ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በዓለም እና ወንጌል መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ያስፈልጋል አሉ!

ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 08/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋጠ ቅዳሴ ላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የሚለዩትን ሰዎች  የቀብር ሥነ ሥርዓት ለሚያስፈጽሙ ሰዎች ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ስብከት አደገኛ በሆነው በዓለማዊ መንፈስ ላይ ያጠነጠነ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዓለማዊ መንፈስ እና በቅዱስ ወንጌል መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ መገንዘብ እንችል ዘንድ ፀጋ እንዲሰጠን መንፈስ ቅዱስን እንለምን ማለታቸው ተገልጿል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በአሁኑ ወቅት የምንገኘው በአምስተኛው የፋሲካ ሳምንት ዛሬ ግንቦት 08/2012 ዓ.ም ቅዳሜ ቀን ለዕለቱ በተዘጋጀው ሥርዓተ አምልኮ ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር፤ ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው መግቢያ ላይ ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ በአሁኑ ወቅት በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የሚለዩትን ሰዎች የቀብር ሥነ-ስረዓት ለሚያስፈጽሙ ሰዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን የሚከተለውን ተናግሯል ፡፡

“ወረርሽኙ በተከሰተበት በአሁኑ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች የቀብር ሥነ-ስረዓት ለሚያስፈጽሙ ሰዎች ዛሬ እንጸልይ። ሙታንን መቀበር ከምህረት ሥራዎች አንዱ ነው ፣ እንደ ሚታወቀው በጣም አስደሳች የሆነ ነገር አይደለም። በተጨማሪም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ስለሚጥሉ በበሽታው ሊጠቁ ስለሚችሉ ለእነሱ እንጸልይ።

በመቀጠል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያደረጉት ስብከት ከዮሐንስ ወንጌል ላይ ተወስዶ በተነበበውና “ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለ ዚሁ ነው። ‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም” (ዮሐ 15፡18-21) በሚለው የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ኢየሱስ በእርሱ የተነሳ ዓለም ደቀ መዛሙርትን እንደ ሚጠላ መናገሩን ያወሳል።

የዓለም መንፈስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በበኩላቸው ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ስለ ዓለም እና በእርሱ እና በደቀመዛሙርቱ ላይ ዓለም ስላለው ጥላቻ መናገሩን ያስታወሱ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ በዓለም መንፈስ እንዳይወሰዱ አብ ደቀመዛሙርቱን ከዓለም ለይቶ እንዲወስዳቸው ሳይሆን እዚያው ባሉበት ይረዳቸው ዘንድ አባቱን እንደ እንደ ጠየቀ ቅዱስነታቸው ተናግሯል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን ሲቀጥሉ እንደ ተናገሩት የዓለም መንፈስ ኢየሱስን ፣ ደቀመዛሙርቱን ሊጠላ እና ሊያጠፋ የሚችል እንደ ሆነ፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን ብልሹ የሆነ አሠራር እንድትከተል ሊያደርጋት እንደ ሚችል ጨምረው ገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በስብከታቸው እንደ ገለጹት የዓለም መንፈስ ለሕይወታችን ጠቃሚ መስሎ የሚቀርብ ሐሳብ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ ከመጠን በላይ ዋጋ ያላቸው የመዋቢያ የቅንጦት ዕቃዎች፣ የመልክ ፣ የውበት ፣ የመዋቢያ ቅኝቶች ባህል ነው። እንደሁኔታው ስለሚለዋወጥ ታማኝነት የጎደለው ባሕል ነው። ጥልቀት የሌለው እሴት ነው። ሁሉንም ነገር በድርድር ማከናወን ይፈልጋል ብለዋል።

ተጠቅሞ የመጣል ባህል ምቾት

ኢየሱስ በጸሎቱ ውስጥ አብ እንዲከላከልልን የጠየቀው ይህንን የመሳሰሉ ዓለማዊ መንፈሶችን ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ዓለማዊ መንፈስ ተጠቅሞ የመጣል ባህል እንደ ምቾት ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል ብለዋል። እንዲሁም ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ፣ ነገር ግን ዓለማዊ የሆኑ ነገሮችን የሚከተሉ የብዙ ሰዎች የሕይወት መንገድ ነው፣ ዓለማዊ አስተሳሰብ እምነትን እንድንጠላ ያደርገናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ታዋቂው የ 20 ኛው ክፍለ ዘመን የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል የነገረ መለኮት ምሁር የሆኑትን አባት ሄንሪ ደ ሊብካ በማጣቀሻነት በመግልጸ ዓለማዊ መንፈስ በአሁኑ ወቅት የሚታይ እና ቤተክርስቲያንን ክፉኛ እያጠቃት የሚገኝ ክፉ መንፈስ እንደ ሆነ መግለጻቸውን ያወሱት ቅዱስነታቸው የዓለማዊ መንፈስ የተቀላቀለበት መንፈስዊ ሕይወት የክርስትናን እመነት የሚገድል ነው ምክንያቱም እመነትን ክፉኛ ስለሚጠላ ነው ብለዋል። ዓለማዊ መንፈስ የማይገባበት ቦታ የለም፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንኳን ሳይቀር ስፍራ ሳይመርጥ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ እንደ ገለጹት በእምነት ጥላቻ ምክንያት ብዙ ሰማዕታት መገደላቸውን የጠቆሙ ሲሆን ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር የተቀላቀለ ዓለማዊ መንፈስ ስሩን እስከመጨረሻ መዘርጋት ስለሚችል ጥንቃቄ ማደረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢየሱስ ማመን - ለዓለም መንፈስ መድኃኒት ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደገለፁት ዓለማዊነት መታገስ የማይችለው አንድ ነገር የመስቀሉን አስፈሪነት ነው፣ ከዓለማዊ መንፈስ የሚፈውሰው ብቸኛው መድኃኒት ለእኛ ሲል የሞተው እና ከሙታን የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ዓለምን ድል ለመንሳት በኢየሱስ ማመን ያስፈልጋል፣ የመስቀሉ ሞኝነት እና የክርስቶስ ድል የእኛም ድል ነው ብለዋል።

ዓለም ኢየሱስን ይጠላል እናም ከዓለም መንፈስ እኛን ለመጠበቅ ኢየሱስ ስለእኛ አብን ይለምናል፣ሆኖም እምነት ማለት አክራሪ መሆን ወይም ከሌሎች ጋር አለመወያየት ማለት አይደለም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ስለዚህ ክርስቲያኖች እንዳይታለሉ በዓለማዊ መንፈስ እና በወንጌል መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ መገንዘብ እንችል ዘንድ ፀጋ እንዲሰጠን መንፈስ ቅዱስንን እንለምን ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የእለቱን ስብከት አጠናቀዋል። 

16 May 2020, 16:18
ሁሉንም ያንብቡ >