ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችን በቫቲካን ተቀብለዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችን በቫቲካን ተቀብለዋል   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ "በጨለማ ውስጥም እግዚአብሔር ከእኛ አለ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፖላንድ ውስጥ በሚገኙ ሁለት የማዕድን ማውጫዎች ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦችን ዓርብ መጋቢት 15/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው፣ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን በሙሉ በጸሎት አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሚያዚያ ወር 2014 ዓ. ም. በደቡባዊ ፖላንድ በሚገኙ ሁለት የከሰል ማዕድን ማውጫዎች ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ፣ በአንድ ሳምንት ብቻ 18 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሁለቱ አደጋዎች የተጎዱ ቤተሰቦች አባላትን ዓርብ መጋቢት 15/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው አጋርነታቸውን ገልጸው፣ የአደጋው ሰለባዎችን በሙሉ በኅብረት በጸሎት አስታውሰዋል። ፒኒዮክ በተባለች ደቡባዊ ፖላንድ የማዕድን ማውጫ ሥፍራ ሚያዝያ 12/2014 ዓ. ም. በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በመፈነዳው ጋዝ አሥር ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ከሦስት ቀናት በኋላ ቦረይኒያ-ዞፊዮውካ ሌላ የማዕድን ማውጫ ሥፍራ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።  

የዝምታ የተገለጸ የርኅራሄ ስሜት

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሟች ቤተሰቦችን ለጉብኝታቸው ካመሰገኑኗቸው በኋላ የአደጋው ሰለባዎችን በሙሉ በርኅራሄ ልብ በዝምታ ጸሎት ማስታወሳቸውን ገልጸው፣ ዝምታ የርኅራሄ ስሜት የሚገለጽበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ከአደጋው ሰለባዎች መካከል አንዳንዶቹ እስከ ዛሬ ድረስ በማዕድን ማውጫዎቹ ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ ገልጸው፣ ባልን ወይም የልጆች አባትን በእንደዚህ ዓይነት አደጋ ማጣት እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር “በቃላት ባልገልጽም ያለኝን ልባዊ ቅርበት፣ በዚህ አስቸጋሪ እና ክፉ በሆነ ሁኔታ መካከል በጸሎት አብሬአችሁ መሆኔን አረጋግጥላችኋለሁ” ብለዋል። “አንዳንድ ጊዜ በተለይም እንደነዚህ ባሉ ጊዜያት፣ እግዚአብሔር የማይሰማን ሊመስለን ይችላል" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሙታን ዝምታ እና እንደዚሁም የእግዚአብሔር ዝምታ እንዳለ ገልጸው፣ ይህ ዝምታ አንዳንድ ጊዜ በውስጣችን የቁጣ ስሜትን ሊፈጥርብን እንደሚችል አስረድተዋል።

“ቁጣው በራሱ ጸሎት ነው” በማለት በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦችን ቅዱስነታቸው አጽናተዋል። ቁጣው እነዚህን በመሳሰሉ ሁኔታዎች መካከል ስንገኝ፥ “ይህ ለምን ሆነ?” ብለን የምናቀርበው ጥያቄ አካል እንደሆነ ገልጸው፣ መልሳችንም፣ እንዴት እንደሆነ ባናውቅም፥ "በጨለማ ውስጥም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው!” የሚል እንደሆነ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው እንግዶቹ በጸጥታ አብረዋቸው እንዲጸልዩ ጋብዘው፣ ከእያንዳንዱ እንግዳ ጋር ሰላምታ ከመለዋወጣቸው በፊት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

የአደጋው መንስኤ ፍለጋ

የፖላንድ ፍርድ ቤት የአደጋውን ምክንያት የሚያጣራ ወገን በማቋቋም ምርመራዎችን እያካሄደ ሲሆን፣ የሁለቱንም የማዕድን ማውጫዎች የደህንነት ሁኔታን እየተከታተለ እንደሚገኝ ታውቋል። አብዛኛው የፖላንድ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማውጫ ቦታዎች በደቡባዊው የሲሊሲያ ክልል ሀገር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ከፍተኛ የሜቴን ጋዝ መጠን ያለባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ይነገራል። ከዚህ በፊትም በግንቦት ወር 2010 ዓ. ም. ዞፍሎካ በተባለ የማዕድን ማውጫ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አምስት ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

25 March 2023, 15:41