ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ስደት በሰብዓዊነት እና በአብሮነት መንገድ ሊገለጽ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማርሴ በባሕር ላይ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ መርከበኞችን እና ስደተኞች ለማስታወስ በተደረገው የሕሊና ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደርጉት ንግግር፥ በሜድትራኒያንያ አካባቢ አገራት ዘንድ የሚታዩ አሳዛኝ የስደት ዘመን ተግዳሮቶች ሰብዓዊነትን እና አብሮነትን በተላበሰ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማርሴ ከተማ ዓርብ ማምሻውን በ "ኖትሬዳም ዴ ላ ጋርዴ" ባዚሊካ ፊት ለፊት በሚገኝ ሐውልት ዙሪያ ባደርጉት ሁለተኛ ስባሰባ ላይ፥ ለስደተኞች እርዳታን በማቅረብ ላይ ከሚገኙ የገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም የምዕመናን መንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች ጋር አንድ ላይ በመሆን በባሕር ላይ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ መርከበኞችን እና ስደተኞች በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

በኖትር ዴም ዴ ላ ጋርዴ ባዚሊካ ፊት ለፊት በቆመው የመታሰቢያ ሐውልት ዙሪያ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል  መንግሥታዊ ያልሆነው የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የ“ማርሴ ኢስፔራንስ” አባላት፣ ስቴላ ማሪስ የተባለ ካቶሊካዊ ድርጅት፣ ካሪታስ ጋፕ-ብሪያንሰ፣ የሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና የሌሎች ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

በሜዲትራኒያ ባሕር ውስጥ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር ብቻ አይደሉም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በሥፍራው ለተሰበሰቡት እንግዶች ባደረጉት ንግግር፥ የሜዲትራኒያን ባሕር ወደ “መቃብርነት” የቀየረውን የስደት አሳዛኝ ክስተት በቃላት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ እርምጃ መፍታት እንደሚገባ ደግመው አሳስበዋል። የተሻለ መፃኢ ዕድል ለማግኘት ሲሉ በባሕር ላይ ሕይወታቸውን የሚያጡ ስደተኞች፥ በቁጥር ብቻ የሚገለጹ ሳይሆን ለግጭት፣ ለድህነት እና ለአካባቢ አደጋዎች የተጋለጡ መልክ እና ስም ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን አስምረውበታል።

“የመርከብ ላይ አደጋን እንደ ዜና፥ በባሕር ላይ የሚደርሰውን ሞት በቁጥር መግለጽን አንልመድ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህ ለአደጋው የተጋለጥት ሰዎች መጠሪያ ስሞች፣ መልክ እና ታሪክ ያላቸው፣ ሕይወታቸው እና ሕልሞቻቸው የተሰበረባቸው ሰዎች ናቸው” ብለዋል።

የሰብአዊነት እና የአብሮነት ግዴታ

በዚህ የስደት ዘመን፥ ስደተኞች ከአፍሪካ አገር ጊኒ ወደ አውሮፓ የሚያደርጉትን አደገኛ ጉዞን በሚተርክ   “ትንሹ ወንድም” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ስደተኞች በሕይወት እና በሞት መካከል እንደሚገኙ እና የአውሮፓ አገራት በስልጣኔ መንታ መንገድ ላይ መቆማቸውን አስረድተዋል።

በአንድ በኩል ማኅበረሰብ በመልካምነት እንዲያብብ የሚያደርግ ወንድማማችነት መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በሌላ በኩል የሜዲትራኒያን ባሕርን የሚያደማ የግድየለሽነት ባሕል መኖሩን ተናግረው፥ በባሕር ላይ አደጋ የሚሞቱ ሰዎችን ማዳን የሰብዓዊነትም የስልጣኔም ተግባር መሆኑን አበክረው  ተናግረዋል። “በየብስ እና በባሕር ላይ የሚጓዙ ደካሞችን እንዴት መንከባከብ እንዳለብን ካወቅን፥ በሞት የሚቀጣውን ፍርሃት እና ቸልተኝነት ማሸነፍ ከቻልን፥ በዚህ እግዚአብሔር ይባርከናል" ብለዋል።

“የሰው ልጅ መደራደሪያ ሆኖ ሲቀርብ፣ ሲታሰር እና ሲሰቃይ በዝምታ መመልከት  አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በጭካኞች፣ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና በግዴለሽ ጽንፈኝነት ምክንያት የሚከሰተውን የመርከብ አደጋን በዝምታ መመልከት አንችልም” ብለዋል። “ለማዕበል አደጋ የተጋለጡ ሰዎችን መታደግ የሰው ልጅ የስልጣኔ ግዴታ ነው!" በማለት አስረድተዋል።

በሜዲትራኒያን ባሕር አካባቢ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት አርአያ እንዲሆኑ የጠርተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል “የስደት ቀውስን ለመቅረፍ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች በተለይም ሦስቱ የሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት አብርሃማዊ የእምነት ተቋማት እንግዳን በእግዚአብሔር ስም በፍቅር ተቀብለው ለማስተናገድ ተጠርተዋል ብለዋል። “እኛ አማኞች በወንድማማችነት አቀባበል አርአያ መሆን አለብን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የማኅበረሰቡን ትክክለኛውን ሕይወት የሚያበላሽ የአክራሪነት ርዕዮተ ዓለምን መቅሰፍት” በማለት ወቅሰዋል።

ማርሴይ ልዩ ልዩ ተስፋ ያለበት አካባቢ

በተለይም የፈረንሳይ የወደብ ከተማ ማርሴ "በመንታ መንገድ ላይ የምትገኝ" በማለት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የማርሴን ውስብስብ የመድብለ-ባሕል እና ሃይማኖታዊ እውነታን በመጥቀስ፥ ዛሬ እየጨመረ የመጣውን ማኅበራዊ ውጥረት የምትጋፈጥ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስደተኞችን በመርዳት እና በማኅበረሰቦች መካከል ሰላማዊ አብሮነትን በማስፈን ላይ የተሳተፉ በርካታ ድርጅቶችን እና በተለይም መንግሥታዊ ያልሆኑ የሃይማኖት ድርጅቶች ላከናወኗቸው መልካም ተግባራት አወድሰዋል ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የሐይማኖት ድርጅቶችን፥ "የማርሴ የወደፊት ተስፋዎች ናችሁ" ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የማርሴ ከተማ ለፈረንሣይ፣ ለአውሮፓ እና ለዓለም የተስፋ ምልክት እንድትሆን በመመኘት ተስፋን ሳይቆርጡ ወደፊት እንዲጓዙ አደራ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ፈረንሳዊው አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር ጁልየስ ይስሐቅ፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአይሁድ እና በክርስትና እምነቶች መካከል ግንኙነትን ለማሳደግ ባደረገው ጥረቱ “የውይይት ምስክርነቶች ፈር ቀዳጅ” ብለውታል።

አብረን ለሰላም እንሥራ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ አውሮፓ በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ የጅምላ ስደትን በማስከተል ላይ ያለውን ወቅታዊ የስደት ተግዳሮት ለመግታት ጥረት እንደምታደርግ እና የልዩነት ግንቦችን አፍርሳ የአንድነት ድልድይ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ ያላቸውን እምነት ገልፀው፥

የሟቹን የቀድሞ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት አቶ ዴቪድ ሳሶሊ፥ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ2020 ዓ. ም. የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በባሪ ከተማ “ሜዲትራኒያን የሰላም ድንበር” በሚል ርዕሥ  በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ያቀረበውን ተማጽኖ አስታውሰው፥ “ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ!፥ እነዚህን የስደት ቀውሶችን በጋራ በመጋፈጥ የመርከብ አደጋን ተስፋ ሳናደርግ ነገር ግን አብረን ለሰላም እንሥራ!" በማለት ተማጽኖ አቸውን አቅርበዋል።

 

23 September 2023, 16:27