ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከደቡብ እስያ አገራት ተማሪዎች ጋር ያደረጉት የአውታረ መረብ ላይ ውይይት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከደቡብ እስያ አገራት ተማሪዎች ጋር ያደረጉት የአውታረ መረብ ላይ ውይይት 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የእስያ ወጣቶች ከርዕዮተ ዓለም ይልቅ የስምምነት ምስክሮች እንዲሆኑ አሳሰቡ

በሰሜን አሜሪካ ቺካጎ ከተማ የሚገኝ ሎዮላ ዩኒቨርሲቲ እና በላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ኮሚሽን አስተባባሪነት በተዘጋጀው መድረክ በሕንድ፣ በኔፓል እና በፓኪስታን ከሚገኙ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ አሥራ ሁለት ተማሪዎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የአውታረ መረብ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ማክሰኞ መስከረም 15/2016 ዓ. ም. ከወጣቶቹ ጋር ያካሄዱት ሲኖዶሳዊ ውይይት መሠረት ያደረገው፥ የሃይማኖት ነጻነት እና የወንጌል ምስክርነት፣ ጉልበተኝነት፣ የወጣቶች ራስን ማጥፋት፣ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች አጠቃቀም እና የሚዲያ እውቀት የሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ያተኮረ እንደ ነበር ተመልክቷል። ቅዱስነታቸው በዚህ ውይይት መካከል ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የእስያ ወጣቶች በአኅጉሪቱ ውስጥ በሚገኙ ልዩነቶች መካከል ስምምነትን እና መግባባትን መፍጠር ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል።

የክርስቲያን ቁጥር አናሳ በሆኑባቸው የደቡብ እስያ አገራት ማለትም  ከሕንድ፣ ከኔፓል እና ከፓኪስታን ካቶሊክ ዩንቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተማሪዎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ባደረጉት የአውታረ መረብ ላይ ውይይት፥ በማኅበረሰቦቻቸው ውስጥ ስለሚደርስባቸው አድልዎ፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ስደት፣ አንዳንድ ጊዜ አክራርነትም መኖሩን ተናግረዋል። ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ከቅዱስነታቸው ጋር ባደረጉት ብርቱ ውይይት፥ ስለወደፊት ሕይወት ያላቸውን ሕልም፣ እምነታቸውን በነጻነት መመስከር ያለ መቻል እና በዚህም እንደሚጨነቁ አስረድተዋል።

“የእርስ በርስ መገናኛ ድልድይ መገንባት” በሚል መሪ ርዕሥ፥ በላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና በቺካጎ የሎዮላ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ እና ማኅበረሰብ ሐዋርያዊ ጥናት ተቋም ተባባሪነት የተዘጋጀው የአውታረ መረብ ላይ ውይይት ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደ ውይይት እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ዓመት በተጀመረው የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ዋዜማ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት ወር 2022 ዓ. ም. ከአሜሪካ ወጣቶች ጋር እና በኅዳር ወር ከአፍሪካ ወጣቶች ጋር ካደረጉት የአውታረ መረብ ላይ ውይይት ቀጥሎ ይህ ከደቡብ እስያ ወጣቶች ጋር ያደረጉት ውይይት ሦስተኛው እንደሆነ ታውቋል።

እስያ ቢቢ፥ ከፍርሃት የተወለደ የአክራሪነት ሰለባ ነች

የሦስቱ ወጣቶች ክርስቲያናዊ ምስክርነት ልባቸውን እንደነካው የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥  የፓኪስታናዊቷ ወጣት የአስያ ቢቢን ስቃይ በማስታወስ፥ አስያ ቢቢ ከፍርሃት፣ ከልዩነት እና ከአድልዎ የተወለደ የአክራሪነት ሰለባ እንደሆነች ገልጸው፥ ለዚህ ሁሉ መንሴው የማኅበራዊ እሴቶች መቀነስ እና መዳከም ነው በማለት አክለዋል።

ባሕላዊ እሴቶች ወደ ርዕዮተ ዓለማዊነት የሚለወጡ ከሆነ ባሕል እንደሚጠፋ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለዚህ ምላሹ ከዓለማዊነት በተቃራኒ፥ “እግዚአብሔር ለእኔ እቅድ አለው የሚለው አስተሳሰብ” ጠንካራ ምስክርነት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ በሰጡት ምክር፥ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ለማወቅ አባቶች የነበራቸውን ድፍረት ማሰብ እንደሚገባ ተናግረው፥ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም በእምነት ከጠንከሩ ሕልምን እውን ማድረግ እንደሚቻል እና ይህም ሁሉ ሰው እንዲያድግ ማገዙን እና የወንጌል ምስክርነትን እየሰጡ ዘወትር ይቅር ባይ መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከሁሉም ጋር እየተግባቡ የራስን እምነት መግለጽ

ከሳንታ ማርታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሮዚታን፥ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የተሰደደችው ወጣት ሮሲታ፥ በምጣኔ ሃብት እና በማኅበራዊ ሳይንስ የተመረቀች ስትሆን፥ አሁን በምትኖርበት አገር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ማንነቷን እንደምታጣ ያደረችበትን ስጋት ገልጻለች። ይህን ስጋት በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሮሲታ በሰጡት ምክረ ሃሳብ፥ የራስን እምነት በተግባር እየገለጹ ከሌሎች ጋር በስምምነት እና በመግባባት መኖር እንደሚገባ ጋብዘዋታል። አባታቸውም ስደተኛ እንደነበሩ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በባዕድ አገር አዲስ ሕይወት ቢጀምሩም ነገር ግን የመጡበትን የባሕል መሠረት መዘንጋት እንደማይገባ አስምረውበታል።

ከጉልበተኝነት ይልቅ ተግባብቶ የመኖር ውበትን ማወቅ ይገባል

በአውታረ መረብ ላይ ውይይት የተሳተፉት ሌሎች ሦስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፥ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ወጣቶች ራስን የማጥፋት አደጋን ጨምሮ የጉልበተኝነት ችግሮችን አስመልክተው ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ባደረጉት ውይይት፥ በሕንድ በሚገኝ ባንጋሎር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኬሚስትሪ ተማሪ ወጣት ሜሪሊን ሮዝ፥ “ኅብረተሰቡ ከሚያስቀምጠው የውበት ደረጃ ላይ አይደለሽም” በማለት ወጣቶች እንደሚሳለቁባት ገልጻለች።

ቅዱስነታቸው ይህን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ውበት እንዳለው ገልጸው፥ ነገር ግን ይህን ውበት በሚገባ በማወቅ፣ ከሰዎች እና ከራስ ጋር ጭምርም መስማማት እንደሚያፍስፈልግ በመናገር፥ የእስያ ወጣቶች በአኅጉሪቱ ውስጥ በሚገኙ ልዩነቶች መካከል ስምምነትን እና መግባባትን መፍጠር ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል።

ወጣቶችን ከወደቁበት እንዲነሱ ማገዝ ያስፈልጋል

“አንድ ወጣት ወደፊት ሊያጋጥሙት የሚችሉ መልካም ዕድሎችን መመልከት ካልቻለ እና ሕልሞቹ በሙሉ የተዘጉ ከመሰሉት ያለው አማራጭ እራሱን ማጥፋት ይሆናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ "መላዕክት እንኳ ከወደቁበት መነሳት ባይችሉም፣ ነገር ግን እኛ ሰዎች ከወደቅንበት መነሳት የምንችልበትን ኃይል እና ችሎታ እግዚአብሔር ሰጥቶናል" የሚለውን በማስታወስ፥ ዋናው ነገር መውደቅ ሳይሆን ነገር ግን ከወደቅንበት ለመነሳት የሚያግዝ ሰው ማግኘት ነው” ብለው፥ የአእምሮ ጤናን የሚሰጥ የውስጥ ሰላምን ፈጽሞ ማጣት እንደማይገባ አሳስበዋል።

እስያ ውስጥ ኢንተርኔትን የተሻለ የግኑኝነት ሥፍራ ማድረግ ያስፈልጋል

በሕንድ ኬረላ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኝ ጆሴፍ እና በባንጋሎር የሕግ ትምህርቷን በመከታተል ላይ የምትገኝ ሜሪ ላቪና፥ በእስያ ውስጥ ስላለው የኢንተርኔት ፈተና እና ወጣቶች ሊኖራቸው የሚገባውን የማኅበራዊ ሚዲያ እውቀት አስፈላጊነትን ሲናገሩ፥ ኢንተርኔት መረጃዎች በስፋት እንዲደርሱ ቢያደርግም፣ ነገር ግን የሃይማኖት፣ የጎሳ እና የፖለቲካ ውዝግቦች እንዲጨምር በማድረጉ፥ የሚያስከትለውን አደጋ ተናግረው፥ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙት መካከል ልዩነት መኖሩን ገልጸዋል። ይህን ፈተና ለማሸነፍ መወሰድ ያለበትን እርምጃ እንዳለ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ፈተናውን ለማሸነፍ የሃሳብ፣ የልብ እና የእጅ ቋንቋ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል። እያንዳንዱ ሰው የብዙ ፈጠራ ባለቤት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው አክለውም፥ “ርዕዮተ ዓለም አእምሮን ሊቀንስ እንደሚችል፥ ልብን እንደሚያሳንስ እና እጅንም ሽባ እንደሚያደርግ አስረድተዋል። ርዕዮተ ዓለሞችን በማስወገድ የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እኩል ተጠቃሚነት ዕድል እንዲኖር ለማድረግ መሞከር እንደሚገባ መክረው፥ ይህም ኢንተርኔትን የተሻለ የአገልግሎት ሥፍራ እንደሚያደርገው በመግለጽ፥ አንዱ ከሌላው ጋር በስምምነት መገናኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለእውነታዎች ታማኝነትን ማሳየት ያስፈልጋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማኅበራዊ ግንኙነት በማስመልከት በሰጡት አስተያየታቸው፥ ግማሽ እውነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረው፥ ዜና ሳይቆረጥ ወይም ሳይቀነስ ለሁሉ ሰው በሙላት መቅረብ አለበት ብለዋል። ለሕዝብ የሚነገር ዜና ለእውነታዎች ታማኝ መሆን አለበት ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አንዳንድ ጊዜ የሐሰት ዜና እንደሚሰራጭ በማስታወስ እውነተኛው ዲሞክራሲ የጋራ ውይይትን እንደሚደግፍ ተናግረዋል። ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚደረግ ጥረት ሰብዓዊነት ይገልጻል ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የልዩነት ቋንቋ የተሳሳተ እንደሆነ በመግለጽ፥ ሁለት ወገኖች በተለያየ መንገድ ቢያስቡም ወደ ስምምነት ካልደረሱ ወደፊት ሊራመዱ እንደማይችል በማስረዳት ከተማሪዎች ጋር የነበራቸውን ውይይት አጥናቅቀዋል።

 

 

 

27 September 2023, 17:08