ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ማርሴ ከተማ ደረሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፈረንሳይ ውስጥ የወደብ ከተማ በሆነች ማርሴ የሚካሄዱትን የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርብ መስከረም 11/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ጀምረዋል። በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከመስከረም 6 እስከ መስከረም 12/2016 ዓ. ም. ድረስ ሲካሄድ የቆየው የሜዲቴራኒያ አገራት ስብሰባ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዳሜ ምሽት ወደ ቫቲካን ከማቅናታቸው በፊት ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት አቶ ኤማኑኤል ማክሮን ጋርም እንደሚገናኙ እንዲሁም ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር የሚደረገውን የኅብረት ጸሎት እንደሚመሩ እና ቀጥለውም የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ይገልጻል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን 44ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ዓርብ መስከረም 11/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጀምረው በማርሴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል። የሜዲትራኒያ ባሕር አካባቢ አገራት በተለያዩ ከተሞች በየዓመቱ የሚያካሂዱት ስብሰባ ዋና ዓላማ፥ በክልሉ ተግዳሮቶች ላይ ለመወያየት በተለይም ስደትን በማስመልከት ለሚነሱ ችግሮች የጋራ መፍትሄዎችን ለማግኘት ያለመ እንደሆነ ይታወቃል።

ዘንድሮ በማርሴ ከተማ የሚካሄደው የሜዲትራኒያ ባሕር አካባቢ አገራት ስብሰባ ወደ 70 የሚጠጉ የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳትን እና 120 ወጣቶችን የሚያሳትፍ ሲሆን፣ ወጣቶቹ ከ20 እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች እንደሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ማርሴ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በፈረንሳይ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሴልስቲኖ ሚሊዮሬ እና በቅድስት መንበር የፈረንሳይ አምባሳደር ወይዘሮ ፍሎረንስ ማንጂን አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ማርሴ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በሥፍራው ሲጠባበቁ የነበሩ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ኤልሳቤጥ ቦርን እና ወታደራዊ ዘብ የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል። አራት ሕጻናት ለቅዱስነታቸው የአበባ እቅፍ እና በ7ኛው ክፍለ ዘመን የደቡባዊ ፈረንሳይ ጳጳስ የነበረሩ የታዋቂው ቅዱስ ኤሊጂየስ ምስል በስጦታ አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም፥ በ "ኖትሬዳም ዴ ላ ጋርዴ" ባዚሊካ ውስጥ ከሀገረ ስብከቱ ካኅናት ጋር በመሆን ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ጸሎት ካቀረቡ በኋላ፥ በባሕር ላይ ጉዞ ሕይወታቸውን ያጡ መርከበኞችን እና ስደተኞች በሚያስታውስ ሐውልት ፊት ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የአጭር ጊዜ የሕሊና ጸሎት አድርሰዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ መሠረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2014 ጀምሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ የሜዲትራኒያንን ባሕር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሚያደርጉት ሙከራ ከ28,000 በላይ ስደተኞች ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. እስካሁን 180,000 የሚሆኑ ስደተኞች መመዝገባቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም ስደተኞችን ወደ ሥፍራው ሲደርሱ ተቀብለው ከሚያስተናግዱ ማኅበራት ተወካዮች ጋር እና በሜዲትራኒያ ባሕር አካባቢ አገራት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከመጡ የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።

ቅዱስነታቸው በማርሴ ያደረጉትን የመጀመሪያ ቀን ጉብኝት ሲያጠቃልሉ በከተማው ሊቀ ጳጳስ መኖሪያ ቤተ በተዘጋጀላቸው የእንግዳ መቀበያ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

 

23 September 2023, 16:21