ መንግስት በተማሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥሮችን በመጣል ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መሰናክሎች ይፈጥር እንደነበር አስታውሰው፥ በዚህም ምክንያት፣ ተነሳሽነቱ ደካማ ወይም ስብዕናው ጠንካራ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ወደ ትምህርት ቤቱ መግባት እንደማይችል እና ቢገባም እንኳ ብዙም ሳይቆይ ይወጣ እንደነበር ገልጸዋል።

ወታደራዊ አገልግሎቱን የጨረሰ ወይም ዩኒቨርሲቲ ተምሮ የወጣ አንድ ወጣት ወደ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቱ ለመግባት ፍላጎት እንዳለው ሲታወቅ፣ አስፈሪ የሆኑ "ቃለ-መጠይቆች" ይደረጉለት እንደነበረ እና ውሳኔውን እንዲቀይር ጫና ይደረግበት እንደነበር አስታውሰው፥ ወደ ትምህርት ቤቱ መግባት ከባድ ተግባር እንደነበርና አንዳንድ ወጣቶች ይሄንን ለማሳካት እስከ አስር ዓመት ድረስ መሞከር እንደነበረባቸው አመላክተዋል።

በአንጻሩ ዛሬ እንደዚህ ዓይነት መሰናክሎች እንደሌሉ፥ ሆኖም ግን፣ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ወደ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች ለመግባት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ፣ አንዳንዴም ከሞላ ጎደል ባዶ መሆኑን ጠቁመው፥ በቅርብ ጊዜያት እንኳን ሳይቀር የሃይማኖት ትምህርት ቤቶቹን ጉዞ የጀመሩ በርካታ ወጣቶች፣ በኋላ ላይ ይህ መንገድ ለእነሱ እንዳልሆነ ሲገነዘቡ ማየታቸውን ገልጸው፥ “በአጭሩ፣ እኛ የምንኖረው ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ እና አውድ ውስጥ ነው” ብለዋል።

ለነፃነት ሲሉ ህይወታቸውን በመሰዋት ከፍተኛውን ዋጋ የከፈሉ ወንዶችና ሴቶች የቀብር ሥነ-ሥርዓቶች ላይ በመገኘት የቤተሰቦቻቸውን ሀዘን እንደሚከፈሉ የገለጹት ጳጳሱ፥ ዩክሬን ጥቃት ስለተፈጸመባት ራሷን ለመከላከል በተገደደችበት ሁኔታ ውስጥ መኖሯን ጠቁመው፥ ሃገራቸውን ለመጠበቅ የሚመርጡ ሰዎች ምን ያህሉ "ህይወታችንን እየሰጠን ነው" ብለው በግልጽ እያሰቡ እንደሚያደርጉት በእርግጠኝነት እንደማያውቁ የገለጹ ሲሆን፥ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ለመኖር እና በሕይወት ለመትረፍ ተስፋ እንደሚያደርጉ፥ ነገር ግን እንደ ወታደር፣ ለሞት የሚዳርግ አደጋ ያለበትን ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

“እንደ አለመታደል ሆኖ እነዚህ ሰዎች በጥይት እና በጠላት መሳሪያ ተመትተው ይገደላሉ” ያሉት ጳጳሱ፥ የዩክሬን ዜጎች ሃገራቸውን ለመጠበቅ እና እነሱን ተክቶ ይህንን ሊያደርግ የሚችል ሌላ አካል ስለሌለ ወደ ጦርነቱ ለመግባት እንደሚገደዱ አመላክተው፥ ይህ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የሚከብደን እጅግ ታላቅ ዋጋ ነው ብለዋል።

“እኛ "የአባቶች ምድር" ብለን የምንጠራውን ይሄንን የጋራ መኖሪያችንና የጋራ ቤታችንን ጠላት መስኮቶችን በኃይል ከፍቶና በሮችን ሰብሮ ሲገባ፣ ማንኛውም ሰው ቤተሰቡንና የሚወዳቸውን ሰዎች ለመከላከል ይነሳል” ያሉት ጳጳሱ፥ ጉዳዩ የጋራ ቤታቸው እና ሁሉንም ዩክሬናውያን የሚያስተሳስር ጉዳይ በመሆኑ፥ ሁሉም ዩክሬናውያን ምድራቸውን ለመጠበቅ መነሳታቸውን አመላክተዋል።

የሚከፈለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም በህዝቡ ላይ የተጋረጠው አደጋም ጭምር በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ እንደሆነ፥ የሩሲያ ሃይል ወደ ይክሬን የገባው የተለየ የፖለቲካ ሥርዓት ለመጫን ወይም አዲስ የምርጫ ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ ለመግደልና ለማውደም ጭምር እንደሆነ ገልጸው፥ ዩክሬን ራሷን ለመከላከል የተገደደችው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት ስለ ጦርነት ከነበራቸው አስተሳሰብ፣ ማለትም መጻሕፍትን በማንበብ፣ ፊልሞችን በመመልከት ወይም በሌሎች የዓለም ክፍሎች ስለሚደረጉ ጦርነቶች ሪፖርቶችን በመከታተል ካዳበሩት ሀሳቦች በጣም የተለየ መሆኑን በመግለጽ ይህ ሙሉ በሙሉ አዲስ ተሞክሮ እንደሆነ የጠቆሙት ጳጳሱ፥ ጦርነት በእርግጥ እንዲህ እንደሆነ አስበው እንደማያውቁ አመላክተው፥ ይህ ሁሉ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ጦርነት ታላቅ መቅሰፍት ነው፤ እሱን ለማስወገድ ትንሽ ዕድል እንኳን ካለ፣ ያንን ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለው ከተናገሩት ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲስማሙ ማድረጉን ገልጸዋል።

“ሰላም እጅግ ታላቅ ስጦታ ነው” ያሉት ጳጳሱ፥ ጦርነት ግን በውስጡ ለተሳተፈ ወይም ለተጎዳ ማንኛውም ሰው ሊለካ የማይችል ጉዳት እንዳለው እና ሰላም እጅግ ውድ የሆነ በረከት በመሆኑ ለሰላም የሚደረግ ጸሎት ሊለካ የማይችል ዋጋ እንዳለው በጥልቀት መረዳታቸውን ገልጸው፥ ምናልባት ዋጋውን በግልጽ የምንረዳው ሰላም ሲጠፋ መሆኑን፥ እንዲሁም ህጻናት፣ አረጋውያን፣ ደካሞች እና ጠንካራዎችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ለአደጋ ሲጋለጥ መሆኑን ጠቁመው፥ ሰላም ለአንድ ህዝብ እና ለአንድ ሀገር ምን ያህል ውድ እንደሆነ የምንረዳው በዚያን ጊዜ ነው ብለዋል።

“ሌላው ታላቅ ተሞክሮ የአብሮነት ወይም የአጋርነት ስሜት ነው” ያሉት ብፁዕ አቡነ ቪታሊጅ፥ በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ ሰዎች ለዩክሬን ህዝብ ያሳዩት ልዩ ቅርበት እና አብሮነት ትልቅ ተሞክሮ እንደሆነ ጠቁመው፥ ከቁሳዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍ ጋር ተዳምሮ ይህ አጋርነት ዘላቂ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ሰዎች ለእኛ መጸለይን እና እኛን መርዳት አይሰለቹም ብለዋል።

‘ይህ እጅግ ታላቅ ስጦታ ነው’ ያሉት ጳጳሱ፥ እንዲህ ዓይነቱ አብሮነት በግዴታ የሚሰጥ ሳይሆን፥ በቀጥታ ከልብ የሚመነጭ መሆኑን ገልጸው፥ በመጨረሻም፥ ይህ ሁሉ እጅግ በርካታ ጥንካሬ እና ተስፋ እንደሚሰጣቸው እና ይህ ጦርነት በተቻለ ፍጥነት እንዲያበቃ መጸለያቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ አጠቃለዋል።

26 Aug 2026, 14:44