ፈልግ

ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን - አቢጃን ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን - አቢጃን  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በውሃ ምክንያት ሊነሱ የሚችሉ ጦርነቶችን ማስቀረት እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፈዋል። ቅዱስነታቸው ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ውሃ መሠረታዊ በመሆኑ በማስታወስ፣ ሊባክን እንደማይገባ እና በፍፁም ለጦርነት ምክንያት ሆኖ መቅረብ እንደሌለበት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በየዓመቱ መጋቢት 22 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን፣ ውሃ ለሰው ልጅ ቀዳሚ እና መሠረታዊ ፍላጎት መሆኑ እና በዓለማችን ሁለት ቢሊዮን ሰዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኙ ግንዛቤ የሚሰጥበት ቀን ነው።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ለማስገንዘብ ባስተላለፉት የዘንድሮ መልዕክታቸው፣ “ውሃ በፍፁም የሚባክን፣ አለአግባብ የሚጠቀሙት እና የጦርነት ምክንያት መሆን የለበትም” ብለው፣ “ለዛሬው እና ለመጪው ትውልድ ጥቅም ሲባል ተጠብቆ መቀመጥ አለበት” በማለት አሳስበዋል።

ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ያቀረቡትን ሳምንታዊው ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለታደሙት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፣ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ፣ ውዳሴ ላንተ ይሁን ባለው የምስጋና ጸሎቱ፣ "ጌታዬ ሆይ፣ ይህን እጅግ ጠቃሚ፣ ትሑት፣ ውድ እና ንፁህ የሆነች እህት ውሃን ስለሰጠኸን ተመሰገን!” ማለቱን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ “ቅዱስ ፍራንችስኮስ በእነዚህ ቀላል ቃላት በኩል የፍጥረትን ውበት እና ሊደረግለት በሚገባው እንክብካቤ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን እንድንገነዘብ ያሳስበናል" ብለው፣ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ጉባኤ በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ጉባኤ (እ. አ. አ 2023)

ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. በተጀመረው የሦስት ቀናት የውሃ ጉባኤ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ልዑካን ይሳተፋሉ። "ለጉባኤው ስኬታማነት እጸልያለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አስፈላጊነቱ የታመነበት ይህ ጉባኤ በውሃ እጥረት ለሚሰቃዩ ሰዎች ድጋፍን ለመስጠት የተጀመረውን እቅድ እንደሚያፋጥነው ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ “ውሃ ለሰው ልጅ ጥቅም ቀዳሚ ነው" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ታላቁ የውሃ ጉባኤ አስቀድሞ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ያለውን የውሃ ቀውስ እና ከአቅም በላይ በሆነ ፍጆታ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የውሃ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል። ሪፖርቱ አክሎም፣ ዓለም አደገኛውን መንገድ በጭፍን እየተጓዘ መሆኑን ገልጾ፣ በውሃ ላይ ከሚያስፈልገው መጠን ያለፈ ፍጆታ መታየቱን አስታውቋል።

22 March 2023, 16:42