ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ቅዱሳን ቄረሊዮስ እና መቶድየስ የስላቭ ሐዋርያት ናቸው ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ከቫቲካን ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 14/2016 ዓ.ም ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም “ለስብከተ ወንጌል ያለው ፍቅር፡- የምእመናን ሐዋርያዊ ቅንዓት” በሚል ዐብይ አርዕስት ስያደርጉት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይና “የቅዱሳን ቄርልዮስ እና መቶደስ የስላቪ ሐዋርያት” በሚል ንዑስ አርዕስት የቀረበ የክፍል 24 የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱሳን ቀርልዮስ እና መቶድየስ የስላቭ ሐዋርያት ናቸው ማለታቸው ተገለጸ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው ምንባብ

ስለዚህ ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ፣ ከተገረዙት ወገን የነበሩ አማኞች ነቀፉት፤ 3እንዲህም አሉት፤ “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ።” ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ነገሩን በቅደም ተከተል ያስረዳቸው ጀመር፤ ...“እኔም ገና መናገር ስጀምር፣ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ በእነርሱም ላይ ወረደ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን ለእኛ የሰጠንን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፣ ታዲያ፣ እግዚአብሔርን መቋቋም እችል ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” (የሐዋርያት ሥራ 11,2-4.15.17)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ “የስላቭ ሐዋርያት” ተብለው እስኪጠሩ ድረስ በምስራቅ ውስጥ በጣም ታዋቂ ስለነበሩት ቄርልዮስ እና መቶድየስ ሁለት ወንድማማቾች እነግራችኋለሁ። በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመኳንንት ቤተሰብ ውስጥ በግሪክ የተወለዱት ራሳቸውን ለገዳማዊ ሕይወት ለማዋል የፖለቲካ ሥራቸውን ትተዋል። ነገር ግን የታቀደው የመኖር ህልማቸው ተሞክሮ አጭር ነበር። ሚስዮናውያን ሆነው ወደ ታላቋ ሞራቪያ ተልከዋል፤ እሱም በዚያን ጊዜ የተለያዩ ሕዝቦችን ያካተተ፣ ቀድሞውንም በከፊል ወንጌል የተሰበከ ቢሆንም ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ አረማዊ ልማዶችና ወጎች ይገኙበት ነበር። በእዚያን ጊዜ የነበረው ንጉሥ የክርስትናን እምነት በቋንቋቸው የሚያስረዳ አስተማሪ ጠየቀ።

ስለዚህ ቄርልዮስ እና መቶድየስ የመጀመሪያ ተግባር የእነዚያን ህዝቦች ባህል በጥልቀት ማጥናት ነበር። ሁሌም አንድ ዓይነት ጥንቃቄ እና እቀባ እምነት መመስረት እና ባህሉ መሰበክ አለበት። እምነትን ማዳበር፣ የባህል ወንጌላዊነት፣ ሁልጊዜ አስፈላጊ ነው። ቄርልዮስ የቋንቋ ፊደል እንዳላቸው ጠየቀ እነርሱም የለንም ብለው መለሱለት።  እሱም “በውሃ ላይ ንግግርን ማን ሊጽፍ ይችላል?” ሲል መለሰ። በእርግጥም፣ አንድ ሰው ወንጌልን ለማወጅና ለመጸለይ ትክክለኛ፣ ተስማሚ፣ የተለየ መሣሪያ ያስፈልገው ነበር። ስለዚህ የግላጎሊቲክ ፊደላትን ፈጠረ። መጽሐፍ ቅዱስንና የአምልኮ ሥርዓቶችን ተርጉሟል። ሰዎች የክርስትና እምነት ‘ባዕድ’ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ነበር፣ ይልቁንም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚነገር እምነታቸው ሆነ። እስቲ አስቡ፡- ሁለት የግሪክ መነኮሳት ለስላቭ ሕዝቡ ፊደል ፈጠሩ። በመካከላቸው ወንጌሉ ሥር እንዲሰድ ያደረገው ይህ የልብ መገለጥ ነው። ሁለቱ ምንም ፍርሃት አልነበራቸውም ደፋር ነበሩ።

በጣም ብዙም ሳይቆይ ግን አንዳንድ የላቲን ሰዎች ለስላቭ መስበክን በብቸኝነት ተቆጣጥረው ስለነበረ ይህንን የተነፈጉ መስሎ ስለታያቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎች ብቅ አሉ። በቤተክርስቲያን ውስጥ ውጊያ የሚጀመረው ሁሌም እንደዛ ነው። ተቃውሟቸው ሃይማኖታዊ ነበር፣ ነገር ግን እንዲያው ለታይታ ብቻ ነው፡- እግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችለው በመስቀል ላይ በተጻፉት በሦስቱ ቋንቋዎች ማለትም በዕብራይስጥ፣ በግሪክና በላቲን ቋንቋ ብቻ ነው አሉ። የራሳቸውን የራስ ገዝ አስተዳደር ለመጠበቅ የተዘጋ አስተሳሰብ ነበራቸው። ቄርልዮስ ግን በጠንካራ ሁኔታ ምላሽ ሰጠ፡- እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ በቋንቋቸው እንዲያመሰግኑት ይፈልጋል። ከወንድሙ መቶድየስ ጋር በመሆን ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይግባኝ ጠየቀ እና በኋላ ደግሞ የሥርዓተ አምልኮ ጽሑፎቻቸውን በስላቭ ቋንቋ አጽድቀዋል። በቅድስት ማርያም ሜጀር ቤተክርስቲያን መሠዊያ ላይ ትርጉሞቻቸው እንዲቀመጡ ተደርገ፣ እና በእነዚያ መጻሕፍት መሠረት የጌታን ውዳሴ አብሯቸው ዘመሩ። ቄርልዮስ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሞተ፣ እና ቅሬት አካሉም አሁንም እዚህ ሮም፣ በቅዱስ ክሌመንት ባዚሊካ ውስጥ ይገኛል። መቶድየስ በምትኩ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሞ ወደ ስላቭ ግዛቶች ተመለሰ። እዚያ ብዙ መከራ ይደርስበት ነበር፡ እሱ እንኳን ይታሰር ነበር፣ ነገር ግን ወንድሞች እና እህቶች፣ የእግዚአብሔር ቃል በእነዚያ ህዝቦች ውስጥ እንዳልታሰረ እና ሳይሰራጭ አለመቅረቱን እናውቃለን።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የአውሮጳ ጠባቂ ቅዱሳን እንዲሆኑ የመረጣቸውንና በላቲን ቋንቋ “ስላቮረም አፖስቶሊ” (የስላቭ ሐዋርያት) የተሰኘ ጳጳሳዊ መልእክት የጻፋላቸው የእነዚህን ሁለት ወንጌላውያን ምስክርነት ስንመለከት ሦስት ጠቃሚ ገጽታዎችን እንመልከት።

በመጀመሪያ አንድነት። ግሪኮች፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና ስላቮች: በዚያን ጊዜ, በአውሮፓ ውስጥ ያልተከፋፈለ ክርስትና ነበር እሱም ለወንጌል ስርጭት ሚና ተጫውቶ እና ተባባሪ ነበር።

ሁለተኛው ጠቃሚ ገጽታ ከባሕል ጋር ማዋሃድ ሲሆን ከዚህ ቀደም እንደተናገርኩት ከሆነ ባሕሉን ባዋዛ መልኩ ስብከተ ወንጌል ማድረግ ወንጌልና ባህሉ ጥብቅ ትስስር እዲኖራቸው ያደርጋል። አንድ ሰው በረቂቅ፣ በተጣራ መንገድ ወንጌልን መስበክ አይችልም፣ አይደለም፡ ወንጌል ባሕልን ያዋዛ መሆን አለበት፣ የባህል መግለጫም ነው።

የመጨረሻው ገጽታ ነፃነት ነው። ስብከት ነፃነትን ይጠይቃል ነፃነት ግን ሁሌም ድፍረትን ይፈልጋል። አንድ ሰው ደፋር እስከሆነ ድረስ ነፃ ነው እናም ነፃነቱን በሚነጠቁ ብዙ ነገሮች እንዲታሰር አይፈቅድም።

ወንድሞች እና እህቶች፣ የ"በፍቅር የተሞላ ነጻናት” መሳሪያዎች እንሆን ዘንድ የስላቭስ ሐዋርያት የሆኑትን ቅዱሳን ቄርዮስ እና መቶድየስን እንጠይቅ። በጸሎት እና ሐሳብ የማመንጨት ችሎታ ያለን እንሆን ዘንድ፣ የማያቋርጥ እና ትሁት ለመሆን ይረዱን ዘንድ የቅዱሳኑን አማላጅነት እንጠይቅ።

25 October 2023, 13:34

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >