ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ወንጌል የሚሰበክበት የመጀመሪያው መንገድ ምስክርነት ነው!” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ጣሊያንን ጨምሮ ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ባቀረቡት ሳምንታዊ አስተምህሮ፥ “ወንጌል የሚሰበክበት የመጀመሪያው መንገድ የወንጌል ምስክርነት ነው” በማለት አስገንዝበዋል። ክቡራት እና ክብራን አድማጮቻችን ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን ለአስተንትኖ እንዲሆን የመረጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናቀርብላችኋለን፥

“በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ እርስ በእርሳችሁ ተሳሰቡ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ ርኅሩሆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም  በረከትን ልትወርሱ ተጠርታችኋል።” (1ኛ ጴጥ. 3: 8-9)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችን ለዘመናችን የወንጌል ስርጭት አገልግሎት እንዲያግዘን የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ‘ወንጌልን ማወጅ’ በማለት እንደ ጎርጎራሳውያኑ በታኅሳስ 8/1975 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የሚለንን መሪ እቅድ እንመለከታለን። የወንጌል ምስክርነት ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ሥነ-ምግባራዊ ትምህርት በላይ ነው። ከሁሉም በላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን የግል ግንኙነት የምንመሰክርበት መንገድ፤ የዓለም የዳነበት እና በሥጋ የተገለጠ ቃል ነው። መተኪያ የሌለው ምስክርነት ነው፤ ምክንያቱም ከሁሉ አስቀድሞ የወንጌል ምስክሮች ራሳቸው ሊያውቁትና ሊለማመዱት ስለሚገባው አምላክ እንዲመሰክሩ ዓለም እየጠራ ያለበት በመሆኑ ነው። (‘ወንጌልን ማወጅ’ ቃለ ምዕዳን ቁ. 76) ከዚህም በላይ ‘የዘመናችን ሰው ከወንጌል መምህራን ይልቅ የወንጌል ምስክሮችን በሙሉ ፈቃደኝነት መስማትን ይመርጣል። የወንጌል መምህራንን የሚሰማ ከሆነም የወንጌል ምስክሮች በመሆናቸው ነው። (‘ወንጌልን ማወጅ’ ቃለ ምዕዳን ቁ. 41) የክርስቶስ ምስክርነት ማለት በተመሳሳይ መንገድ የመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት መንገድ ነው። ለውጤታማነቱም አስፈላጊ መስፈርት በመሆነው በወንጌል ስርጭት ፍሬያማ ይሆናል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት እምነትን እንደሚጨምር ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህም ማለት፣ ወሰን በሌለው ፍቅሩ በፈጠረን እና ባዳነን በእግዚአብሔር አብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ማመን እና ከእርሱ ጋር አንድ መሆን ማለት ነው። እኛን የሚለውጥ፣ በመካከላችን ያለውን ግንኙነት የሚያስተካክል፣ ምርጫዎቻችንን የሚወስን መስፈርት እና እሴት እምነት ነው። ስለዚህ ምስክርነት አንድ ሰው በሚያምንበት እና በሚናገረው መካከል ካለው ወጥነት ሊለይ አይችልም።

እያንዳንዳችን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደሚከተለው ላስቀመጧቸው ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለብን። ‘የምትሰብኩትን ታምናላችሁ? ያመናችሁትን ትኖሩታላችሁ? የምትኖሩትን ትሰብካላችሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች በቀላሉ ቶሎ ብለን በምንሰጣቸው መልሶች ልንረካ አንችልም።ምንም እንኳን ያልተረጋጋን ብንሆን፣ በእያንዳንዳችን ውስጥ በሚሠራው በመንፈስ ቅዱስ ተግባር በሙላት በመታመን፣ እንቅፋቶችን በማለፍ ከድንበሮቻችን፣ ከአቅማችን እና ከውስንነታችን በላይ ሆነው ሊያጋጥሙን የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ፈተናዎች ለመጋፈጥ ተጠርተናል።  

ከዚህ አንፃር፣ የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምስክርነት በጥምቀት ላይ የተመሠረተ እና የቅድስና ጉዞን ያካተተ በመሆኑ፣ ‘የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድንሆን ያደርገናል፤ በዚህም በእውነት የተቀደስን ነን’ (የሕዝቦች ብርሃን ሕገ ቀኖና ቁ. 40) ቅድስና ለጥቂቶች ብቻ የተቀመጠ አይደለም። ተቀብለነው ለራሳችን እና ለሌሎች ፍሬ እንድናፈራ የሚጠይቀን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በእግዚአብሔር የተመረጥን እና የተወደድን በመሆናችን ከቅዱሳን ጋር በአንድነት እንድንኖር ይጠበቅብናል። ‘ለቅዱሳን የማይገባው፣ ማንኛውም የዝሙት እና የርኩሰት፣ ወይም የስስት ነገር ሁሉ በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ።’ (ኤፌ. 5:3) የመልካምነትን፣ የትህትናን፣ የየዋህነትን እና የታላቅነትን ስሜት ልንለብስ ይገባል። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን እና የተዋጃችሁ ሆናችሁ ምሕረትን፣ ርኅራሄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግስትን ልበሱ። (ቆላ. 3:12)

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን ማፍራት ይገባል። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት (ገላ. 5:22) ፣  ‘አሁን ግን ከኃጢአት ነፃ ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ባርያዎች ሆናችኋል፤ ፍሬያችሁም ቅድስና ነው፤ መጨረሻውም የዘለዓለም ሕይወት ነው።’ (ሮሜ 6:22) የወንጌል ምስክርነት ቅንዓት የሚመነጨው ከቅድስና እንደሆነ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አስተምረውናል። በጸሎት የዳበረ፣ ከሁሉም በላይ በቅዱስ ቁርባን ፍቅር ወንጌልን መስበክ ቅድስናን ይጨምራል። በተመሳሳይም ‘ያለ ቅድስና የሚቀርብ ወንጌል ምስክርነት የዘመናችንን ሰው ልብ ለመንካት ይቸገራል’፣ የከንቱነት እና የፍሬ አልባነት አደጋ ያጋጥመዋል’ (‘ወንጌልን ማወጅ’ ቃለ ምዕዳን ቁ. 76)

ስለዚህ ወንጌል የሚሰበክላቸው ሰዎች ሌሎች ሳይሆኑ፣ የሌላ እምነት ተከታዮች ወይም እምነት የሌላቸው ሳይሆኑ፣ ነገር ግን ለራሳችን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ለምንል እና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ብርቱ አባላት መሆኑን ማወቅ አለብን። እኛ በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተካተትን፣ ከሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባውን ኅብረት እና እንደዚሁም መለኮታዊ ፍጽምናን ለመመስከር የተጠራን ነን። ይህን ለመመስከር ቤተ ክርስቲያን ራሷን በቅዱስ ወንጌል ማነጽ መጀመር አለባት። በእርግጥም፣ ማመን ያለባትን ነገር ሳታቋርጥ ማዳመጥ አለባት። የተስፋዎችዋ ምክንያቶችን እና አዲሱን የፍቅር ትዕዛዝ ማዳመጥ አለባት። ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ የምትገኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ናት። ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጣዖቶች የምትፈተን በመሆኗ፣ ወደ ጌታዋ የጠራትን የእግዚአብሔር ተአምራት ሁልጊዜ መስማት አለባት። ዘወትር በእርሱ መጠራት እና ከእርሱ ጋር አንድ መሆን አለባት። ባጭሩ ይህ ማለት፣ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ንቁ ሆና ወንጌልን ለመመስከር እና ጥንካሬን ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ የማያቋርጥ የወንጌል አገልግሎት ፍላጎት ሊኖራት ይገባል ማለት ነው። (‘ወንጌልን ማወጅ’ ቃለ ምዕዳን ቁ. 15)

በመንፈስ ቅዱስ ለምትመራ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን የምትመሰክር ቤተ ክርስቲያን ራሷን በወንጌል የምታዘጋጅ እና ቀጣይነት ባለው የመለወጥ እና የመታደስ ጎዳና የምትራመድ መሆን ይጠበቅባታል። ቀጣይነት ያለው የመለወጥ እና የመታደስ ጎዳና እንድትጓዝ የሚጠበቅባት ቤተ ክርስቲያን ናት። ይህ ደግሞ የመረዳት መንገዶችን የመቀየር እና በታሪክ ውስጥ ያለውን የወንጌል አገልግሎት በተግባር የመኖር ችሎታን እና ‘ሁልጊዜ በዚህ መንገድ ስናከናውን ኖረናል’ በሚለው አመክንዮ በመታገዝ ራስን መከላከልን ማስወገድን ይጨምራል። ይህች ቤተ ክርስትያን ሙሉ በሙሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰች፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ባለው የማዳን እቅድ ውስጥ ተሳታፊ የሆነች እና እንደዚሁም ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደ ሰው ልጆች የመለሰች ናት። ከዓለም ጋር በውይይት የምትገናኝ፣ የወንድማማችነት ግንኙነትን የምታክሂድ፣ የእርስ በርስ መገናኛ መድረኮችን የምታመቻች፣ ለእንግዶቿ መልካም አቀባበል የምታደርግ፣ ከሌሎች ጋር ላላት አንድነት እና ልዩነት እውቅናን የምትሰጥ፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እና በውስጧ ለሚገኙት ፍጥረታት በሙሉ የምትጨነቅ ቤተ ክርስቲያን ናት።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! በቤታችሁ እና በማኅበረሰባችሁ ውስጥ ‘ወንጌልን ማወጅ’ የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንድታነቡት ግብዣዬን በድጋሚ አቀርባለሁ።”

22 March 2023, 16:16