ፈልግ

ሁለት ሶራዊያን ጥንዶች ከሕጻን ላጃቸው ጋር ሆነው የሚያሳይ ፎቶ ሁለት ሶራዊያን ጥንዶች ከሕጻን ላጃቸው ጋር ሆነው የሚያሳይ ፎቶ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለልጆቻቸው ሲሉ ተግዳሮቶችን የሚጋፈጡ ወላጆች ጀግኖች ናቸው ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ወላጅ መሆን ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ እና ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ምስክርነት በተመለከተ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ ማደረጋቸው የተገለጸ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቅዱስ ዮሴፍ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ አባቶች የጥንካሬ እና ርኅራኄ ምሳሌ ነው በማለት እንደ ተናገሩ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ለቅዱስ ዮሴፍ የተወሰነው ልዩ ዓመት እ.አ.አ በታህሳስ 8 ቀን 2021 ዓ.ም አብቅቷል፣ ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለዚህ ቅዱስን ያላቸው ትኩረት እና ፍቅር አላበቃም እናም ለአለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ደጋፊነት ምስል አድርገው በሚያቀርቧቸው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የበለጠ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በእኛ በኩል በጣሊያንኛ “L’Osservatore Romano” በተሰኘው የቅድስት መንበር ጋዜጣ አማካይነት ከባለፈው የአ.አ ከ2021 ዓ.ም ጀምሮ ወርሃዊ በሆነው ዝግጅት አማካይነት በቀጣይነት የቅዱስ ዮሴፍን የአባትነት ኃላፊነትን የሚገልጹ መጣጥፎችን ይፋ ማድረግ መቀጠላችን የሚታወቅ ሲሆን ይህም በቫቲካን ዜና ድረ-ገጽ ላይ በላቲን ቋንቋ “ Patris corde” (በፓትሪስ ኮርዴ፣ የአባት ልብ) በተሰኘው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ዮሴፍን በተመለከተ ይፋ ካደርጉት ሐዋርያዊ መልእክት ላይ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ጠንካራ አባትነት ላይ ያተኮረ ጹሑፎችን ይፋ ማድረጋችን ይታወሳል። ይህ ከአባቶች ጋር የተገናኘ ታሪክ ሲሆን ነገር ግን ከልጆች እና እናቶች ጋር ጥሩ ውይይት እንዴት እንደ ሚደረግ እና የዬሴፍ እጮኛ ከነበረችው ከማርያም ጋር የነበረውን ግንኙነት ስለ አባትነት እና ስለ ልዩ ልዩ ገፅታዎች ፣ ተግዳሮቶች እና ውስብስብ ጉዳዮች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ለመወያየት ፍላጎት እንዲያሳድርብን ያደረገ ጉዳይ ሲሆን በዚህም መሰረት እርሳቸው ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።

በዚህም መሰረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለጥያቄዎቻችን መልስ እንዲሰጡን ፣ ለቤተሰብ ያላቸውን ፍቅር ፣ በመከራ ውስጥ ላሉ ሰዎች ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት እና ዛሬ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ችግሮችን የሚጋፈጡ አባቶች እና እናቶች ቤተክርስትያን ማቀፉን እና ለወደፊቱም ማቀፍ መቀጠሏን አሳይተዋል።

1.    ጥያቄ፡- ቅዱስ አባታችን፣ ለቅዱስ ዮሴፍ የተሰጠ ልዩ ዓመት አስታውቀዋል፣ በላቲን ቋንቋ Patris corde (ፓትሪስ ኮርዴ) የሚል ሐዋርያዊ መልእክቶ ለቅዱስ ዮሴፍ ከፍተኛ የሆነ ቦታ የሰጡት ሲሆን በመቀጠልም እርሱን በተመለከተ ተከታታይነት ያላቸው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በማደረግ ላይ ይገኛሉ። ቅዱስ ዮሴፍ ለእርሶ ምን ዓይነት ሰው ነው?

ስለቅዱስ ዮሴፍ የተሰማኝን እና ለእርሱ ያለኝን ቅርበት ደብቄ አላውቅም። ከልጅነቴ ከተፈጠርኩበት ጊዜ አንስቶ የመጣ ነገር ይመስለኛል። እኔ ሁል ጊዜ ለቅዱስ ዮሴፍ ያለኝን ልዩ ፍቅር እያሳደኩኝ የመጣው ሲሆን ምክንያቱም የእርሱ ማንነት ለእያንዳንዳችን የክርስትና እምነት ምን መሆን እንዳለበት በሚያምር እና በቀላል መንገድ እንደሚወክል አምናለሁ። በእውነቱ ቅዱስ ዮሴፍ እንደ ማንኛውም ሰው የተለመደ ሰው ነው እናም ቅድስናው ባጋጠመው እና በተጋፈጣቸው ውብ እና አስቀያሚ ነገሮች እራሱን ቅዱስ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው። ነገር ግን ቅዱስ ዮሴፍን በወንጌል ውስጥ በተለይም በማቴዎስ እና በሉቃስ ወንጌሎች ውስጥ የድነት ታሪክ ጅማሬ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ መገኘቱን ልንክድ አንችልም። በእርግጥም የኢየሱስን መወለድ ያመለከቱ ክስተቶች በእንቅፋት የተሞሉ፣ በችግር፣ በስደት፣ በጨለማ የተሞሉ፣ አስቸጋሪ ክስተቶች ነበሩ። እናም በአለም ውስጥ ወደ ተወለደው ወደ ልጁ ይመጣ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ማርያምንና ዮሴፍን ከጎኑ አድርጎ አቆማቸው።

ቃል ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነው ማርያም ከወለደችው በኋላ ሲሆን ከእዚያን በኋላ ግን ሕጻኑን የተንከባከበው፣የጠበቀው፣ ያሳደገው፣ ቅዱስ ዮሴፍ ነበር። በእሱ ውስጥ የአስቸጋሪ ጊዜያት ሰው፣ ተጨባጭ የሆነ ሰው፣ ኃላፊነትን እንዴት እንደሚወስድ የሚያውቅ ሰው አለ ማለት እንችላለን። በዚህ መልኩ በቅዱስ ዮሴፍ ውስጥ ሁለት ባህሪያት ተቀላቅለው እናገኛለን። በአንድ በኩል የእርሱ ምልክት መንፈሳዊነት፣ በሕልም ታሪኮች አማካኝነት በወንጌል ተተርጉሟል፣ እነዚህ ዘገባዎች ዮሴፍ አምላክ የልቡን ሲናገር እንዴት መስማት እንዳለበት የማወቅ ችሎታ እንዳለው ይመሰክራሉ። የሚጸልይ ሰው ብቻ ነው፣ ኃይለኛ መንፈሳዊ ህይወት ያለው፣ በእኛ ውስጥ በሚኖሩ ሌሎች ብዙ ድምፆች መካከል የእግዚአብሔርን ድምጽ እንዴት እንደሚለይ የማወቅ ችሎታ ሊኖረው የሚችለው። ከዚህ አንፃር፣ ሌላም ነገር አለ፡- ዮሴፍ ተጨባጭ ሰው ነው፣ ማለትም ችግሮች የሚያጋጥሙት ትልቅ ተግዳሮት፣ ችግሮች እና መሰናክሎች ሲያጋጥሙት ተጎጂ የመሆንን ቦታ ፈጽሞ የማይወስድ ሰው ነው። ይልቁንም ራሱን ሁልጊዜ አዘጋጅቶ፣ ምላሽ የመስጠት፣ በአምላክ በመታመን እና በፈጠራ መንገድ መፍትሄ በማግኘት ረገድ ራሱን ያስቀምጣል።

2.   ጥያቄ፣ በዚህ በታላቅ የፈተና ጊዜ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ያሎት የታደሰ ትኩረት ልዩ ትርጉም አለው ወይ?

አሁን ያለንበት ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ተለይቶ የሚታወቅ አስቸጋሪ ጊዜ ነው። ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው፣ ብዙ ቤተሰቦች ለችግር ተጋልጠዋል፣ ብዙ ሰዎች በሞት ጭንቀት እየተዋጡ ነው፣ የወደ ፊት ነገሮችን በእርግጠኝነት የማናውቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። እነዚህን የጨለማ ጊዜያት እንዴት መጋፈጥ እንዳለብን ለማወቅ ትክክለኛው መንገድ የትኛው እንደሆነ ለመረዳት የሚያበረታታን፣ የሚረዳን፣ የሚያነቃቃን ሰው እንደሚያስፈልገን በትክክል ተሰማኝ። ቅዱስ ዮሴፍ በጨለማ ጊዜ ብሩህ ምስክር ነው። መንገዳችንን እንደገና ለማግኘት በዚህ ጊዜ ለእርሱ ቦታ መስጠት ተገቢ የሆነው ለዚህ ነው።

3.   ጥያቄ፡ የእርሶ የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና አገልግሎቶን የጀመረው እ.አ.አ. በመጋቢት 19/2013 ዓ.ም ሲሆን ይህ ቀን ደግሞ የቅዱስ ዮሴፍ አመታዊ በዓል የሚከበርበት ቀን ነው፣ ይህንን እንዴት ይመለከቱታል?

የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና አገልግሎቴን እ.አ.አ. በመጋቢት 19/2013 ዓ.ም ለመጀመር በመቻሌ ከሰማይ እንደ ወረደ በረከት አድርጌ እቆጥራለሁ። በሆነ መንገድ ቅዱስ ዮሴፍ እኔን እንደሚረዳኝ፣ ከጎኔ እንደሚሆን፣ እና እሱን እንደ ጓደኛዬ ማስበው እንደምችል ሊነግረኝ የፈለገ ይመስለኛል፣ የማምንበት እና የምተማመንበትም ነገር ነው።እንዲማልድልኝ እና እንዲጸልይልኝ መጠየቅ እችል ነበር። ነገር ግን በእርግጥ፣ ይህ ከቅዱሳን ህብረት የሚመጣው ግንኙነት ለእኔ ብቻ የተዘጋጀ አይደለም። ለብዙዎች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ነው ለቅዱስ ዮሴፍ የተወሰነው አመት የብዙ ክርስቲያኖች ልብ የቅዱሳን ኅብረት ያለውን ጥልቅ እሴት እንደገና እንዲገነዘብ ያደረገው፣ ረቂቅ ኅብረት ሳይሆን ራሱን በተጨባጭ ግንኙነት የሚገልጽ እና ተጨባጭ ውጤት ያለው ተጨባጭ ኅብረት እንዲሆን ያደረገው ለዚህ ነው።

4.   ጥያቄ፡ በጋዜጣችን ላይ በላቲን ቋንቋ “Patris corde” (በፓትሪስ ኮርዴ፣ የአባት ልብ) የተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክት ለቅዱስ ዮሴፍ በተሰጠው ልዩ አመት የቅዱሱን ሕይወት ከአባቶች ሕይወት ጋር እና በተጨማሪም ከዛሬዎቹ ልጆች ሕይወት ጭምር ጋር አስተሳስረን ነበር። የዛሬ ልጆች፣ የነገ አባቶች፣ ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ምን ሊያገኙ ይችላሉ?

አንድ ሰው እንደ አባት ሆኖ አይወለድም፣ ነገር ግን ሁላችንም እንደ ልጅ ሆነን የተወለድነው በእርግጠኝነት ነው። ልናስብበት የሚገባን የመጀመሪያው ነገር ይህ ነው፡- ማለትም እያንዳንዳችን ሕይወት ካዘጋጀልን ነገር ሁሉ በቀር በመጀመሪያ ደረጃ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ መሆናችንን እና እንዲያሳድገን በኃላፊነት ለተሰጠው አደራ ተሰጥቶታል። ይህም በክፉም በደጉም ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። ይህንን ግንኙነት መመስረት እና በህይወታችን ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ መገንዘብ ማለት በአንድ ሰው ህይወት ላይ ሀላፊነት የምንወስድበት ቀን - ማለትም አባትነትን በተግባር ማሳየት ሲኖርብን - በመጀመሪያ ያገኘነውን ልምድ ይዘን እንደምንሄድ መረዳት ማለት ነው። እናም ተመሳሳይ ስህተቶችን ላለመድገም እና ያጋጠሙንን ውብ ነገሮች እንደ ውድ ነገር ለመመልከት ይህንን የግል ተሞክሮ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። ቅዱስ ዮሴፍ ከኢየሱስ ጋር የነበረው የአባትነት ግንኙነት በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ እርግጠኛ ነኝ፣ ይህም የኢየሱስ የወደፊት ስብከት በትክክል ከአባታዊ ምስሎች በተወሰዱ ምስሎች እና ማጣቀሻዎች የተሞላ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ አባቱ እግዚአብሔር እንደሆነ ተናግሯል፣ ይህ አባባል ግድየለሾች እንድንሆን ሊተወን አይችልም፣ በተለይም ስለ አባትነት ሰብዓዊ ተሞክሮ ስናስብ ግድየለሾች እንድንሆን ሊያደርጉን አይችሉም። ይህ ማለት ቅዱስ ዮሴፍ በጣም ጥሩ አባት ስለነበር ኢየሱስ በዚህ ሰው ፍቅር እና አባትነት ውስጥ ለእግዚአብሔር ሊሰጥ የሚችለውን እጅግ የሚያምር ማጣቀሻ አግኝቷል። የዛሬዎቹ ልጆች ነገ አባቶች ይሆናሉ፣ ምን ዓይነት አባቶች እንደነበሩ እና ምን ዓይነት አባቶች መሆን እንደሚፈልጉ እራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው ማለት እንችላለን። የአባትነት ሚና የአጋጣሚ ወይም ያለፈ ልምድ ውጤት ብቻ እንዲሆን መፍቀድ ሳይሆን አንድን ሰው እንዴት መውደድ እንዳለበት፣ የአንድን ሰው ኃላፊነት እንዴት መሸከም እንደሚቻል አስቦ በዚህ ግንዛቤ መወሰን ማለት ነው።

5.   ጥያቄ፣ በላቲን ቋንቋ “Patris Corde”  ፓትሪስ ኮርዴ (የአባት ልብ) የተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክት የመጨረሻው ምዕራፍ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ የአባትነት ድባብ ይናገራል። እንዴት መገኘት እንዳለበት የሚያውቅ አባት፣ ነገር ግን ልጁ በነፃነት እንዲያድግ ያደርጋል። የክብር ቦታን እና ታይታን በሚያስተዋውቀው ወይም በሚሸልመው ማሕበረሰብ ውስጥ ይህ ይቻላል ወይ?

በጣም ቆንጆ ከሆኑት የፍቅር ገጽታዎች አንዱ እና የአባትነት ነገር ብቻ ሳይሆን በእርግጥ ነፃነት ነው። ፍቅር ሁል ጊዜ ነፃነትን ይፈጥራል። ፍቅር እስር ቤት፣ ንብረት መሆን የለበትም። ቅዱስ ዮሴፍ በኢየሱስ ላይ ከፍተኛ የሆነ የቁጥጥር መንፈስ ሳያሳይ፣ ሊጠቀምበት ሳይፈልግ፣ ከተልእኮው ሊያዘናጋው ሳይፈልግ የመንከባከብ ችሎታውን እርሱ አሳይቶናል። እንደ እኔ ከሆነ፣ እኔ እንደማስበው ይህ ለመውደድ ያለን አቅም ፈተና እና እንዲሁም አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እንዴት መውሰድ እንደሚገባን ለማወቅ ያለን አቅም ፈተና ነው። አባት ጥሩ የሚሆነው ልጁ በውበቱ፣ በልዩነቱ፣ በምርጫው፣ በሙያው እንዲወጣ ለማደረግ በትክክለኛው ጊዜ ራሱን እንዴት ማግለል እንዳለበት ሲያውቅ ነው። ከዚህ አንፃር፣ በእያንዳንዱ መልካም ግንኙነት፣ ከከፍታ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮችን ለመጫን መሻትን መተው አለብን፣ ምስልን፣ መጠበቅን፣ በእርግጥም ታይታን፣ ትእይንቱን ውብ የሚያደርግ ከልክ ያለፈ ገጸ ባህሪይ ተሞልቶ እንዲኖር ከመጠን በላይ መገፋፋት አይገባም። ወደ ላይ ብቻ ሳይሆን እንዴት ወደ ጎን መውጣት እንዳለበት የማወቅ ሙሉ በሙሉ “ዮሴፍን የሚመስል” ባሕርይ፣ ወደ ሁለተኛ ቦታ የመግባት አቅም ያለው ትሕትና፣ ምናልባትም ዮሴፍ ለኢየሱስ ያለው ፍቅር በጣም ወሳኝ ገጽታ ነው። በዚህ መልኩ ዮሴፍ በጣም አስፈላጊ ገፀ-ባህሪ ነው፣ በኢየሱስ የህይወት ታሪክ ውስጥ አንድ አስፈላጊ ነገር ነው ለማለት እደፍራለው ምክንያቱም በተወሰነ ጊዜ ላይ ኢየሱስ በተጠራው ጥሪ ሁሉ፣ በተልእኮው ሁሉ እንዲያበራ ከትዕይንቱ እንዴት መውጣት እንዳለበት ያውቃል። ከዮሴፍ ምስል ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚኖርብን ሲሆን እኛ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን እንዴት ወደ ኋላ መመለስ እንዳለብን ለማወቅ ሌላውን እና በተለይም በአደራ የተሰጡን፣ በውስጣችን የማመሳከሪያ ነጥብ እንዲያገኙ ለመፍቀድ፣ ነገር ግን በጭራሽ እንቅፋት ሳንሆን እንዴት ወደ ፊት መጓዝ እንደ ምንችል ማሳየቱ ተገቢ ነው።

6.   ጥያቄ፡- አባትነት ዛሬ ችግር እየገጠመው መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል። ምን ማድረግ ይቻላል፣ ለህብረተሰቡ መሠረታዊ የሆነውን የአባት እና ልጅ ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር ቤተክርስቲያን ምን ማድረግ ትችላለች?

ቤተክርስቲያንን ስናስብ እሷን እንደ እናት እናስባታለን እና ይህ በእርግጠኝነት ስህተት አይደለም። በእነዚህ አመታት ውስጥ፣ እኔም ይህን አመለካከት ለማጉላት በጣም ሞክሬ ነበር ምክንያቱም የቤተክርስቲያን እናትነት መጠቀሚያ መንገድ ነው፣ ይህም ምሕረት ማለትም ፍቅር ሕይወትን የሚያመነጭ እና የሚያድስ እንደ ሆነ የሚያሳይ ነው። ይቅርታና ዕርቅ ዳግም ወደ ነበርንበት ቦታ የምንመለስበት መንገድ አይደለምን? ሌላ ዕድል ስለተቀበልን አዲስ ሕይወት የምንቀበልበት መንገድ አይደለምን? በምህረት ከሌለ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሊኖር አይችልም! ሆኖም ቤተ ክርስቲያን የእናት ብቻ ሳትሆን የአባትም መሆን አለባት ለማለት ድፍረት ሊኖረን የሚገባ ይመስለኛል። የተጠራችው የአባትነት አገልግሎትን ልትሰጥ እንጂ የአባትነት አመራር ልትሰጥ ግን አይደለም። እናም ቤተክርስቲያኗ ይህንን የአባትነት ገፅታ እንደገና ማግኘት አለባት ብዬ ስናገር፣ ልጆች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ነጻነታቸውን እንዲጠቀሙ እና ምርጫ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች ውስጥ የማስገባት ሙሉ በሙሉ አባታዊ የሆነውን አቅም ነው። በአንድ በኩል ምህረት ቢያድነን፣ ቢፈውሰን፣ ቢያጽናናን፣ ቢያበረታን በሌላ በኩል፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በይቅርታ እና በፈውስ ብቻ የተወሰነ አይደለም፣ ይልቁንም፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ውሳኔ እንድናደርግ፣ ወደ ወደ ባህር ወደ ጥልቁ  እንድንሄድ ያነሳሳናል።

7.   ጥያቄ፣ አንዳንድ ጊዜ በዚህ ባለንበት ወቅት እየተከሰተ በሚገኘው ወረርሽኝ ምክንያት ፍርሃት ይህንን ሐሳብ ሽባ ሊያደርግ አይችልም ወይ?

አዎን በታሪክ ውስጥ ይህ ጊዜ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ውሳኔ ማድረግ ባለመቻሉ የሚታወቅበት ወቅት ነው። ወጣቶቻችን ብዙውን ጊዜ ለመወሰን፣ ለመምረጥ፣ አደጋን ለመጋፈጥ ይፈራሉ። ቤተክርስቲያን እንደዚህ ያለችው አዎ ወይም አይደለም ስትል ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ ስታበረታታ እና ትልቅ ምርጫዎችን ስታደርግ ነው። እናም እያንዳንዱ ምርጫ ሁል ጊዜ አንዳንድ ውጤቶች እና አንዳንድ አደጋዎች አሉት ፣ነገር  ግን አንዳንድ ጊዜ መዘዞችን እና አደጋዎችን በመፍራት ሽባ እንሆናለን እናም ምንም ነገር ማድረግ ወይም ምርጫ ማድረግ አንችልም። እውነተኛ አባት ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን አይነግርህም፣ ነገር ግን ነገሮች ጥሩ ባልሆኑበት ሁኔታ ውስጥ እራስህን ብታገኝ እንኳን እነዚያን ጊዜያት ማለትም እነዚያን ውድቀቶች እንኳን በመጋፈጥ እና በክብር መኖር ትችላለህ ብሎ የሚነግርህ አባት ነው። አንድ የጎለመሰ ሰው በአሸናፊነቱ ብቻ ሳይሆን ውድቀትን እንዴት እንደሚለማመድ በማወቁ ሊታወቅ ይችላል። የአንድ ሰው ባህሪ ሊታወቅ የሚችለው በመውደቅ እና በድክመቱ ልምድ ውስጥ በትክክል ማለፍ ሲችል ነው።

8.   ጥያቄ፡ መንፈሳዊ አባትነት ለእርስዎ በጣም አስፈላጊ ነው። ካህናት እንዴት አባት ሊሆን ይችላል?

ቀደም ብለን አባትነት እንደ ተራ ነገር አይቆጠርም ብለን የነበረ ሲሆን ሁላችንም አባት ሆነን አይደለም የተወለድነው። በተመሳሳይ መንገድ ካህን እንደ አባት ሆኖ አልተወለደም፣ ነገር ግን ከሁሉ አስቀድሞ ራሱን እንደ እግዚአብሔር ልጅ አድርጎ በመገንዘብ፣ በኋላም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅ በመገንዘብ በጥቂቱ ሊማር ይገባዋል። እናም ቤተክርስቲያን ረቂቅ ፅንሰ-ሀሳብ አይደለችም። እሷ ሁል ጊዜ የአንድ ሰው ፊት ፣ ተጨባጭ ሁኔታ ፣ ትክክለኛ ስም የምንሰጥበት ነገር ነች። እምነታችንን የምንቀበለው ከአንድ ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ነው። የክርስትና እምነት ከመጻሕፍት ወይም ቀላል በሆነ ምክንያት የምንማረው ነገር አይደለም። ይልቁንም በግንኙነታችን ውስጥ የሚያልፍ የህልውና ምንባብ ነው። የእምነት ልምዳችን ሁል ጊዜ የሚመነጨው ከአንድ ሰው ምስክርነት ነው። ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች ምስጋናን በምን መንገድ ማቅረብ እንችላለን ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። እናም ከሁሉም በላይ ይህን ወሳኝ አቅም ጠብቀን ከሆነ በእነሱ ውስጥ ማለፍ የቻሉትን በጣም ጥሩ ያልሆኑትን እንዴት መለየት እንደሚቻል ለማወቅ መጣር አለብን። መንፈሳዊ ሕይወት ከሰው ሕይወት ያን ያህል የተለየ አይደለም። ጥሩ አባት፣ እንደ ሰው ሆነን ለመናገር ያህል ልጁ እርሱን እንዲመስል የሚረዳው ከሆነ፣ ነጻነቱን ሲያረጋግጥለት፣ ትላልቅ ውሳኔዎችን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ከሆነ መልካም አባት አይደለም፣ መንፈሳዊ አባትም እንዲሁ በአደራ የተሰጡት ሰዎች ሕሊና በራሱ ሲተካ ተገቢ አይሆንም። እርሱ ጥሩ መንፈሳዊ አባት የሚሆነው እነዚህ ሰዎች በልባቸው ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ሲመልስ ብቻ ሳይሆን በአደራ የተሰጡትን ሰዎች ሕይወት ሲቆጣጠር ሳይሆን በጥበብና በተመሳሳይ ጊዜ መንገዱን ማሳየት ሲችል ነው፣ የተለያዩ የሕይወት ትርጓሜዎችን ለእነርሱ በማሳየት በገዛ ፈቃዳቸው በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ውሴኔ ለራሳቸው እንዲያደርጉ መርዳት ሲችል እና እገዛ ሲያደርግ ነው።

9.   ጥያቄ፡ ይህን የአባትነት መንፈሳዊ ገጽታ ለማጠናከር ዛሬ የሚያስፈልገው አስቸኳይ ነገር ምንድነው?

መንፈሳዊ አባትነት በተለይ ከተሞክሮ የሚነሳ ስጦታ ነው። አንድ መንፈሳዊ አባት የንድፈ ሃሳቡን ችሎታ ሳይሆን የሚያስፈልጉት ከሁሉም በላይ የግል ልምዱን ማካፈል ሲችል ነው። በዚህ መንገድ ብቻ ለአንድ ልጅ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። መንፈሳዊ አባትነት ብለን ልንገልጸው የምንችላቸው ትርጉም ያላቸው ግንኙነቶች በታሪክ ውስጥ በዚህ ወቅት ትልቅ አስቸኳይ ጉዳይ አለ፣ ነገር ግን፣ ስለ መንፈሳዊ እናትነትም እንድናገር ፍቀድልኝ ምክንያቱም ይህ የማጀብ ሚና የወንድ መብት ወይም የካህናቶች ብቻ አይደለም። ብዙ ጥሩ ሃይማኖተኛ ሴቶች፣ የተቀደሱ ሴቶች፣ ነገር ግን ለሌሎች ሰዎች ሊያካፍሉ የሚችሉ የልምድ ክህሎት ያላቸው ብዙ ምእመናን እና ሴቶች አሉ። ከዚህ አንፃር፣ መንፈሳዊ ግንኙነት ከሌሎች የስነ-ልቦናዊ ወይም የሕክምና ተፈጥሮ መንገዶች ጋር ሳናደናግር በዚህ ታሪካዊ ወቅት በአዲስ ጥረት እንደገና ልናገኛቸው ከሚገቡ ግንኙነቶች አንዱ ነው።

10.  ጥያቄ፣ ኮቪድ 19 ካስከተለው አሳዛኝ መዘዞች መካከል የብዙ አባቶች ስራ ማጣትም አንዱ ነው። ችግር ላጋጠማቸው አባቶች ምን ማለት ይፈልጋሉ?

በተለይ በወረርሽኙ ሳቢያ ከምንም በላይ ለእነዚያ ቤተሰቦች፣ አባቶች እና እናቶች ልዩ ችግር እያጋጠማቸው ላለው ስቃይ በጣም ቅርብ መሆኔ ይሰማኛል። እኔ እንደማስበው ልጆቹን መመገብ አለመቻል፣ ለሌሎች ህይወት ሃላፊነት መሰማቱ፣ ለመጋፈጥ ቀላል ያልሆነ መከራ ነው። በዚህ ረገድ ጸሎቴ፣ መቀራረቤ ነገር ግን የቤተክርስቲያኗ ድጋፍ ሁሉ ለእነዚህ ሰዎች፣ ለትንንሾቹ ነው። ነገር ግን ጦርነትን የሚሸሹ፣ በአውሮፓና በሌሎችም ቦታዎች ውድቀትን የሚያስከትሉ፣ ስቃይና የፍትሕ መጓደል የሚያጋጥማቸው ብዙ አባቶችን፣ ብዙ እናቶችንና ብዙ ቤተሰቦችን አስባለሁ። እነዚህ አባቶች፣ እነዚህ እናቶች፣ ለኔ ጀግኖች ናቸው ማለት የምፈልገው በልጆቻቸው ፍቅር፣ ለቤተሰባቸው ፍቅር ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉትን ሰዎች ሁሉ በድፍረት ጀግኖች ልላቸው እፈልጋለሁ። ማርያምና ​​ዮሴፍም በሄሮድስ ዓመፅና ሥልጣን ምክንያት ወደ ባዕድ አገር በመሸሽ ይህን ግዞት አሳልፈዋል። የደረሰባቸው ስቃይ ዛሬም ተመሳሳይ ፈተና እየደረሰባቸው ካሉት ወንድሞች ጋር እንዲቀራረቡ አድርጓቸዋል። እነዚም አባቶች በአደራ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ ይመለሱ፣ እንደ አባት እርሱም ተመሳሳይ ልምድ እንዳሳለፈ አውቀው አንድ ዓይነት ግፍ እንደደረሰበት አውቀው ወደ እርሱ ይመለሱ። እናም ለሁሉም እና ለቤተሰቦቻቸው፣ ብቸኝነት እንዳይሰማችሁ ልላቸው እፈልጋለሁ! ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁልጊዜ ያስታውሷቸዋል እና በተቻለ መጠን ለእናንተ ድምጽ መስጠታቸውን ይቀጥላሉ እናንተን በፍጹም አረሳችሁም።

14 January 2022, 16:15