ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በማርሴ መልካም ዝንባሌ እና ጉጉት እንዳለ መመልከታቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 16/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች፥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በፈረንሳይ ማርሴ ከተማ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድርገዋል። ጣሊያንን ጨምሮ ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ በማርሴ ውስጥ ከተደረገው ስብሰባ እና ከአካባቢው ሕዝብ መልካም ዝንባሌን እና ጉጉትን ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ክቡራት እና ክቡራን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 16/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ም ዕመናን የደረጉትን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች! ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የፈረንሳይ ከተማ በሆነች ማርሴ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ፥በሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳትን እና ከተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች እንዲሁም ከበርካታ ወጣቶች ጋር በመሆን የሜዲቴራንያን አካባቢ አገራት ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ተገኝቻለሁ። በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ወቅት የአካባቢው አገራት ሕዝቦች የወደፊት አመለካከት  ክፍት መሆኑን ተረድቻለሁ። በእውነቱ በማርሴ ከተማ የተካሄደው ስብሰባ ተስፋ ያለበት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።ፈተናዎች ቢኖሩም ዘወትር ተስፋን ማለም ይቻላል። የሜዲትራኒያን ባሕር ከደረሰበት ቀውስ በማገገም የስልጣኔ እና የሰላም ቤተ ሙከራ የመሆን ጥሪውን መልሶ ማግኘት ይችላል።

እንደምናውቀው የሜዲትራኒያን ባሕር አካባቢ የስልጣኔ እና የሕይወት መገኛ ነው። ነገር ግን ዛሬ የመቃብር እና የግጭት ስፍራ መሆን የለበትም። የሜዲትራኒያን ባሕር በስልጣኔዎች መካካል ጦርነት ከሚካሄድበት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚካሄድበት ሥፍራ ፈጽሞ የተለየ ነው። የሜዲትራኒያን ባሕር በአፍሪካ፣ በእስያ እና በአውሮፓ መካከል የመገናኛ መንገድ በመሆኑንም ጭምር ፍጹም የተለየ ነው። በሰሜን እና በደቡብ ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ፣ በሰዎች እና በባሕሎች ፣ በሕዝቦች እና በቋንቋዎች ፣ በፍልስፍና እና በሃይማኖቶች መካከል ግንኙነት እንዲኖር የሚያግዝ ነው። እርግጥ ነው! ባሕር ውስጥ ከወደቁ አሸንፈው የሚወጡት ገደል ነው፤ አልፎ ተርፎም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ውኃው ግን ሕይወትን ይጠብቃል፣ ይንከባከባል። ማዕበሉ እና ነፋሱ ሁሉን ዓይነት መርከብ እንዲንቀሳቀስ ያግዛል።

ከምሥራቃዊው የባሕር ዳርቻ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ወንጌል ወደ ዓለም ዳርቻዎች ተሰራጨ። በእርግጥ ይህ የወንጌል ስብከት እንዲሁ ተፈጽሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚከናወን አይደለም። እያንዳንዱ ትውልድ የሚኖርበትን ዘመን ምልክቶች እያነበበ በትንሽ በትንሹ እንዲጓዙት የሚጋብዝ ጉዞ ፍሬ ነው።

በማርሴ ከተማ የተካሄደው ስብሰባ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2020 ዓ. ም. በጣሊያን ባሪ ከተማ እንዲሁም ያለፈው ዓመትም በጣሊያን ፍሎረንስ ከተማ ከተካሄዱ ተመሳሳይ ስብሰባዎች ቀጥሎ የተካሄደ ነው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1950ዎቹ መገባደጃ ላይ የፍሎረንስ ከንቲባ በሆነው በጆርጆ ላ ፒራ በተዘጋጀው “የሜዲትራኒያን ስብሰባ” የተጀመረ እርምጃ እንጂ የተለየ አልነበረም። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ “የሕዝብ ልማት” በተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ፥ “የሚሰጥ እና የሚቀበል ማኅበረሰብ፥ የአንዳንድ ሰዎች ዕድገት ሌሎች በከፈሉት ዋጋ የማይገዛበት የበለጠ ሰብዓዊነት የሰፈነበትን ዓለምን ማስተዋወቅ ይገባል” በማለት ላቀረበው አቤቱታ ዛሬ ምላሽ ለመስጠት አንድ እርምጃ ነው። (“የሕዝብ ልማት” ቁ. 44)

ከማርሴ ስብሰባ ምን ሊገኝ ይችላል? ከማርሴ ስብሰባ ሊገኝ የሚችለው በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ባለን አመለካከት፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ስትራቴጂ ወይም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን በቀላሉ ሁሉንም ነገር ወደ የሰው ልጅ ቀዳሚ እሴት እና ወደማይደፈርሰው ክብር የማመልከት ችሎታ ያለው ሰብዓዊነት ነው።ከዚያም በተመሳሳይ መንገድ ተስፋ ያለው አመለካከት ሊገኝ ይችላል። ኢሰብአዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የኖሩት ወይም የተጋሩት ሰዎች የሚሰጡትን ምስክርነት ስትሰሙ፥ ዛሬ እነርሱ ራሳቸው በወንድማማችነት አመለካከታቸው "ተስፋ ፈጣሪዎች" በመሆን የሚሰጡትን ምስክርነት ስትሰሙ ይህ ያስደነቃል፥ 

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ይህ ተስፋ፣ ይህ ወንድማማችነት ከንቱ ሆኖ መቅረት የለበትም። ይልቁንም ሰዎች ፍጹም ክብር ባለው መልኩ መሰደድን ወይም አለመሰደድን እንዲመርጡ በረጅም፣ በመካከለኛ እና በአጭር ጊዜ ዕቅድ መደራጀት ያስፈልጋል። የሜዲትራኒያን ባሕር የተስፋ መልዕክት መሆን አለበት።

ነገር ግን ሌላ ተጨማሪ ገጽታ አለ። ተስፋ ለአውሮፓ ማኅበረሰብ በተለይም ለአዲሱ ትውልድ ተመልሶ መምጣት አለበት። እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ ራሳችን ስለ ወደፊቱ ጊዜ የመረዳት ችሎታ ከሌለን ሌሎችን እንዴት መቀበል እንችላለን? በተስፋ ድሆች የሆኑ፣ በግል ሕይወታቸው የተዘጉ፣ የራሳቸዉን ስጋት ለመቆጣጠር የሚጨነቁ ወጣቶች፣ ከሌሎች ጋር ለመገናኘት እና ለመካፈል እንዴት ራሳቸውን መክፈት ይችላሉ? ኅብረተሰባችን ብዙውን ጊዜ በግለኝነት እና በጥቅም የታመመ ነው። ነፍሳቸውን እና መንፈሳቸውን በንጹሕ አየር መፈወስ አለባቸው፣ የወደቁበትን ቀውስ እንደ አጋጣሚ የሚያውቁት ከሆነ በአዎንታዊ መልኩ መቋቋም ይችላሉ።

አውሮፓ መልካም ተነሳሽነት እና ዝንባሌ ሊኖረው ይገባል። በማርሴ ውስጥ ከተደረገው ስብሰባ መልካም ዝንባሌን እና ጉጉትን አገኝቻለሁ ማለት እችላለሁ። ካርዲናል አቬሊን፣ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማሩት ሠራተኞች ለትምህርት በሚሰጡት ታማኝነት፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሳዩት መንፈሳዊነት ከፍተኛ ዝንባሌን እና ጉጉትን አገኝቻለሁ ማለት እችላለሁ። የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኤማኑኤል ማክሮንን እና የፈረንሣይ ሕዝብ በሙሉ በማርሴ ለተደረገው ዝግጅት ትኩረት ሰጥተው እንደነበር መስክረዋል። የማርሴይ ከተማ ነዋሪዎች፥ “የክርስቲያኖች ጠባቂ” በማለት የሚያከብሯት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ የሥልጣኔ እና የተስፋ አካባቢ ተብሎ የሚጠራው የሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት ሕዝቦችን በጉዞአቸው ወቅት ዘወትር ትርዳቸው።”

 

 

 

27 September 2023, 16:59