ፈልግ

ፔሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወደ ደቡብ አሜሪካ leሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ዝግጅት እያደረገች ነው ፔሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወደ ደቡብ አሜሪካ leሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ዝግጅት እያደረገች ነው  (ANGELA PONCE)

በፔሩ የሚገኙ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተነገረ

ሰሞኑን ሲካሄድ የነበረው የፔሩ ብፁዓን ጳጳሳት 130ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከህዳር 2 – 8 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ በፔሩ በሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ወቅት ወደ ሃገሪቱ ለሚመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን አገልግሎት ለመስጠትና ድጋፍ ለማድረግ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶችንና ምዕመናንን ያካተተው “የር.ሊ.ጳ. ሊዮ ወዳጆች” (Friends of Leo) ተብለው የተሰየሙትን ይፋዊ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ይፋ በማድረግ መጠናቀቁ ተገልጿል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከህዳር 2 – 8 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ በፔሩ በሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ወቅት ወደ ሃገሪቱ ለሚመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን አገልግሎት ለመስጠትና ድጋፍ ለማድረግ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶችንና ምዕመናንን በማካተት የተቋቋመው ይህ ቡድን ይፋ የተደረገው የፔሩ ብፁዓን ጳጳሳት 130ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መጠናቀቅን ተከተሎ መሆኑ ተገልጿል።

የፔሩ የካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላላ ስብሰባ፣ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉብኝት ዝግጅት ላይ የሚሳተፉትን የቤተክርስቲያኒቱን እና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችን በጋራ ያሰባሰበ ሲሆን፥ በስብሰባው ወቅት ብፁዓን ጳጳሳቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተለይም ከፔሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና በቺክላዮ ከተማ በጳጳስነት ያገለገሉበትን ጊዜ በማስታወስ፣ በሃገሪቱ ለሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉዞ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ለአገልግሎት የተደረገ ጥሪ
“የር.ሊ.ጳ. ሊዮ ወዳጆች” ቡድን ክህሎታቸውንና ተሰጥዖዋቸውን ተጠቅመው በዚህ ወሳኝ በሆነ ዝግጅት ላይ አገልግሎት ለመስጠት ለሚፈልጉ ከ18 እስከ 45 ዓመት የሆኑ ሰዎች ክፍት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በጎ ፈቃደኞቹ የእንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ፣ የመረጃ ልውውጥ (ኮሙኒኬሽን)፣ የሎጂስቲክስ፣ የአደረጃጀትና የደህንነት፣ የመጀመሪያ እርዳታ እንዲሁም የትርጉም ሥራዎችን በማከናወን መርዳት ይችላሉ ተብሏል።

ይህ ተነሳሽነት “ማገልገል፣ መንከባበብ እና አብሮ መሆን” በሚል መሪ ቃል በጎ ፈቃደኞቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጉብኝታቸው ወቅት በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ ለሚሳተፉ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል የሚያደርጉ እና በቀላሉ ሊቀረቡ የሚችሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር የቡድኑ አባላት የመንፈሳዊ፣ የእረኝነት እና የአሰራር ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

በጎ ፈቃደኞቹ የሥነ-ምግባር ደንብን እንዲከተሉ እንዲሁም ጥበቃን እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን በተመለከተ የተዘረጉ መመሪያዎችን እንዲያከብሩ ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን፥ የበጎ ፈቃደኞቹ ተልዕኮ የድርጅታዊ ሚና ከመወጣት ባሻገር እንደሚሄድ፥ እንዲሁም በቅርበትና በወንድማማችነት መንፈስ መንፈሳዊ ነጋዲያኑን ለመምራት፣ ለማዳመጥ እና አብረዋቸው ለመጓዝ ጥሪ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

ለጉብኝቱ ምዝገባ እና ዝግጅቶች
የተነሳሽነቱ ማስጀመሪያ ላይ ለጉብኝቱ የተዘጋጀው ይፋዊ ድረ-ገጽ መቅረቡ እና የበጎ ፈቃደኞች ምዝገባም ቀድሞውኑ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን፥ በመቀጠልም ተሳታፊዎች ስለ ስልጠና ክፍለ-ጊዜዎች፣ ስለጉብኝቱ አካሄድ እና ስለሚወጡት ኃላፊነቶች መረጃ ያገኛሉ ተብሏል።

አዘጋጆቹ በመጪዎቹ ወራት የዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ ስለ ጉብኝቱ መርሃ ግብር ተጨማሪ እንቅስቃሴዎች እና መረጃዎች በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ መንፈሳዊ ዝግጅቱ አካል፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉብኝት የተዘጋጀው ይፋዊ ጸሎትም የቀረበ ሲሆን፥ ይህ ጸሎት በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ማህበረሰቦች እንዲደርስ በማሰብ ወደ ኩዌቹዋ፣ አይማራ እና አዋጁን ቋንቋዎች እንደሚተረጎሙ ተነግሯል።

በፔሩ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ እና በሊማ ሃገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት በጋራ በተዘጋጀ ውድድር የተመረጠውና ለጉብኝቱ የተዘጋጀው “ሊዮ፣ በጉዞ ላይ ያለ ወንድም” (Leo, Brother on the Journey) የተሰኘው ይፋዊ መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ መቅረቡ ተገልጿል።

ተስፋን ያነገበ ጉብኝት
በፔሩ የምትገኘው ቤተክርስቲያን፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ጉብኝት እምነትን ለማጠናከር፣ እንዲሁም አንድነት፣ ሰላም፣ ተስፋ እና አብሮነትን የመሳሰሉ እሴቶችን ለማስተዋወቅ እንደ መልካም አጋጣሚ አድርጋ እንደምትመለከት የተገለጸ ሲሆን፥ “የሊዮ ወዳጆች” (Friends of Leo) የተሰኘው ቡድን በመቋቋሙ፣ ወጣቶች እና ምዕመናን ለዚህ እጅግ ጠቃሚ መርሃ ግብር ዝግጅት እና አፈጻጸም ንቁ ተሳትፎ የማድረግ እድል እንደሚያገኙ እና የአገልግሎታቸው ዓላማም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ለመቀበል ፔሩ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

27 Aug 2026, 15:49