ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ከቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት ሠራተኞችን በቫቲካን ተቀብለው  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ከቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት ሠራተኞችን በቫቲካን ተቀብለው   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እውነተኛ ጋብቻ ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አዲስ የሥራ ዓመት የሚጀምሩ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት አባላትን በቫቲካን ለተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ዓርብ ጥር 19/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ለተገኙት የሐዋርያዊ ፍርድ ቤት ሠራተኞች ባስተላለፉት መልዕክት፣ “የቤተሰብ ወንጌልን” ማወጅ ከቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ እውነተኛ ጋብቻ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቤተሰብ የሚመሠረትበትን፣ በወንድና በሴት መካከል ያለውን የጋብቻ ጥምረት ትርጉም እና ታላቅነት  እንደገና የመገንዘብ ከፍተኛ አስፈላጊነት በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ መኖሩን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው አዲስ የሥራ ዓመት ለሚጀምሩት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት አባላት መልዕክት ሲያስተላለፉ እንደተናገሩት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቹን ቃል ለዓለም በሙሉ ለማወጅ ባላት ተልዕኮዋ፣ ከጋብቻ ጋር ያለውን ታላቅ ምስጢር እና የቤተሰብ ፍቅርን ማጉላት እና በክብር ማቆየት እንደሆነ አስረድተዋል።

ጋብቻ ስጦታ ነው!

“ጋብቻ በክርስቲያናዊ ትርጉሙ ከባሕላዊ ሥነ-ሥርዓት ወይም ከማኅበራዊ ክስተት በላይ ነው” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ጋብቻ ተራ ወይም ረቂቅ ሐሳብ ሳይሆን የራሱ ትክክለኛ ወጥነት ያለው እውነት ነው” መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ እውነታው አንጻር፣ ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም፣ የራሱ ድክመቶች እና ስህተቶች ቢኖሩትም፣ እንዴት አሳታፊ፣ ታማኝ እና ዘላቂ ሊሆን እንደሚችል ጠይቀዋል። ለዚህ ጥያቄ ባቀረቡት መልስም፣ እውነተኛ ጋብቻ በሙሉ፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚፈጸም እንኳ ቢሆን፣ ለባለትዳሮቹ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ እንደሆነ ገልጸው፣ በማከልም ጋብቻ ሁሌም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ፣ የጋብቻ ታማኝነት በመለኮታዊ ታማኝነት ላይ እንደሚመካ፣ የጋብቻ ፍሬያማነት በመለኮታዊ ፍሬያማነት ላይ እንደሚመካ አስረድተዋል።

በዚህ ምክንያት ጋብቻ “ወደ ስሜት እርካታነት ወይም ወደ ራስ ወዳድነት ሊቀየር እንደማይችል አስገንዝበው፣“ጋብቻ የሚቆየው ስሜታዊ ፍቅር እስካለ ድረስ ብቻ ነው” የሚለው ሃሳብ ትክክል እንዳልሆነ፣ የጋብቻ ፍቅር ከትዳር ሕያወት የማይነጣጠል፣ ደካማ እና ውስን የሆነው የሰው ፍቅር ከመለኮታዊ ፍቅር ጋር በመገናኘት ሁል ጊዜ ታማኝ እና ይቅር ባይ እንደሆነ አስረድተዋል። “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ!” የሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ጋብቻንም እንደሚመለከት፣ ባለ ትዳሮችን ዘወትር በጸጋው የሚደግፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን አስረድተዋል።

ጋብቻ መልካም ነው!

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ጋብቻ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ካብራሩ በኋላ ቀጥለውም፣ ጋብቻ መልካም እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው፣ ለሰው ልጅ በሙሉ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው፣ ለባለ ትዳሮች እና ልጆቻች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቤተሰቦች፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለመላው ዓለምም ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።በተጨማሪም “ጋብቻ በክርስቲያናዊ የድነት ጉዞ በዕለት ተዕለት ሕይወትም ወደ ቅድስና የሚወስድ መንገድ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፣ “ጋብቻ የቤተሰብ ወንጌል አስፈላጊ ገጽታ ነው” በማለት አስረድተዋል።

በችግር እና ፈተና ውስጥ የሚገኙ ጋብቻዎችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣  የተለያዩ ችግሮችን የሚጋፈጡ ባለትዳሮችን ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ዓይን ተመልክታቸው መደገፍ እንደሚገባ አሳስበው፣ የቤተ ክርስቲያ ሐዋርያዊ አገልግሎት ምላሽ፣ ጋብቻ የማይሻር የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን እንደገና ማስገንዘብን እና ማደስን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም ጋራ ማኅበራዊ ሳይንስ ለጋብቻ ሕይወት የሚያበረክታቸውን አስተዋፅዖዎች ችላ ሳይሉ፣ በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ የሚቀረጸው መልካም አስተሳሰብ በትዳር ሕይወት ውስጥ ለእርቅ ጉዞ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት፣ የጋብቻ ሕይወት ድክመቶች ቢያጋጥሙትም ከመንፈስ ቅዱስ በሚያገኘው ዕርዳታ በመታገዝ ሕልውናውን አስጠብቆ ሊቆይ ይገባል ብለዋል።

28 January 2023, 16:25