ፈልግ

መጣሊያን የተለያዩ ትርኢቶችን በማቅረብ የሚያዝናና የጎጋና ላይ አርቲስቶች ብሔራዊ ማኅበር መጣሊያን የተለያዩ ትርኢቶችን በማቅረብ የሚያዝናና የጎጋና ላይ አርቲስቶች ብሔራዊ ማኅበር   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የጎዳና ላይ አርቲስቶች በብቸኝነት ዓለም ውስጥ ደስታን እንደሚያመጡ ገለጹ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በጎዳናዎች የተለያዩ ትርኢቶችን በማቅረብ ሕዝብን የሚያዝናና የአርቲስቶች ብሔራዊ ማኅበር አባላትን መጋቢት 11/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በአደባባይ የሚቀርብ ትርኢት አስፈላጊነትን በማስመልከት ለማኅበሩ አባላት ባደረጉት ንግግር፣ በርካታ ሰዎች ከተንቀሳቃሽ ስልካቸው ወይም ኮምፒዩተራቸው ጋር ብቻ ከሚያሳልፉት ጊዜ በተቃራኒ ከመኖሪያቸው ውጭ ከሚያገኟቸው ሰዎች ጋር እውነተኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል የጥበብ ዘርፍ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተሽከርካሪዎች ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በተለያዩ ትርኢቶች ሕዝብን የሚያዝናኑ የጥበብ ስዎች በሚያስገኙት ደስታ ወንጌልን በመስበክ በሰፊው የሚተባበሩ መሆናቸውን በቫቲካን በሚገኝ ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ለተቀበሏቸው የጣሊያን ተጓዥ አርቲስቶች ብሔራዊ ማኅበር አባላት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ከተሞች እና መንደሮች ውስጥ እየዞሩ የአዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜና እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ከሚያውጁት ጎን  መሆኑና አረጋግጠው፣ እነዚህ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቀሰው ትርኢቶቻቸውን የሚያሳዩ የጥበብ ሰዎች ደስታን የሚዘሩ በመሆናቸው ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።  

ለአርቲስቶቹ ባደረጉት ንግግር፥ “ጥሪያችሁ ደስታን መዝራት ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አርቲስቶቹ ልባቸውን እና ሕይወታቸውን ሁል ጊዜ ለእምነታቸው ክፍት እንዲያደርጉ አደራ ብለው፣ በዚህ መንገድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመገናኘት በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ፣ በመካከላቸው እና በየቦታው በሚያገኟቸው ሰዎች መካከል ደስታን በመፍጠር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ ማድረጋቸውን አስረድተው፣ ከመልካም ሥራዎች መካከል አንዱ በሰዎች መካከል ደስታን መፍጠር በመሆኑ ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።    

በመንደሮች እና በከተሞች ውስጥ የሚያሳዩት ትርኢቶች በልጆች እና በጎልማሶች ልብ ውስጥ ደስታን እንደሚፈጥርላቸው የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህም ዕለት ተዕለት በሕይወታቸው ከሚያጋጥማቸው ጭንቀቶች እንዲወጡ እንደሚያደርግ አስታውሰው፣ በሕጻናት አእምሮ እና በሁሉም የቤተሰብ ልብ ንጹሕ ደስታን የሚሰጥ መሆኑን አስታውሰዋል።

ደስታ የሚገኘው እራስን ዝቅ በማድረግ ነው

በመንደሮች እና በከተሞች ውስጥ በሚቀርቡ ትርኢቶች አማካይነት የሚሰራጩ የደስታ ስሜቶች ከፈጠራ ሥራዎች እና ከልበ ወለድ እንደሚመጡ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ ስሜቶች በብዙሃን መገናኛዎች በኩል የሚሰራጩትን እና ዘወትር አዳዲስ ስሜቶችን የሚፈልጉ ሞዴሎችን የማይከተሉ እንደሆኑ አስረድተው፣ ይልቁንም ሰዎች በርከት ብለው በሚገኙባቸው በቀላል እና እውነተኛ የመዝናኛ ሥፍራዎች የሚፈጠሩ ስሜቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የጥበብ ሥራቸው ብዙውን ጊዜ የሰዎች ስሜት ከብዶ በሚታይበት እና ችግር በሚተነፈስበት ዓለም ውስጥ እንደሚቀርብ የተናገሩት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ደስታ የሚገኘው እራስን ዝቅ በማድረግ እንደሆነ አስታውሰው፣ በከተሞች እና በመንደሮች የሚያሳዩአቸው ትርኢቶች፣ ዛሬ በብዛት ከምናየው እና በርካታ ሰዎች ከእርስ በእርስ ግንኙነት ተለይተው ከተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው እና ኮምፒውተሮች ጋር ብቻ ከሚሆኑበት መንገድ ወጥተው በአደባባይ እንዲገናኙ እና አብረው እንዲዝናኑ የሚጋብዙ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጎዳናዎች የተለያዩ ትርኢቶችን በማቅረብ ሕዝብን ለሚያዝናና ብሔራዊ የአርቲስቶች ማኅበር አባላት ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃለሉ፣ “ይህ ሁሉ የሚያስገነዝበን የተፈጠርነው ለሥራ ብቻ ሳይሆን ለመዝናናትም ጭምር ነው” በማለት አስተያየታቸውን በመስጠት፣ በወንድማማችነት እና በቅንነት አብረን ስንደሰት እግዚአብሔርም ደስ ይለዋል” በማለት ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው በቫቲካን ውስጥ ከተቀበሏቸው ብሔራዊ የአርቲስቶች ማኅበር አባላት መካከል፣ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር አባል እና ለረጅም ዓመታት ሮም ከተማ በሚገኙ የመዝናኛ ፓርኮች ውስጥ ትርኢቶችን በማቅረብ ከሚታወቁ እህት ጄኒኔቭ ዣኒንግሮስ ጋር ተገኝተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዕለቱ የልደት በዓላቸውን 80ኛ ዓመት ላከበሩት እህት ጄኒኔቭ መልካምን ተመኝተው፣ በአዳራሹ ውስጥ ከተገኙት የማኅበሩ አባላት ጋር የመልካም ምኞት መዝሙርን በመዘመር እንግዶችን ተሰናብተዋል። 

21 March 2023, 15:56