ፈልግ

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የፊት ለፊት ገጽታ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የፊት ለፊት ገጽታ  

ከ16ኛው የሲኖዶስ ጉባኤ ቀደም ብሎ የአብያተ ክርስቲያናት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ 16ኛውን የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን ለመንፈስ ቅዱስ በአደራ በሚሰጡት የመስከረም 19/2016 ዓ. ም. የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

16ኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚቀርበውን የጸሎት ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚመሩት ታውቋል።

በዚህ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቁስጥንጥንያው የክርስቲያኖች ተውህዶ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ የሚገኙ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን በደስታ ስትገጽ፥ በተጨማሪም በእንግሊዝ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን ዌልቢ፣ ሌሎችም በርካታ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ከልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን እንደሳተፉ ታውቋል።

ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. ማታ የሚቀርበው የዋዜማ ጸሎት ዓላማ፣ ከመስከረም 23 - ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የሚካሄደውን 16ኛውን የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ለመንፈስ ቅዱስ በአደራ ለመስጠት የታሰበ ሲሆን፥ በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ቃለ እግዚአብሔርን ማዳመጥ፣ የምስጋና እና የምልጃ ጸሎት እንድሁም አስተንትኖን ጨምሮ በታይዘ ማኅበረ ክርስቲያን የተዘጋጁ ዝማሬዎችም እንደሚቀርቡ የዝግጅቱ መርሃ ግብር ያስረዳል።

በማኅበራዊ መገናኛዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሥነ-ሥርዓት ነው

መስከረም 19/2016 ዓ. ም. ማታ የሚካሄደው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በቫቲካን ዩቲዩብ ሚዲያ በኩል በስምንት ቋንቋዎች በቀጥታ እንደሚተላለፍ ታውቋል። በማኅበራዊ መድረኮች አማካይነት ክስተቱን በማስመልከት የሚወጡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ማግኘት የሚፈልጉ ተከታታዮች በፌስቡክ እና በኢስታግራም፥ @30Sept2023 ፣ #together2023 እና በኤክስ (የቀድሞው የትዊተር መስመር)፡ @Together2023 ማኅበራዊ ሚዲያዎች መከታተል እንደሚችሉ ታውቋል።

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሰኞ መስከረም 14/2016 ዓ. ም. ይፋ እንዳደረገው፥ ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. ከሚቀርብ የዋዜማ ጸሎት አስቀድሞ ከሰዓት ከአሥራ አንድ እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ አራት ስጦታዎችን ያማከሉ የምስጋና ጸሎቶች የሚቀርቡ ሲሆን እነርሱም፥ ለሲኖዶሳዊ ጉዞ እና ለአንድነት ስጦታ የሚቀርብ የምስጋና ጸሎት፣ ሌላውን የማግኘት ስጦታ፣ ለሰላም ስጦታ እና ለፍጥረት ስጦታ የሚቀርቡ የምስጋና ጸሎቶች ናቸው። ወቅቱ አብያተ ክርስቲያናት የፍጥረት ወቅትን በአንድነት የሚያከብሩበት ወቅት በመሆኑ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በዛፎች እና በአበባዎች ከመሸፈኑ በተጨማሪ በቅዱስ ዳሚያኖ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ የቅዱስ ፍራንችስኮስ መስቀልም በአደባባዩ እንደሚተከል ታውቋል።

ወጣቶች እና መላው ዓለም በጸሎት ይተባበራል

ከመስከረም 18-20/2016 ዓ. ም. ድረስ በሮም አካባቢ ሊካሄድ በታቀዱ አውደ ጥናቶች እና ስብሰባዎች ላይ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የተነገረ ሲሆን፥ ዝግጅቱ ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. ከሚቀርብ የዋዜማ ጸሎት ቀደም ብሎ ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባሲሊካ ውስጥ የሚቀርበውን የምስጋና እና የአምልኮ ጸሎትን እንደሚያካትት ታውቋል።

ወጣቶቹ የሚያካሂዷቸው አውደ ጥናቶች መሪ ሃሳብ፥ ስደተኞች የሚያካፍሉትን ልምድ ማዳመጥ፣ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት እና ቤተ እምነቶች መማር፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን እና የተገለሉ ወገኖችን መጎብኘት፣ በተለያዩ ባሕሎቻች ውስጥ የሚገኘውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ፣ ሥነ-ምህዳርን በማስመልከት የሚቀርቡ የፓናል ውይይቶችን መከታተል እና ፍጥረትን መንከባከብ የሚሉት ይገኙበታል።

በተመሳሳይም መስከረም 19/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ከሚቀርብ የአብያተ ክርስቲያናት ጸሎት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ከ200 በላይ የጋራ ጸሎቶች እና የአስተንትኖ ሥነ-ሥርዓቶች በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድም መዘጋጀታቸው ታውቋል።  

26 September 2023, 16:42